የመን ተስፋና ቀቢፀ ተስፋ | ዓለም | DW | 22.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የመን ተስፋና ቀቢፀ ተስፋ

ተስፋ፤ ተማፅኖ፤ ክርክሩ ከጄዤኔቭ ሲንቆረቆር ደኸይቱ ሐገር ካለፈዉ መጋቢት ጀምሮ እንደኖረችበት የሐብታም ጎረቤቶችዋ ቦምብ-ሚሳይል-ካየር፤ የተቀናቃኝ ተፋላሚዎችዋ መድፍ፤ ታንክ፤ የፅንፈኛ ዜጎችዋ ቦምብ ከምድር ያነድዳት ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:39
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
12:39 ደቂቃ

የመን ተስፋና ቀቢፀ ተስፋ

የየመን ፖለቲኞች የሰሞኑ አጭር ታሪክ።የተፋላሚ ሐይላት ተወካዮች ባለፈዉ ሳምንት ሰኞ ወደ ዤኔቭ-ሲዊዘርላንድ መጡ።ሊደራደሩ።የአንድ ሐገር፤ የአንድ ቋንቋ፤ ሐይማኖት ተጋሪዎቹ የአንድ ዘመን ፖለቲከኞች ፊት ለፊት መነጋገር ቀርቶ እንዳቸዉ ከሌላቸዉ ለመተያየት እንኳ ተጠያይፈዉ በየክፍላቸዉ ተሰበሰቡ።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልክተኛ አማካይነት «ሥማበለዉ» ሲሉ እስከ አርብ ቆዩ።ከዚያ፤ እንደለመዱት በባዕዳን እየተገፉ፤እየተደገፉ ተከታዮቻቸዉን ሊያዋጉ፤ የጋራ ሕዝብ፤ ሐገር፤ ሐብታቸዉን ሊያወድሙ ወደየመጡበት ሔዱ።ሳይጀመር ያለቀዉ ድርድር መነሻ፤ የጣልቃ ገብ መንግሥታት ዓላማ ማጣቀሻ፤ የደሐይቱ ሐገር ጥፋት፤የጣልጋ ገብ መንግሥታት ምክንያትን እንቃኛለን።

ካለ፤ ከሆነና፤ ከሚሆነዉ ይልቅ እንዲሆን የሚፈለገዉን መናገር ወይም ማዉራት ለብዙዎች መሠረት የለሽ ፤ ለደፋሮች ዉሸት ሊሆን ይችላል።ለአብዛኛዉ ፖለቲከኛ እና ዲፕሎማት ግን-የፖለቲከኝነት ልኩ፤ዲፕሎማትነት ወጉ ነዉ።ሞሪታኒያዊዉ ዲፕሎማት ኢስማኢል ኡልድ ሼኽ አሕመድ የተለዩ ቢሆኑ ኖሮ ዲፕሎማት ባልሆኑ።በየመን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ልዩ መልዕክተኛ የየመን ተፋላሚ ሐይላት በዤኔቩ ድርድራቸዉ ከሆነ ሥምምነት ላይ እንደሚደርሱ «ተስፋለኝ» ብለዉ ነበር።

«ተስፋ እንዳለኝ መናገር እችላለሁ።ዉሳኔዉ ከባድ እንደሆነ አዉቀዋለሁ።ሁኔታዉን ስንከታተል ነበር።የመንን ሁለቴ ጎብኝቻለሁ።በፊትም አዉቃታለሁ።ተስፈኛ የሆንኩት ግን እንደሚመስለኝ፤ከመጀመሪያዉ ዕለት ጀምሮ እንዳልነዉ መፍትሔዉ አንድ ብቻ ነዉ።ሠላማዊ መፍትሔ።ይሕ ጦርነት የሚቆምበት ብቸኛ መንገድ የመኖች በጠረጴዛ ዙሪያ ሲቀመጡ፤ ተኩስ ለማቆም ሲስማሙ እና ምሰሶዎች በምንላቸዉ ሰወስት ጉዳዮች ላይ ሲወያዩ ነዉ።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ-ፓን ጊ ሙንም እንደ ልዩ መልዕክተኛቸዉ ባይበዛም ተደራዳዎች ቢያንስ ላጭር ጊዜ ተኩስ ለማቆም ይስማማሉ የሚል ተስፋ ነበራቸዉ።ፓን ቁጥብ ተስፋቸዉ ዕዉን እንዲሆን ተፋላሚ ሐይላት ቢያንስ በሙስሊሞቹ ቅዱስ ወር በረመዳን ተኩስ እንዲያቆሙ ተማፅነዋልም።

ዋና ፀፊዉ «ከዓለም ትላልቅ ሐብታም ሐገራት የምትጎራበት ግን ከዓለም ደሐ ሐገራት እንዷ»-ያሏትን የመንን ሠላም ለማድረግ «ልዩ ሐላፊነት» አለብን ብለዉም ነበር።

«መፍትሔ የመፈለግ ልዩ ሐላፊነት አለብን።አስከፊዉ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት እንኳን የመን ከዓለም ሐብታሞች ባንዱ አካባቢ የምትገኝ ግን ከዓለም ድሐ ሐገራት እንዷ ናት።»

ተስፋ፤ ተማፅኖ፤ ክርክሩ ከጄዤኔቭ ሲንቆረቆር ደኸይቱ ሐገር ካለፈዉ መጋቢት ጀምሮ እንደኖረችበት የሐብታም ጎረቤቶችዋ ቦምብ-ሚሳይል-ካየር፤ የተቀናቃኝ ተፋላሚዎችዋ መድፍ፤ ታንክ፤ የፅንፈኛ ዜጎችዋ ቦምብ ከምድር ያነድዳት ነበር።ደሕ ሕዝቧግን የሰነዓዉ ተባባሪ ወኪላችን ግሩም ተክለ ሐይማኖት እንዳለዉ በክሳይ ድቃቂዉ ክምር መሐልም ሆኖ ከዤኔቭ የሚሰማዉን ተስፋ በተስፋ መጠበቁ አልቀረም።

ካለፈዉ መሥከረም ጀምሮ ርዕሰ ከተማ ሠነዓን ጨምሮ አብዛኛዉን የመንን የሚቆጣጠሩት የሁቲ ሚሊሺያ ተወካዮች ለዤኔቩ ድርድር ሲጓዙ ከጀቡቲ እንዳይንቀሳቀሱ ተከልክለዉ ነበር።መልዕክተኞቹ ከጂቡቲ እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱት ያሳፈራቸዉ አዉሮፕላን በግብፅ የዓየር ክልል እንዳይበር የግብፅ መንግሥት በመከልከሉ ነበር።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልመናና በሐያላን መንግሥታት ጥያቄ መልዕክተኞቹ እንዲንቀሳቀሱ ተፈቅዶላቸዉ ዤንቭ የገቡት ድርድሩ ይጀመራል ከተባለበት ባንድ ቀን ዘግይተዉ ነዉ።

ሁቲዎች ድርድሩ ዉጤት እንዲያመጣ ከተፈለገ መደራደር ያለብን የመንን ከምትደበድብና ከምታስደበድበዉ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር እንጂ ሳዑዲ አረቢያ ከተሰደደዉ፤ በሳዑዲ አረቢያ ከሚደገፈዉ ከብድ ረቦ መንሱር ሐዲ መንግሥት ጋር መደራደሩ ትርጉም የለዉም ባዮች ነበሩ።የሠማቸዉ እንጂ የተቀበላቸዉ የለም።እና የሁቲ፤ ከሁቲዎች ጋር ያበሩት የቀድሞዉ የየመን ፕሬዝደንት የዓሊ አብደላ ሳላሕ ተወካዮች፤ የስደተኛዉ መንግሥት ተጠሪዎችም በየፊናቸዉ የሚሉትን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ነገሩ፤ ልዩ መልዕክተኛዉ ካንዱ የሰሙትን ለሌላዉ አጋሩ፤ አርብ፤ ተበተኑ።

ለመተያየት እንኳን ላይፈቅዱ፤ የሚሹ የሚፈልጉትን ለዓለም አቀፉ ዲፕሎማት ለመናገር ዤኔቭ ድረስ የመጓዛቸዉ ምክንያት በርግጥ ግራ ነዉ።ልዩ መልዕክተኛ ሼኽ አሕመድ ግን ድርድሩ ሳይጀመር ቢያበቃም የተፋላሚ ሐይላት ተወካዮች ዤኔቭ ደርሰዉ መመለሳቸዉ ራሱ ጥሩ ጅምር ነዉ ባይ ናቸዉ።በየመን ሠላም ለማዉረድ የእስካሁን ጥረታቸዉን በእጥፍ እንደሚጨምሩም ዲፕሎማቱ አስታዉቀዋል።

እስከመቼ ? አይታወቅም።የሚታወቀዉ የመን ዛሬም መጥፋት፤ መዉደሟ፤ የሕዝቧ ሥቃይ ሰቆቃ ማየሉ ነዉ።እንደገና ግሩም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቁጥር ለመጥራት ግን አልሰነፈም።ድርጅቱ እንደሚለዉ ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር የመንን መደብደብ ከጀመረበት ካለፈዉ መጋቢት ወዲሕ ከ2800 በላይ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ተሰደዋል።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘገባ መሠረት ከየመን ሕዝብ 80 በመቶዉ ወይም ከ21 ሚሊዮን የሚበልጠዉ አስቸኳይ ሰብዓዊ ርዳታ ያስፈልገዋል።እስካሁን ግን ሟቹ ቀባሪ፤ ቁስለኛዉ መታከሚያ፤ ስደተኛዉ መጠለያ የለዉም።

ለወትሮዉ የመንን እንደ መሥሪያ፤ እንደ መሸጋገሪያ ወይም እንደመጠለያ አድርጎ የተሰደደባት የዉጪ ሐገር ዜጋ ሥቃይ ደግሞ ከሐገሬዉም የከፋ ነዉ።እርግጥ ነዉ አብዛኛዉ የዉጪ ስደተኛ አንድም ወደ ወደየሐገሩ አለያም ወደ ሰወስተኛ ሐገር ሸሽቷል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያንና ኤርትራዉያን ግን አሁንም የመንን ሙጥኝ ማለታቸዉ የየመኖችን ራሳቸዉን አጃኢብ እያሰኘ ነዉ። ነዉ።

ግሩም እንደሚለዉ የሁለቱ ሐገራት ስደተኞች ሲሞቱ ቀባሪ አይደለም ቆጣሪም የላቸዉም።ቁስለኛ፤ ሕመምተኛዉ ቀርቶ ጤነኛዉም እሕል ዉሐ አያገኝም።ለሳዑዲ አረቢያና ለተባባሪዎችዋ የአዉሮፕላን ሚሳዬል፤ ለሐዲ ደጋፊና ለሁቲ ሚሊሺያዎች ጥይት፤ለአልቃኢዳ ወይም ለISIS ቦምብና ካራ ለወርሮ በሎች ዱላ፤ ለሁሉም ጥቃት የተጋለጠ ነዉ።በሁሉም ጥቃት ሕይወት አካሉን ያጣል።

የሪያድ፤ የኩዌት፤የዶሐ፤ የማናማ፤ የአቡዳቢ፤ የአማን፤ የራባት ነገሥታት ወይም አሚራት ምርጫ የሚባል ነገር አያዉቁም።የካይሮ ገዢዎች ሥልጣን የያዙት በሕዝብ የተመረጠ መሪ በጠመንጃ አስወግደዉ ነዉ።እነዚሕ ገዢዎች ሱዳንን፤ ሴኔጋልን፤ እና ማሌዢያን አስከትለዉ የመንን ከሚደበድቡት ምክንያቶች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቅሱት በሕዝብ የተመረጠዉን የሐዲ መንግሥት ወደ ሥልጣን ለማዉጣት የሚል ነዉ።

ዩናይትድ ስቴትስ፤ ብሪታንያ፤ ፈረንሳይ፤ ቤልጂግ እና ቱርክ የምርጫ፤ ዴሞክራሲ፤ የፍትሕ እኩልነት ሐገር ብቻ አይደሉም።የዲሞክራሲ ተቆርቋሪዎችም ጭምር እንጂ።የየራሳቸዉን ሕዝብ ነፃነት የሚረግጡ፤ የመንን የሚደበድቡ አምባገነን ነገሥታትን ግን በግልፅ ይረዳሉ፤ በገፍ ያስታጥቃሉ።

ሁለተኛዉ ምክንያት ኢራኖች የሚደግፏቸዉ የዛይዲ ሐራጥቃ ሙስሊሞች የመንን መቆጣጠር የለባቸዉም የሚል ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ቬትናምን በምትወጋበት በ1970ዎቹ፤ ጦርነቱ ያሰለቸዉ አሜሪካዊ ጦሩ እዚያ ድረስ ሔዶ፤ ለዚያን ያክል ዓመታት የሚዋጋበትን ምክንያት ሲጠይቅ የሚሰጠዉ መልስ «ኮሚንስቶችን ለማጥፋት የሚል» ነበር።መልሱም እንደ ጦርነቱ የሰለቸዉ፤ «ኮሚንስትን ለማጥፋት ከሆነ ለምን አንድነቱን ሞስኮን አንወርርም» ብሎ መለሰ አሉ-ያዩ የሰሙ።ለየመኑ ድብደባ ኢራንን ከሆነች ምክንያቷ ሰነአላይ የሚያናፍሩት ለምን ቴሕራንን «ሞከር-ፈተሽ አያረጓትም»---እንበል ይሆን ብቻ ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች