የመን፤ የጦርነት ድርድር፤ የድርድር ጦርነት ምድር | ዓለም | DW | 20.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የመን፤ የጦርነት ድርድር፤ የድርድር ጦርነት ምድር

ድርድሩ ግን ቀጥሏል።የተደራዳሪዎችን ወጪ ከሚሸፍኑት አስራ-ስምንት ሐገራት ሳዑዲ አረቢያን ጭምሮ አስሩ ድርድሩ መቀጠሉን ፈቅደዋል።ጦርነቱም ቀነሰ እንጂ አልተቋረጠም።ተፋላሚዎች ድርድሩ ሚያዚያ መጀመሪያ ላይ ሲጀምሩ ያወጁት ተኩስ አቁም ተከብሮ አያዉቅም።ሰዉም እየሞተ፤ በሕይወት ያለዉ በችግር እየቆራመደ ነዉ-

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:36

የመን

የየመን ተፃራሪ ፖለቲከኞች እዚያዉ ሰነዓ፤ ሪያድ፤ ዤንቭ በቅርቡ ደግሞ ኩዌት ዉስጥ ይደራደራሉ።ደጋፊ አስታጣቂዎቻቸዉም ለዉይይት ድርድሩ ስኬት እንደሚጥሩ ቃል ይገባሉ።ወዲያዉ ግን ይዋጋሉ።ደሞ በተቃራኒዉ በሐገር ሽማግሌዎች አግባቢነት ታኢዝ፤ራዳ፤ደማር ላይ ምርኮኛ ይለዋወጣሉ።ካፍታ ፋታ በኋላ እንደገና ይዋጋሉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ እስከ2011 ድረስ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የኢትዮጵያ፤የሶማሊያ፤የኤርትራ፤ የኢራቅ ስደተኞች መሥፈሪያ ወይም መተላለፊያ ነበረች።ዛሬ የዓለም ስደተኞች ቀን ሲዘከር በስደተኛ ተፈናቃይ ብዛት በመጀመሪያዉ ረድፍ ከተሰለፉት ሐገራት አንዷ ናት።የመን። የጦርነት ድርድር፤የድርድር ጦርነቱ ሒደት ዉጤት ምን ይመስላል?

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ኮሚሽነር UNHCR የበላይ ሐላፊ ፊሊፖ ግራንዲ፤ የዓለም ስደተኞች ቀን ዛሬ ሲከበር እንዳሉት ዓለም ከየ113ቱ ነዋሪዋ አንዱ ስደተኛ ነዉ።በየደቂቃዉ 24 ሰዉ ይሰደድባታል።ድምር 65 ሚሊዮን ሕዝብ።«ተገድዶ የሚፈናቀለዉ ሕዝብ ቁጥር 65 ሚሊዮን ነዉ።ይሕ ቁጥር አምና ከነበረዉ ከሐምሳ ዘጠኝ ሚሊዮን ትንሽ የሚበልጥ ስደተኛ በአስር በመቶ የጨመረ ነዉ።»

ቁጥሩ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ ዓለም አይታዉ የማታዉቀዉ አዲስ ነዉ።መፍትሔዉ ግን በርግጥ አዲስ አይደለም።የሕዝብ እልቂት ስደትን ሙሉ በሙሉ ማቆም ባይቻል እንኳን ለመቀነስ አብነቱ ጦርነት፤ ግጭት ዉዝግብን በድርድር ማስወገድ ነዉ።ግራንዲም ዛሬ ሌላ አላሉም።

«እርምጃ መዉሰድ አለብን።ፖለቲካዊ እርምጃ።የስደተኛን ብዛት ለመቀነስ በጣም አስፈላጊዉ ነገር ይሕ ነዉ»የየመን ተፋላሚ ሐይላት እና አዝማቾቻቸዉ ካለፈዉ ታሕሳስ ጀምረዉ ዉይይት፤ ድርድር

ሲሉ ለአዲሱ ችግራቸዉ አሮጌዉን ግን ተገቢዉን መፍትሔ የመምረጥ፤ የመዘየድ ወይም የመገደዳቸዉ ምልክት ሆኖ ነበር።ወትሮም ከአረብ ሐገራት ሁሉ እጅግ የደኸየችዉን ሐገር የሚያወድመዉን ጦርነት ለማስቆም በስማ በለዉ ሰነዓ ተጀምሮ አደን፤ሪያድ ዤኔቭ እያለ ባለፈዉ ሚያዚያ ኩዌት ላይ ፊት ለፊት ከቀጠለዉ ድርድር ዉጪ ብዙዎች እንደሚሉት የተሻለ አማራጭ አልነበረም።

ከአምና መጋቢት ጀምሮ በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉትን የሁቲ አማፂያንን የሚደበድቡት ሳዑዲ አረቢያና ተከታዮችዋም የጦርነቱ ኪሳራ እየቆጠቆጣቸዉ ነዉ።የሪያድ ነገስታት ግፋ ቢል «በሰወስት ወር» እናጠናቅቀዋለን ብለዉ ከተሞጀሩበት ጦርነት «የጎበዝ መዉጪያዉ በር» ድርድር መሆኑን የመረዳታቸዉ ማረጋገጪያም ነበር።ሪያድ የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ስለሺ ሽብሩም ከመጋቢት ጀምሮ ይሕ ታዝቧል።

ሳዑዲ አረቢያ እንደዘበት ለገባችበት ጦርነት እስካሁን ድረስ ከ5.3 ቢሊዮን ዶላር በላሽ ከስክሳለች።ሳዑዲ አረቢያን ተከትለዉ ከካይሮ-እስከ ካርቱም ከዳካር እስከ ራባት፤ ከአማን እስከ ማናማ ከጦርነቱ የተሞጀሩ አስር መንግስታት አሉ።ብላክ ዎተር የተሰኘዉ የአሜሪካ ቅጥረኛ ወታደሮች አዝማች ድርጅትም የጦርነቱ ተካፋይ ነዉ።ለቅጥረኛ ወታደሮቹ የሚከፈለዉን ጨምሮ አስሩ ሐገራት እስካሁን ያወጡት ገንዘብ ከሳዑዲ አረቢያዉ አይተናንስም ነዉ-የሚባለዉ።

የጦርነቱ መቆም በተለይ ለሳዑዲ አረቢያ ወጪን ከመቀነስም በላይ በጣም የሚያስፈልግበት ምክንያት አለ።እንደገና ስለሺ ሽብሩ።ድርድሩ ለአግባቢ ዉጤት እንዲበቃ በጦርነቱ የሚያልቅ፤የሚፈናቀል የሚሰደደዉን ሕዝብ ያሕል የሚመኝ የሚፀልይ በርግጥ የለም።የሰነዓዉ ተባባሪ ዘጋቢያችን ግሩም ተክለ ሐይማኖት እንደሚለዉ የኩዌቱ ድርድር እንደተጀመረ የነበረዉ ምኞት ተስፋ ግን አሁን እየደበዘዘ ነዉ።

ተደራዳሪዎች እስካሁን የደረሱበት ሰምምነት የለም።አስረኛ ሳምንታቸዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ኢስማኢል

ኡሉድ ሼኽ አሕመድ ያዘጋጁት ባለሰወስት ነጥብ የመደራደሪያ ሐሳብ ቢያንስ እስካሁን ተፋላሚ ሐይላትን አላግባባም።በተለይ አማፂኑ ትጥቃቸዉን ፈትተዉ ሰነዓን ጨምሮ የሚቆጣጠሯቸዉን አካባቢዎች በሳዑዲ አረቢያ ለሚደገፈዉ መንግሥት እንዲያስረክቡ የሚጠይቀዉ ነጥብ በሁቲዎቹ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም።

ድርድሩ ግን ቀጥሏል።የተደራዳሪዎችን ወጪ ከሚሸፍኑት አስራ-ስምንት ሐገራት ሳዑዲ አረቢያን ጭምሮ አስሩ ድርድሩ መቀጠሉን ፈቅደዋል።ጦርነቱም ቀነሰ እንጂ አልተቋረጠም።ተፋላሚዎች ድርድሩ ሚያዚያ መጀመሪያ ላይ ሲጀምሩ ያወጁት ተኩስ አቁም ተከብሮ አያዉቅም።ሰዉም እየሞተ፤ በሕይወት ያለዉ በችግር እየቆራመደ ነዉ-ግሩም እንደሚለዉ።የ

ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር በየመኑ የርስበርስ ጦርነት ጣልቃ ከገባ ካለፈዉ ዓመት መጋቢት ወዲሕ ከ6ሺሕ አራት መቶ በላይ ሰላማዊ ሰዉ ተገድሏል።አብዛኛዉ የተገደለዉ በተባባሪዎቹ ሐገራት የአዉሮፕላን ቦምብ ነዉ።እስከ 2011 ድረስ የኢትዮጵያ፤ የኤርትራ፤ የኢራቅ በተለይ ደግሞ ከ250 ሺሕ በላይ የሶማሊያ ስደተኞችን ስታስናግድ የነበረችዉ ሐገር ባለፈዉ አንድ ዓመት ብቻ ከ2,8 ሚሊዮን በላይ ሕዝቧ አንድም ስደተኛ አለያም ተፈናቃይ ነዉ።25 ሚሊዮን ከሚገመተዉ ሕዝቧ 85 ከመቶ ያሕሉ አስቸኳይ የምግብ ርዳታ ፈላጊ ነዉ።

የሰነዓዉ ተባባሪ ዘጋቢያችን ግሩም ተክለሐይማኖት እንደሚለዉ ሐብቱ ሞልቶ የተረፋቸዉ ምራባዉያን መንግሥታት ለችግረኛዉ ሕዝብ የሚሰጡት ርዳታ የለም።ካለም አይታይም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተለይ UNHCRም የሟች-ተፈናቃይ-ስደተኛዉን ቁጥር ከመዘርዘር ባለፍ ለተፈናቃይ-ስደተኛዉ የሚሰጠዉ ርዳታ የሌለ ያክል ነዉ።

አረረም መረረ ለሕዝቡ እሕል የሚያቃምሱት አንድም የሐገሬዉ ሐብታሞች አለያም የሳዑዲ አረቢያ መንግሥትና በጎ አድራጊዎች ናቸዉ።ግሩም እንደሚለዉ።ከጦርነቱ በፊት ሳዑዲ አረቢያ ለገቡ የየመን ዜጎች ደግሞ የሳዑዲ አረቢያ በጦርነቱ መካፈል ሳይደግስ አይጣላም አይነት ነዉ-የሆነዉ።

የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት የየመኖችን ልብና አዕምሮ ለመግዛት በሐገሩ የሚገኙ ሁለት ሚሊዮን የመኖችን እየተንከባከበ ነዉ ።ስለሺ ሽብሩ እንደሚለዉ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚኖሩ ስደተኞችም ሕጋዊ መኖሪያ ፍቃድ እየተሰጠ ነዉ።

ከፖለቲካዊ ድርድሩ ይልቅ እስካሁን ተጨባጭ ዉጤት ያሳየዉም የሐገር ሽማግሌዎች ወይም ሼኾች የመሩት ሽምግልና ነዉ።የተለያዩ አካባቢዎችን የሚወክሉ ሽማግሌዎች ተፋላሚ ሐይላትን አግባብተዉ ምርኮኞች እንዲለዋወጡ አድርገዋል።የሁቲ አማፂያን ደግሞ ዛሬ የረመዳን ወርን ምክንያት በማድረግ ከሁለት መቶ በላይ የመንግሥት ደጋፊዎችን ከእስር ለቀዋል።

የምርኮኛ ልዉዉጥ መደረጉ ወይም እስረኞች መፈታቸዉ በተነገረ በሰዓታት ልዩነት ዉስጥ ግን ዉጊያ መግጠማቸዉ እንቆቅልሹ።ጦርነቱ በሳዑዲ አረቢያ እና በኢራን የሚደገፉ የሚባሉት ሐይላት ብቻ አይደለም።የአል ቃኢዳ፤የእስላማዊ መንግሥት፤ የጎሳ ታጣቂዎች፤ የአካባቢ ሽፍቶች ጭምር እንጂ።የመን። የጦርነት-ድርድር፤ የስምምነት፤ ጦርነት እንቆቅልሽ ምድር።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic