የመን «የዓላማ ቢስ ጦርነት» ምድር | ዓለም | DW | 21.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የመን «የዓላማ ቢስ ጦርነት» ምድር

የፖለቲካ ተንታኝ ፈሪኢድ አል ሙስሊሚ እንዳሉት ጦርነቱ ለየመኖች፤ ለሳዑዲዎች፤ ለመላዉ የአካባቢዉ ሐገራት ሕዝብ ከጥፋት በስተቀር «ዓላማ ቢስ» ይሆን ይሆናል።ለለንደን-ዋሽግንተን-ኦታዋ የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪዎች ግን ቢሊዮነ ቢሊዮናት ዶላር እየዛቁበት ዓላማ ቢስ መሆኑ በርግጥ ያጠያይቃል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:53
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
12:53 ደቂቃ

የመን «የዓላማ ቢስ ጦርነት» ምድር

ዕለት-በዕለት ትወድማለች።ወትሮም ከድሕነት ያልተላቀቀዉ ሕዝቧ አንድም በቦምብ፤ በጥይት፤ በካራ አለያም በበሽታ ሰዓት በሰዓት ያልቃል።«የታደለዉ» ይሸሻል።የመን።ሳዑዲ አረቢያ መራሹ የዉጪ ጦር ጥፋት፤ እልቂት፤ ፍጅት ስደቱን ማጋጋም ከጀመረ ዘንድሮ መጋቢት ዓመት ደፈነ። የመካከለኛዉ ምሥራቅ የፖለቲካ ተንታኝ ፈርኢድ ዓል ሙስሊሚ «ግልፅ ዓላማ እና ግልፅ ጠላት የሌለዉ» ጦርነት ይሉታል።ጦርነቱን ለማስቆም እስካሁን የተደረጉት ሙከራዎች ከሙከራ አላለፉም።አሁንም ሌላ ሙከራ መደረጉ ከወደ ሪያድ ተስምቷል።ያም ሆኖ እንደ ጦርነቱ ዓላማ ሁሉ ሰላም የማስፈኑ ጥረትም ግልፅ አይደለም።አንድ ነገር ግልፅ ነዉ።ጥፋቱ።

የብሪታንያ መንግሥት የመንን የሚደበድቡትን ሐይላት መደገፉን በተለይም ለሳዑዲ አረቢያ የጦር መሳሪያ መሸጡን በመቶ የሚቆጠሩ የብሪታንያ ዜጎች ባለፈዉ ሳምንት አርብ ባደባባይ ሰልፍ ተቃዉመዉ ነበር።የሠልፉ አስተባባሪዎች እና የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት የብሪታንያ መንግሥት ለሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር የስለላ መረጃ ከማቀበል አልፎ ካለፈዉ ሰኔ እስከ ጥር በተቆጠረዉ ስድስት ወር ላንዲት ሳዑዲ አረቢያ ብቻ የ4.3 ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያ ሸጧል።ካናዳም በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ጦር መሳሪያ ለሳዑዲ አረቢያና ለተባባሪዎቹ መንግሥታት ቸብችባለች።

ዩናይትድ ስቴትስ ለሳዑዲ አረቢያ እና ለተባባሪዎችዋ የምትሰጠዉ የስለላ መረጃ፤ሥልጠና፤ የምትሸጠዉ የጦር መሳሪያ ብዛት እና ዋጋ ብሪታንያና ካናዳ ከሚሸጡት በእጥፍ ይበልጣል።የፖለቲካ ተንታኝ ፈሪኢድ አል ሙስሊሚ እንዳሉት ጦርነቱ ለየመኖች፤ ለሳዑዲዎች፤ ለመላዉ የአካባቢዉ ሐገራት ሕዝብ ከጥፋት በስተቀር «ዓላማ ቢስ» ይሆን ይሆናል።ለለንደን-ዋሽግንተን-ኦታዋ የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪዎች ግን ቢሊዮነ ቢሊዮናት ዶላር እየዛቁበት ዓላማ ቢስ መሆኑ በርግጥ ያጠያይቃል።

ሳዑዲ አረቢያ፤የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፤ባሕሬን፤ ኩዌይት፤ቃጣር፤ ግብፅ፤ ዮርዳኖስ፤ ሞሮኮ፤ ሱዳን እና ሴኔጋል በቀጥታ ሌሎች በርካታ መንግስታት በተዘዋዋሪ በከፈቱት ጥቃት ዓደንን የመሳሰሉ ትልልቅ የየመን ከተሞችን የዘይዲ እስልምና ሐራጥቃን ከሚከተሉት ከሁቲ ሚሊሺያዎች እጅ ማርከዋል።ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሸሽተዉ የነበሩትን የየመን ፕሬዝደንት አብድ ረቦ መንሱር ሐዲ እና ሚንስትሮቻቸዉን ወደ የመን መልሰዋል።

ፕሬዝደንቱ ጊዚያዊ ቤተ-መንግስት የመሰረቱባት አደን ግን ከመንግሥት ደጋፊ ሚሊሺያዎች እኩል የአል-ቃኢዳ፤ የISIS እና የሌሎች አሸባሪ ቡድናት መናኸሪያ ሆናለች።የሰነዓዉ ተባባሪ ወኪላችን ግሩም ተክለ ሐይማኖት።መግሥት ከሌለ ወይም ከተጨናገፈ ወሮበላ ወይም አሸባሪ አለ።የቀድሞዎቹ የዩናይትድ ስቴትስ እና የብሪታንያ መሪዎች ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ እና ቶኒ ብሌር በ2003 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የኢራቅን መንግሥት ሲያፈርሱ የተተኩት አልቃኢዳ እና ብጤዎቹ ነበሩ።አሁንም ናቸዉ።

የኢትዮጵያ ጦር የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤት ሕብረትን በ2006 ሲያፈርስ ሶማሊያን የተቆጣጠረዉ አል-ሸባብ ነበር።በአብዛኞቹ የሶሪያ ግዛቶችም ከ2011 ጀምሮ ሌላ አልታየም።የምራባዉያን መንግሥታት ሊቢያን ለመዉረር ሲጋበዙ አፍሪቃ ዳግማዊት ሶማሊያን ማስተናገድ አትችልም እያሉ ያስጠነቀቁ፤ የተማፀኑም ብዙ ነበሩ።የተቀበላቸዉ ግን የለም።

የለንደን፤ፓሪስ፤ ዋሽግተን መሪዎች የሊቢያ ዘመቻ፤ ሰሜን አፍሪቃዊቱን ሐገር ለISIS እና በብዙ መቶ ለሚቆጠሩ ሚሊሺያ ቡድናት ከማስረከብ ባለፍ ቢያንስ እስካሁን ለዓለም ሰላም የተከረዉ የለም።

የሪያድ፤ዶሐ፤ ማናማ፤ ካይሮ እና ብጤዎቻቸዉ ገዢዎች እርምጃም ሁቲዎችን አጥፈተዉ የመንን የአሸባሪዎች መፈንጫ እንዳያረጓት እያሰጋ ነዉ።GIGA በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የጀርመን ጥናት ተቋም የመካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳይ አጥኚ ስቴፋን ሮዚንይ እንደሚሉት ሊቢያ ዳግማዊት ሶማሊያ ከሆነች የመን ዳግማዊት ሊቢያ ናት።

«ኢራቅና ሶሪያ ዉስጥ የሆነና የሚሆነዉ ሊቢያ ብቻ አይደለም የመንም እየተደገመ ነዉ።(የጠንካራ) መንግሥት አለመኖር ISIS እራሱን ለማደራጀት በጣም ይጠቀምበታል።በጣም የሚያሳዝነዉ የየመን ነዉ።የመን ዉስጥ የሥልጣን ክፍተት እንዲፈጠር የምዕራባዉያን ተሻራኪዋ ሳዑዲ አረቢያ አስተዋፅዖ ማድረጓ ነዉ።»

ሳዑዲ አረቢያ እና ተባባሪዎችዋ ባለፈዉ ዓመት የመንን በጦር ጄት መደብደብ የጀመሩት ሺዓይቱ ኢራን የሁቲ ሚሊሺያዎችን እና ከሚሊሺያዎቹ ጋር ያበረዉን የቀድሞዉን ፕሬዝደንት የዓሊ አብደላ ሳላሕን ጦር እየደገፈች ነዉ በሚል ሰበብ ነበር።ዓሊ አብደላ ሳሌሕ የመንን ሰላሳ-ሁለት ዓመት የገዙት በቴሕራኖች እየተደገፉ ከነበረ ሪያዶች ድፍን ሰላሳ-ሁለት ዓመት የትነበሩ? ኢራኖች ሁቲዎችን ደግፈዉ የሚዋጉ ከሆነ ሳዑዲ አረቢያ መራሹ የዉጪ ጦር ይሁን የፕሬዝደንት አብድ ረቦ ሐዲ ሚሊሺያ አንድ የኢራን ዜጋ እንኳን መግደል ወይም መማረክ እንዴት አቃተዉ?

መልስ የለሽ ጥያቄ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር የመንን መደብደብ ከጀመረበት ካለፈዉ ዓመት ጀምሮ ከስድስት ሺሕ በላይ ሰዉ ተገድሏል።የሰነዓዉ ተባባሪ ወኪላችን ግሩም ደጉ በየዕለቱ፤በየሥፍራዉ የሚያልቀዉን በተለይ ኢትዮጵያዊ ስደተኛዉን የቆጠረዉ የለም ባይ ነዉ።

ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክም ከጂዳ-ሳዑዲ አረቢያ ይኽንኑ ያጠናክራል።የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሐላፊ ዘይድ ረዓድ አል ሁሴይን እንደሚሉት የመን ዉስጥ ከተገደሉት ከስድስት ሺሕ በላይ ሰዎች ከግማሽ የሚበልጡትን የገደለዉ ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር ነዉ።ጦርነቱ የመን ዉስጥ በንብረት ላይ ያደረሰዉ ጥፋት በዉል አይታወቅም።አንዲት ሳዑዲ አረቢያ ብቻ ግን በቀን ሁለት መቶ ሚሊዮን ዶላር ታወጣለች።

በወር ስድት ቢሊዮን ዶላር። እስካሁን ከሰባ-ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ከስክሳለች።ሐገሪቱ ለ2016 የያዘችዉ በጀት የ87 ቢሊዮን ዶላር ጉደለት አለዉ።በየሳዑዲ አረቢያ በጀት ይሕን ያሕል ጉድለት ሲያጋጥመዉ በቱጃሪቱ ሐገር የቅርብ ዘመን ታሪክ የመጀመሪያዉ ነዉ።ለጉድለቱ ሳዑዲ አረቢያ ለየመንና ለሶሪያ ጦርነት የምታወጣዉ ገንዘብ መብዛት ከነዳጅ ዘይት ዋጋ መቀነስ ጋር ተዳምሮ ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች ናቸዉ።

የወጪዉ መብዛት እና የሰላማዊ ሰዎች እልቂት በማየሉ ሰበብ በንጉስ ሰልማን አገዛዝ ከዉጪ የሚሰነዘረዉ ወቀሳ ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ ዘልቆም ብልጭ ድርግም እያለ ነዉ።በየመኑ ጦርነት በአንድ ዓመት ጊዜ ዉስጥ የታሰበዉ ድል አለመገኘቱ፤ ቀደም ሲል እንደተፈራዉ ኢራን በቀጥታ ከጦርነቱ አለመግባትዋ የሳዑዲ መሪዎች ሌላ ብልሐት እንዲያሰላስሉ ሳያስገድዳቸዉ አልቀረም።ድርድር።

የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት የተማረኩ ወታደሮቻቸዉን ለማስፈታት ከዛይዲ መንፍሳዊ መሪዎች እና የሐገር ሽማግሌዎች ጋር ባደረጉት ድርድር ጥሩ ዉጤት አግኝተዋል።በተባበሩት መንግስታት የሳዑዲ አረቢያ አምባሳደር አብዱላሕ አል ሞአላሚ እንዳስታወቁት ደግሞ የሪያድ ገዢዎች ከሁቲ አማፂያን መሪዎች ጋር መደራደር ጀምረዋል። ድርድሩ በይፋ ሳይነገር ሪያድ ዉስጥ በሚደረግበት ወቅት የጄት ድብደባዉም ረገብ ብሎ ነበር።

የሳዑዲ አረቢያ እና የሁቱ አማፂያን የሚስጥር ድርድር ያስገኘዉ ዉጤት እንደ ድርድሩ ሁሉ ሚስጥር ነዉ።ይሁንና በሳዑዲ አረቢያ ለሕልዉናዉ የምትፋለምለት የፕሬዝደንት አብድ ረቦ መንሱር ሐዲ መንግሥትና አማፂያኑ ላንድ ሳምንት ተኩስ ለማቆም ትናንት ተስማምተዋል።ዘገቦች እንደጠቆሙት የሁለቱ ወገኖች ተወካዮች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ በዑስማኤል ዑሉድ ሼኽ አሕመድ አማካይነት የደረሱበት ተኩስ አቁም ዉል የሚቀጥለዉ ድርድር እስከሚደረግ ሊራዘም ይችላልም።ድርድሩ የፊታችን ሚያዚያ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል። ዓላማ ቢሱ ጦርነት ዓላማ ባለዉ ሠላም ይተካ ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ

Audios and videos on the topic