የመን፤ ከድጡ ወደ ማጡ | ዓለም | DW | 30.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የመን፤ ከድጡ ወደ ማጡ

በሳዑዲ አረቢያ መሪነት በየመን የሁቲ አማጽያን ላይ የሚካሄደው የአየር ጥቃት ለአምስተኛ ቀን ቀጥሏል። ዛሬ ለሊት ሁለት የጦር አውሮፕላኖች በየመን ቤተ-መንግስት አቅራቢያ ድብደባ መፈጸማቸውን ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ከፕሬዝዳንት አብደረቦ መንሱር ሐዲ ሃይሎች ጋር አዲስ ውጊያ የገጠሙት የሁቲ አማጽያን ከአደን ከተማ 30 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ መድረሳቸውም ተሰምቷል። የየመንን ችግር ለመፍታት የአካባቢው አገራት ከድርድር ይልቅ የአየር ድብደባን የመረጡ ይመስላል።

በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በግብጽ ሻርም አልሼክ የተሰበሰቡት የዓረብ ሊግ ሃገራት ዋንኛ የውይይት አጀንዳ የመን እና የሁቲ አማጽያን ሆነው ሰንብተዋል።ውይይቱ መልከ ብዙ የሆነ ይመስላል። በጉባኤው የተሳተፉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅ ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን ውይይት ለችግሩ ብቸኛው መፍትሄ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። የሳዑዲ አረቢያው ንጉስ ሳልማን በበኩላቸው በየመን ሰላም እና መረጋጋት እስኪመለስ ድረድ ሃገራቸው በሁቲ አማጽያን ላይ የምታደርገውን የአየር ጥቃት እንደምትቀጥል ቃል ገብተዋል። የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በቀጣናው ለሚፈጠሩ መሰል ስጋቶች ምላሽ መስጠት የሚችል የጋራ ጦር የማቋቋም ሃሳብ አቅርበዋል። የዓረብ ሊግ ለጊዜው ለሳዑዲ አረቢያ የአየር ጥቃት እውቅና ከመስጠት ባለፈ የቀጣናውን ችግር መፍታት ስለመቻሉ ማረጋገጫ የለም። በኢራቅ፤ሶርያ እና ሊቢያን በመሳሰሉ ሃገሮች ለተፈጠረው ቀውስ የሰጠው አንዳች ምላሽ አልነበረምና።ለጊዜው ግን የመን ከውስጥም ከውጪም ዱላ በዝቶባታል።

መጀመሪያ የመንግስታቸው መቀመጫ የሆነችውን ሰንዓን ተነጠቁ። ሸሽተው በደቡባዊ የመን በምትገኘው የትውልድ መንደራቸው የዓደን ከተማ ተቀመጡ። በዚያም አልሆነላቸውም። የሁቲ አማጽያን ግስጋሴ ያሰጋቸው የየመን ህጋዊ መሪ ፕሬዝዳንት አብድረቦ መንሱር ሐዲ አገራቸውን ለሁቲ አማጽያን፤የጦር ጄኔራሎች እና ታጣቂዎች ጥለው ሳዑዲ አረቢያ ከገቡ ከራረሙ። ፕሬዝዳንቱ የመንን ከርስ በርስ ጦርነት ለመታደግ ያቀረቡት ጥያቄ ከጎረቤታቸው ሳዑዲ አረቢያ ምላሽ ያገኘው ወዲያው ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፈይሳል ቢን አብዱል አዚዝ አል-ሳዑድ ቀጣዩን እርምጃ «ይህ ችግር በሰላም ይፈታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በሰላም ካልተፈታ ግን የአካባቢው አገራት እና የአረቡ ዓለም ቀጠናውን ከዚህ ቀውስ ለመታደግ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ ይወስዳሉ።»ሲሉ ጠቁመው ነበር።

116 የሳዑዲ ዓረቢያ እና የዓረቡ ዓለም ተዋጊ የጦር ጀቶች በሁቲ አማጽያን ላይ የሚወስዱትን እርምጃ «Operation Decisive Storm»ሲሉ ሰየሙት። ባለፈው ሳምንት የተጀመረው ጥቃት የሁቲ አማጽያንን ብቻ ሳይሆን የቀድሞውን የየመን ፕሬዝዳንት የአሊ አብደላ ሳላህን ሃይሎች ጨምሮ በአጋሮቻቸው ላይ ያነጣጠረ ነው። «የአየር ጥቃቱ እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ ተቋማት ላይ ነው።ለሊት ላይ በየአካባቢው የአየር መቃወሚያና ከባድ መሳሪያዎች ተጠምደው አውሮፕላኖች ባለፉ ቁጥር ሲተኮስ ነው የሚያድረው። ቀን ደግሞ ትንሽ በረድ ይላል። ህዝቡም በከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ነው ያለው።» ሲል በየመን የዶይቸ ቤለ ዘጋቢ ግሩም ተክለ ሐይማኖት ይናገራል።

ሳዑዲ አረቢያ የየመንን ውስጣዊ ውጥንቅጥ በአትኩሮት የምትከታተልባቸው ሶስት ምክንያቶች መኖራቸውን የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። የሱኒ እስልምና መሰረት የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ የመን ላይ የሺዓ መንግስት በፍጹም አለመፈለጓን በቀዳሚነት ያነሳሉ። የየመን አለመረጋጋት እና በአገሪቱ የበዙት አሸባሪ ቡድኖች ሁለቱ አገሮች የሚጋሩትን ድንበር ተሻግረው ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ የሚለው ስጋት ደግሞ ሁለተኛው ነው። የሺዓ እስልምናን የሚከተሉትን የሁቲ አማጽያን ከጀርባ ሆና ትረዳለች የሚል ክስ የሚቀርብባት የኢራን መስፋፋት ለሳዑዲ አረቢያ የአየር ጥቃት ሶስተኛው ምክንያት ነው። ሳዑዲ አረቢያ ከየመን በምትዋሰንባቸው አካባቢዎች ወታደሮቿን በተጠንቀቅ ማስፈሯ ተሰምቷል። አገሪቱ ወታደሮቿን ወደ የመን ታዘምታለች የሚለው ሃሳብ ግን አዋጪ አይመስልም። በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ የየመን ዘመቻ ካሁን ቀደም በባህሬን እንደሆነው ቀላል አለመሆኑን ይናገራል።

«የመንን ነዋሪ በአብዛኛው የነፍስ ወከፍ ጠብመንጃ የያዘ ተዋጊ መሳይ ነዋሪ ስለሆነ አገሪቱን ቶሎ ለማረጋጋትና የፕሬዝዳንት አብደረቦ መንሱር ሐዲን መንግስት ወደ ቦታቸው ለመመለስ እጅግ በጣም ፈታኝና አስቸጋሪ ይሆናል።»

የሁቲ አማጽያንን ትረዳለች ተብላ የምትከሰሰው ኢራን በየመን የሚፈጸመው የአየር ድብደባ መፍትሄ አለመሆኑን አስታውቃለች። ግን ሰሚ ያገኘች አይመስልም።

ዩናትድ ስቴትስ ሳዑዲ አረቢያ በየመን ላይ ለምታካሂደው የአየር ጥቃት መረጃ በማቀበል ቅኝት በማድረግ እገዛ ታደርጋለች፡፡ ይህንንው እገዛ ኢራን በአይ.ሲስ. ላይ ለምታደርገው ዘመቻ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኗ ተሰምቷል፡፡ የኢራንን የኔኩሌር መርሃ ግብር አስመልክቶ ድርድር ላይ የከረሙት ሁለቱ ሃገሮች በየመን ጉዳይ ላይ ግን በተቃራኒ ቆመዋል፡፡የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን እና የፖለቲካ ተንታኞች ከሁቲ አማፅያን ጀርባ የኢራን እጅ አለ ሲሉ ይደመጣል፡፡ኢራን አማፅያኑን በምን መልክ እያገዘቻቸው ለመሆኑ በግልፅ የተባለ ነገር የለም፡፡የመን ላይ የሚገኘው ግሩም ተ/ሐይማኖት ሰንዓ ላይ የኢራን ድምጽ በአማፅያኑ አንደበት ጎልቶ ይሰማል ሲል ይናገራል፡፡

«ኢራን ወደ የመን መብረር ካቋረጠች ከ35 አመት በኋላ በቀን ሁለት በሳምንት 14 በረራ መጀመሯ አንድ ፍንጭ ነው። እነሱም በመገናኛ ብዙሃኖቻቸው በግልጽ የሚሉት ነገር አለ።»

እንደ ነብዩ ሲራክ ከሆነ የሱኒ እስልምና መሰረት እንደሆነች የሚነገርላት ሳዑዲ አረቢያ በየመን ቀውስ ከሁቲ አማጽያን ይልቅ ከኢራን ጋር የገቡበት የውክልና ጦርነት አሳስቧታል። የሁቲ አማጽያን በሳዑዲ ላይ ከሚፈጥሩት ይልቅ በሊባኖስ ሂዝቦላህን፤በሶርያ ፤በባህሬንና ኢራቅ ያሉ አማጽያንን ትደግፋለች የሚል ወቀሳ የሚሰነዘርባት ኢራን በየመን የሁቲ አማጽያን በኩል ለሳዑዲ አረቢያን ንጉሳዊ ስርዓት ስጋት ሆናለች።

ትናንት እሁድ የፕሬዝዳንት አብድረቦ መንሱር ሐዲ ታማኞች በአደን ከተማ ከሁቲ አማፅያን ጋር መዋጋቸውን ሬውተርስ የዝና ወኪል ዘግቧል፡፡በግጭቱ ሶስት ሰዎች መገዳላቸውንና እና የፕሬዝዳንቱ ታማኝ ሃይሎች በከተማዋ የሚገኘውን የአውሮፕላን ማረፊያ መቆጣጠራቸው ተሰምቷል፡፡በሳዑዲ አረቢያ የአየር ጥቃት 35 ሰዎች ሲሞቱ 88 መቁሰላቸውን የዜና አውታሩ ጨምሮ ዘግቧል፡፡ የአረብ ሊግ የግብፅ ጉባኤ ሲጠናቀቅ በየመን የሁቲ አማፅያን ላይ የሚተጀመረው የአየር ጥቃት እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡በጉባኤው የታደሙት አብድረቦ መንሱር ሐዲ የአገራቸው ችግር ለመፍታት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባቀረቡት የድርድር ሃሳብ የሚስማሙ አይመስልም፡፡የሁቲ አማፅያን ይዞታቸውን በመልቀቅ ወደ ሰሜን የመን ካላፈገፈጉ በቀር በጠረጴዛ ዙሪያ ለመቀመጥ ፈቃደኛ አይደለሁም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ግሩም ተ/ሐይማኖት የሁቲ አማፅያኑም ቢሆኑ ለድርድር ዝግጁ አይደሉም ሲል ይናገራል፡፡

«የድርድር ሃሳቡን የሁቲዎቹ መሪ አሁንም ደጋግመው በመግለጽ ላይ ናቸው። ምንም እንኳ ካቅማቸው በላይ ቢሆንም የአየር ድብደባውን ለማስቆም እየሞከሩ ነው ያሉት። እስካሁን ሁለት ጀት እንደመቱ እየተናገሩ ነው ያሉት።»

የሊቢያ ውጥንቅጥ እና የሶርያ ጉዳይ ዛሬም መልስ አላገኘም፡፡የኢራቅ መንግስት ከተፈታ ከራረመ፡፡የየመን አለመረጋጋት ለአልቃዒዳ ሰርግና ምላሽ ለአሜሪካና ምዕራባውያን ትልቅ የራስ ምታት ሊሆን እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ለመላው የየመን መታመስ ስጋትነቱ ለየመናውያን ብቻ አልሆነም። ሳዑዲ አረቢያ እና የቀጣናው አገራትን ብሎም የአፍሪቃ ቀንድ ልታምስ የምትችልበት እድል አለ። ሳዑዲ አረቢያ ላይ ያለው ጋዜጠኛው ነብዩ ሲራከም ይሁን የሰንዓው ግሩም ተ/ሐይማኖት የየመን ጉዳይ አሳሳቢ እንደሆነ ያምናሉ፡፡

የየመን ውጥንቅጥ እጅጉን የተወሳሰበ ይመስላል።፡፡ እንደ ሶማሊያ፡፡ ሳዑዲ አረቢያ እና የአረብ ሊግ አጋሮቿ የፕሬዝዳንት አብድረቦ መንሱር ሐዲ እና መንግስታቸውን ወደ ስልጣናቸው እንመልሳለን ቢሉም ዋንኛ ትኩረታቸው የራሳቸውን ደህንነት ማስጠበቅ እና ተቀናቃኛቸውን ኢራንን አንገት ማስደፋት ይመስላል። ፕሬዝዳንት አብድረቦ መንሱር ሐዲ ወደ መንበረ ስልጣናቸው ቢመለሱ እንኳ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት የመመስረቱ ጉዳይ እንዲህ ቀላል አይመስልም፡፡

እሸቴ በቀለ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic