የመን: ሰሞናዊ እዉነቷ፥ ታሪኳና ጉዞዋ | ዓለም | DW | 06.06.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የመን: ሰሞናዊ እዉነቷ፥ ታሪኳና ጉዞዋ

የንጉሱ አገዛዝ ያማረረዉ የያኔዉ የመናዊ ንጉስን «ሰይጣን» ሲልም፥ «ገዳይ» ብሎ ሲያወግዝም በድብቅ ነበር።ሳሌሕን ሕዝባቸዉ ካለፈዉ ጥር ጀምሮ ባደባባይ ነዉ ያወገዛቸዉ።አምባገን እያለ። ኢማም አሕመድ በጉምጉምታ ገዳይ በተባሉ በሐምሳ-ስድስተኛዉ አመት ደግሞ ተራዉ የሳሌሕ ሆነ።

default

ፌስታ

06 06 11

ሮሞች የአረቢያ አስደሳች ወይም ዕድል ብለዋት ነበር።አረቢያን ፌሊክስ።አረቦች ግን የአረቢያ ቀኝ አሏት።ደቡብ።የሚን።መልከዓ ምድሯ፥ ለምነቷ ሳቢ፥ ማራኪ ሆኖላት ወይም ሆኖባት ሮሞች ሲቋምጥሏት ማኢንዮኖች ማርከዋታል፥ ኢትዮጵያዉያን ሲደክሙባት-ፋርሶች ተረክቡዋት።ቱርኮች ሲሰናበቱ እንግሊዝች ገብተዉባታል።-የመን።በ1970ዎቹ የሶቭየቶች የአረቢያ ኩባ፥ የግብፆች ቬትናም፥ የሳዑዲዎች ፓናማ ተብላ ነበር።ዘንድሮ ሕዝቧ እንደ ቱኒዚያ ግብፅ ብጤዎቹ ሲያምፅ የአሜሪካኖች አገም-ጠቀም መርሕ ማዕከል ሆነች።ሳዑዲዎች ሽማግሌም-ሐኪምም ሆኑላት ወይም ሆኑባት።የመን። ሰሞናዊ እዉነቷ መነሿ፥ ታሪኳ ማጣቃሻ የወደፊት ጉዞዋ ማጠያያቂያችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።


በ1962 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ልዑል ሙሐመድ አል-ባድር ዘዉድ ሊደፉ ሲደግሱ ከስልጣን ተወገዱ።መገደላቸዉ ከታዒዝ ሲወራ-ወደ ሳዑዲ አረቢያ መሰደዳቸዉ ከሪያድ ተረጋገጠ።ልዑሉ ከዙፋናቸዉ ለመመለስ ብዙ ተዋጉ ግን-አልተመለሱም።ዘንድሮ በአርባ-ዘጠነኛዉ ዓመቱ ፕሬዝዳት ዓሊ አብደላ ሳሌሕ ያቆሰላቸዉ ቦምብ ብዙም እንዳልጎዳቸዉ ለማረጋገጥ ለሕዝብ እንደሚታዩ፥ ንግግር እንደሚያደርጉም ሠነዓ ላይ ሲነገር-ከጂዳ ሳዑዲ መግባታቸዉ ተሰማ።

የሳሌሕ ጉዞ አለማ አንድ የመንግሥታቸዉ ቃል አቀባይ እንዳስታወቁት «ሕክምና» እንጂ እንደ ልዑል አል-ባድር ሥደት አይደለም።

Jemen Präsident Ali Abdullah Saleh NO FLASH

ሳሌሕ«ፕሬዝዳንቱ ጤነኛ ናቸዉ።ለምርመራ ሳዑዲ አረቢያ ናቸዉ።ሳሌሕ በተቻለ መጠን በፍጥነት ወደ ሐገራቸዉ ይመለሳሉ።ሕገ-መንግሥታዊ ተቋማቱ ሥራቸዉን ይቀጥላሉ።ጦር ሐይሉ ተረጋግቶ ምግባሩን እያከናወነ ነዉ።መንግሥት ፈርሷል የሚለዉ የተቃዋሚዎች ሕልም ነዉ።»

የፕሬዝዳንት ዓሊ አብደላ ሳሌሕን የሰላሳ-ሁለት ዘመን አገዛዝ በሕዝባዊ አመፅ ለማስወገድ ካለፈዉ ጥር ማብቂያ ጀምሮ አደባባይ የሚወጣዉ ሕዝብ ግን የቃል አቀባዩን መግለጫ አልተቀበለዉም። ትናንት ዕሁድ ርዕሠ-ከተማ ሰነዓ እና ከሐገሪቱ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ታዒዝ አደባባይ የወጣዉ ሕዝብ እንደ እስከ ዕሁዱ «ሳሌሕ ከሥልጣን ይዉረዱ» አልነበረም መፈክር ጥያቄዉ።
በሳሌሕ መሔድ ፌስታ እንጂ።«ሕዝቡ ሥርዓቱን አስወገደ።» ይላሉ-እነሱ።እሳቸዉ በደስታ አለቀሱ።

እኚሕኛዉ እንደሚሉት ደግሞ ሳሌሕ የመዉጪያ እንጂ የመግቢያ ቪዛ አልተፈቀደላቸዉም።«እኛ አብዮተኞች የሳሌሕ ጉዞ ተገቢ ነዉ ብለን እናስባለን።ቪዛቸዉ ግን የመዉጪያ እንጂ የመመለሻ አይደለም።»

ገዢዎችዋ ቃል-እየገቡ፥ ለመመለስ እየተዋጉ፥ ሲያዋጉባት ግን እንደወጡ ሲቀሩባት ለዚያች ጥንታዊት፥ ሥልታዊት፥ ዉብ አረባዊት ሐገር ያሁኑ የመጀመሪያዋ አይደለም።የመንግሥትነት ቅርፅ በያዘ-አስተዳደር መገዛት ከጀመረበችበት ከአስራ-ሁለተኛዉ ዓመተ-ዓለም ጀምሮ ማኢንዮች፥ ሳባዎች፥ሐድራመዉቶች፥ ቃጠቦች፥አዉሳዎች፥ ሒምራይቶች፥ ኢትዮጵያዎች፥ ፋርሶች፥ የሙስሊም ኸሊፎች በየዘመናቸዉ ገነዉ፥ ገዝተዉ ቀዳሚዎቻቸዉን አስገብረዉ ለተከታዮቻቸዉ ገብረዉባታል።

«የዓለም» የተሰኘዉ የመጀመሪያዉ የሐያላን ቅኝ ገዢዎች ጦርነት ፍፃሜ በተለያየ መልክ፥ቅርፅና ሥፋት የተለያዩ የዉጪና የዉስጥ ገዢዎች ሲፈራረቁበት ዘመነ-ዘመናት ላስቆጠረችዉ ሐገር የአንድነቷ ፍፃሜ፥ የአዲስ ፖለቲካዋ መሠረትም ነዉ።የእስከዚያ ዘመኑ-የዓለም ሐያል ቱርኮች- ተንኮታኩተዉ እንግሊዞች እንደ ዘመኑ-ዘመናይ አደንን ሲቆጣጠሩ ሰሜን የመን በ-መተወኪሊት ሥርወ-መንግሥት ትገዛ ገባች።1918።

በ1948 የመተወኪሊቱ ሥር-ወመንግሥትን ዙፋን የወረሱት ኢማም አሕመድ ቢንያሕያ ጠላቶቻቸዉን በሥልጣን፥ በንዋይ ወይም በጎሳ መሪዎች ምልጃ እያባበሉ፥ ከደጋፊዎቻቸዉ መነጠል፥መነጠላቸዉን ሲረጋገጡ አንገታቸዉን እያስቀሉ፥አለያም ወሕኒ እያስወረወሩ ያለተቀናቃኝ መግዛቱ «ሰይጣኑ አሕመድ» ከሚል ሐሜት ባለፍ ለአስራ-አራት አመታት ያለተቀናቃኝ መግዛቱ አልገደዳቸዉም።

በ1955 ኮሎኔል አሕመድ ጣላያ የመሯቸዉ ወታደሮች ንጉሱን ለማስወገድ የንጉሱን ታማኞች ደምስሰዉ የታዒዝን ቤተ-መንግሥት ከበዉት ነበር።ንጉሱ ሐይላቸዉ መዳከሙን እንዳወቁ ከኮሎኔሉ ጋር ይደራደሩ ገቡ።ዙፋናቸዉን ለታናሽ ወንድማቸዉና ለዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ለ አሚር ሰይፍ አል ኢስላም አብደላሕ እንዲያስረክቡ ኮሎኔሉ ያቀረቡትን ቅድመ-ግዴታም ተቀበሉ።

ዙፋን ለመዉረስ የጓጉት ሰይፍ አል-ኢስላም ሚንስትሮችን እየሾሙ ቀን ሲያሰሉ ዙፋን ለማስረከብ ቃል የገቡት ኢማም አሕመድ ቤተ-መንግሥታቸዉን ለከቡቡት ወታደሮች ገንዘብ ያድሉ ገቡ።ዙፋን የሚያስረክቡበት ቀን ሲደርስ ቤተ-መንግሥቱን ከበዉ ከነበሩት ስድስት መቶ ወታደሮች መካካል የቀሩት አርባ ብቻ ነበሩ።«መለኛዉ» ንጉስ ዙፋን ተረካቢዉን አስገድለዉ፥ የኮሎኔሉን እጅግ-እግር አስቆርጠዉ በዙፋናቸዉ ፀኑ።

እስከዚያ ጊዜ ድረስ የየመን ሕዝብ በጣሙን የጎሳ መሪዎችና የጦር መኮንኖች «ሸይጧን» ይሏቸዉ የነበሩትን ንጉሱ «ገዳይ» እያሉ ያጉተመትሙ ገቡ።የያኔዉ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ዓሊ አብደላ ሳሌሕ አጉረምራሚዉን ጦር ሠራዊት ለመቀላቀል ማመልከቻ ያረቁ ነበር።የንጉሱ አገዛዝ ያማረረዉ የያኔዉ የመናዊ ንጉስን «ሰይጣን» ሲልም፥ «ገዳይ» ብሎ ሲያወግዝም በድብቅ ነበር።ሳሌሕን ሕዝባቸዉ ካለፈዉ ጥር ጀምሮ ባደባባይ ነዉ ያወገዛቸዉ።አምባገን እያለ። ኢማም አሕመድ በጉምጉምታ ገዳይ በተባሉ በሐምሳ-ስድስተኛዉ አመት ደግሞ ተራዉ የሳሌሕ ሆነ።

«ፕሬዝዳንቱ ገዳይ ናቸዉ።ታኢዝ ከተማ ዉስጥ ሰዉ ጨፍጭፈዋል።ይሕ ለዚያ ቅጣታቸዉ ነዉ። በመሔዳቸዉ ተደስቻለሁ።ለሐገሪቱ ይጠቅማል።»

ድሮ፣-ሕይወት፥አካለ፥ ደም፥ ገንዘብ ሕይወት እያጠፉ ዙፋናቸዉን ያስከበሩት ኢማም አሕመድ ጭካኔያቸዉ ያስመረረዉ፥ ከሁሉም በላይ ኮሎኔል ገማል አብድናስር የመሯቸዉ የግብፅ የጦር መኮንኖች ድፍረት፥ ጀግንነት፥ ብሔረተኝነት ልቡን ያሸፈተዉን የጦር መኮንን ልብ ለመስለብ ዘዴ አላጡም።እንደ ንጉስ ስዑዲ አረቢያና ዮርዳኖስን ከመሳሰሉ ዘዉዳዊ ገዢዎች ጋር ያላቸዉን ወዳጅነት እንደጠበቁ፥ እንደ ሪፐብሊካን የግብፅና የሶሪያን ሕብረት ለመቀላቀል ፍላጎት እንዳላቸዉ ደማስቆ ድረስ በላኳቸዉ አልጋወራሽ ልጃቸዉን በኩል አስታወቁ።

የየመንን ባንዲራም ግብፅና ሶሪያ «የተባበሩት አረብ ሪፐብሊክ» ያሉትን ሕብረት የሚወክለዉን ቀለምና መልክ እንዲይዝ አደረጉ።ቀይ፥ ነጭና ጥቁር።1958።ኢማም አሕመድ የንጉስ ፈይሰል ቢን-አብዱል አዚዝ ቢን ሳዑድን ግልምጫ፥ እና የናስርን ቁጣ እኩል ለማስተናገድ እንደ ተዉተረተሩ ሞቱ።ልጃቸዉ አልጋ ወራሽ ሙሐመድ ዓል-ባድር ገና ዘዉድ ሳይደፉ ተሽቀዳድመዉ አፍቃሬ ናስሩን የጦር መኮንን ኮሎኔል አብዱላሕ አስ-ሳላልን የክብር ዘበኛቸዉ ጦር አዛዥ አድርገዉ ሲሾሙ ካይሮ፥ ባግዳድ፥ ደማስቆ የሆነዉ ታኢዝ እንዳይደገም ዘዴ ያሉት ነበር።

ግን አልሆነም።የወለፊንድ ባርቆ ኮሎኔል አስ-ሳላል አልጋወራሹን አስወግደዉ ናስር የሚፈልጉትን የመን ላይ ፈፀሙ።ልዑሉ ሳዑዲ አረቢያ በስደት ኢማምነትን ጭነዉ በሳዑዲና በዮርዳኖስ ድጋፍ ወታደራዊዉን መንግሥት ይወጉ ገቡ።ግብፅ በፋንታዋ ወታደራዊዉን መግሥት ለመርዳት ሰባ ሺሕ ጦሯን የመን ላይ ዘረገፈችዉ።የመጀመሪያዉ የአረብ-የእርስ በርስ ጦርነት ሰሜን የመንን ያንቀረቅባት ያዘ።

አንድ መቶ ሺሕ የመናዊ፥ በአስር ሺሕ የሚቆጠር ሳዑአረቢያዊ፥ ሃያ-ስድስት ሺሕ ግብፃዊ አለቀ። ሳዑዲ አረቢያ አል-በድርን ወደ ሥልጣን መመለስ ቢያቅታትም አሜሪካኖች ፓናማ ላይ በተደጋጋሚ እንደሚያደርጉት ናስርን የሚደግፉ የጦር መኮንኖች ከየመን አስወግዳ ግብፅን የሚቃወሙትን ሲቢል አብዱራሕማን ያሕያ አል-ኢርያኒን አሾሞች።አሜሪካኖች ቬትናም የቀመሱትን ሽንፈት ግብፆች የመን ላይ ተጎነጩት።1967።

አል-ኢርያኒ በየመን አረብ ሪፐብሊክ የእስካሁን ታሪክ የመጀመሪያዉም የመጨረሻዉም ሲቢል መሪ ናቸዉ።የጎሳ መሪዎች ጫና፥ የዉጪ ሐይላት መጓተት ግራ ቀኝ ለሚያላጋት ሐገር፥ የምክር ቤት ምርጫን፥ ሕገ-መንግሥትን ያስተዋወቁ፥ ምጣኔ ሐብቷን ያሳደጉ፥ ከደቡብ የመኖች ጋር ለመዋሐድ ድርድር የጀመሩ መሪ ነበሩ።ወደ ግብፆች የሚያደሉት ኮሎኔል ኢብራሒም አል-ሐምዲ ከሥልጣን አስወገዷቸዉ።1974።

ኮሎኔል ሐምዲ ወደ ካይሮ ማንጋጠጣቸዉ እና ለሶቬት ሕብረት ካደሩት ከደቡብ የመን ኮሚንስቶች ጋር በዳግም ዉሕደት ሰበብ መቀራረባቸዉ በዋሽንግተኞች የሚደገፉት ሪያዶች እንደ ዋዛ የሚያዩት ነገር አልነበረም።ሥልጣን በያዙ በሰወስተኛዉ ዓመት ከወንድማቸዉ ጋር ተገደሉ።ያኔ የወጡ መረጃዎች እንዳረገጡት ገዳዮች የሳዑዲ አረቢያ የስለላ ድርጅት ያዘመታቸዉ፥ በሳዑዲ አረቢያዎች የሚደገፈዉ የአል-አሕመር ጎሳ አባላት ናቸዉ።

ሐምዲን የተኩት ኮሎኔል አሕመድ ቢን ሁሴይን አል-ጋሺሚ የፕሬዝዳንትነቱን ሥልጣን በያዙ በስምንተኛዉ ወር ተገደሉ።በስምት ወር ዘመነ-ሥልጣናቸዉ ካከናወኗቸዉ ተግባራት አንዱ አስር-አለቃ ዓሊ አብደላ ሳሌሕን ለአዉራጃ ገዢነት መሾማቸዉ፥ ለዛሬዋ የመን የበጎ ይሁን የመጥፎ ቅርስ ዉርስ ነዉ የሆነዉ።አሟሟታቸዉ ግን አነጋጋሪ፥ ግራ አጋቢም ነበር።የያኔዉ የደቡብ የመን መሪ ሳሊም ዓሊ ሩባይ ልዩ መልዕክተኛቸዉን ወደ ሰነዓ ይልካሉ።ፕሬዝዳት ጋሺም መልዕክተኛዉን እያነጋገሩ አንድ የሰነድ ቦርሳ (ብሪፍ ኬዝ) ይከፍታሉ።ቦምብ የተጠመደበት ነበር።ፈነዳ።እሳቸዉም መልዕክተኛዉም ሞቱ።

በሰወስተኛዉ ቀን የደቡብ የመን መሪ አሊ ሩቢ በመፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች ተይዘዉ ተረሸኑ።1978።የመን ሰሜን-ደቡብ ላይ ቆሞ «አጃዒብ» ሲል፥ ዓሊ አብደላ ሳሌሕ በጎሳ መሪዎች ድጋፍ አራት ሰዎችን የሚያስተናብረዉ የርዕሠ-ብሔር ኮሚቴ መሪ ሆኑ።የሶቬቶች ጎራ ሲደረመስ ደቡብ የመንንም ጠቅልለዉ የተዋሐደችዉ የመን የመጀመሪያ መሪ ሆኑ።

የየመን ሕዝብ የሳሌሕን አገዛዝ በመቃወም ሲያምፅ አሜሪካ መራሹ ዓለም አመፁን ከቅርብ ርቀት ከመከታተል ባለፍ ሳሌሕን እንደ ቃዛፊ ወይም እንደ አል-በሽር አልጨከነባቸዉም ነበር።አመፁ እየናረ፥ የሳሌሕ ታማኞች እርምጃ እየመረረ ሲመጣ ግን ልክ ቤን ዓሊ፥ ሙባረክ ላይ እንዳደረጉት ሁሉ ስዑዲዎች በሚመሩት በፋርስ ባሕረ-ሠላጤ ሐገራት ምክር ቤት በኩል ድርድር-ሽምግልና ይሉ ገቡ።ሳሌሕ ግን የድርድሩን ሐሳብ እንቢኝ ሲሉ።

ከእንቢታዉ በሕዋላ ከድሮ ጀምሮ በሳዑዲ አረቢያ ነገስታት የሚደገፈዉ የአል-አሕመር ጎሳ አመፀኛዉን ሕዝብ ተቀላቀለ። የሳሌሕ ታማኞች የጎሳዉን መሪ ሼኽ ሳዲቅ አል-አሕመርን ያወግዙ፥ ተከታዮቻቸዉን ያጠቁ ያዙ።ለአብዮተኛዉ ግን የድል ዋዜማ አይነት ነበር።

«ሼሕ ሳዲቅ አል-አሕመር ጥቃት የተፈፀመባቸዉ አብዮቱን ስለደገፉ ነዉ።ሥርዓቱ በሚወስደዉ የሐይል እርምጃ ተቃዋሚዎቹን ለማሸማቀቅ እየሞከረ ነዉ።ከደባባይ ሊያባርረን ነዉ።እኛ ግን ከመቼዉም ይበልጥ ተጠናክረናል።ቆርጠናልም።

Jemen Demo

ሰልፈኛዉ

ኮሎኔል ሐምዲን በ1977 የገደሉት በስዑዲ አረቢያዎች የሚደገፈዉ የአል-አሕመር ጎሳ አባላት ናቸዉ።ባለፈዉ አርብ የዓሊ አብደላሕ ሳላሕ ቤተ-መንግሥትን በቦምብ የደበደቡት፥ፕሬዝዳንቱን ያቆሰለቱም የዚሁ በሳዑዲ ነገስታት ይደገፋል የሚባል ጎሳ ታጣቂዎች መሆናቸዉ አላጠራጠረም።ሳሌሕ የሚታከሙትም ስዑዲ አረቢያ ነዉ።ይመለሱ ይሆን?።በ1962 ልዑል አል-ባድር ሳዑዲ መግባታቸዉ ለየመን ኋላ ለአረብ የርስ በርስ ጦርነት ዋናዉ መንስኤ ነበር።የሳሌሕ ጎዞስ?።ብቻ ያቺ ሐገር ኦሞች እንዳወደሳት-አረቦች እንዳሞገሷት አይደለችም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ
Audios and videos on the topic