የመን፤ ማብቂያ የለሹ ጦርነት | ዓለም | DW | 30.03.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የመን፤ ማብቂያ የለሹ ጦርነት

ሐብሺና ብዙ ጎረቤቶቹ አካላቸዉ ጎድሎ፣ሕሊናቸዉ ነፍሮም ከሰመመናቸዉ ነቁ።ብዙ ዉዶቻቸዉን ግን  ዳግም ማየት አልቻሉም።የሐብሺ የልብ ስብራት  ዘንድሮ በአምስተኛ ዓመቱም አል ጠገገም።የሶስት ልጆቹን ፎቶ ግራፍ እያገለበጠ ይተከዛል፤ ያነባል፤ ሳግ-እሕሁ መለስ ሲልለት ደግሞ ስማቸዉን ይጠራል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:44

5 ዓመት ጦርነት ዓላማ፣ግብና ዉጤት የለሽ ጦርነት

የመኖች ቀልደኞች ናቸዉ።ዓሊ አል- ቃሲም የመናዊ ነዉ።ዓለም በኮሮና ተሕዋሲ ፈጣን ስርጭትና በገዳዩ ኮቪድ 19 አደገኛነት መሥጋት-መጨነቁን እያነሳ ሲጥል በቀደም «ኮሮና የመን ሊገባ? ምን ሊሰራ?»  ጠየቀ አሉ-ዓሊ፣ የሰሙት፤ መለሰም፤ እሱዉ ለሱዉ ጥያቄ «እኛ እንደሁ የለን፣ አልቀናል።» የመኖች በድንበር፣ ቋንቋ፣ እምነት ዘር ተጋሪዎቻቸዉ ግን የነዳጅ ዘይት ሐብት ባናወዛቸዉ ቱጃሮች ቦምብ-ሚሳዬል ማለቅ፣ ስልታዊቱ፤ ጥንታዊቱ፤ የገነት ተምሳሌይቱ ሐገራቸዉ መዉደም ከጀመረች ባለፈዉ  ዐርብ 5 ዓመት ደፈኑ።ኮሮና የሚያስጨንቀዉን ዓለም ረስታ፣ በዓለምም ተርስታ ዛሬም በእልቂት፣ ጥፋት ወድመቷ ጎዳና ለስድስተኛ ዓመት ታዘግማለች። ላፍታ እንዘክራት።
 የሪያድ፣ የአቡዳቢ፣የማናማ፤ የዶሐ (ኋላ ቢተዉትም) ነገስታት፣ የካይሮና ካርቱም አምባገነኞች፣ የቴሕራን ጠላቶች፣የዋሽግተን ታዛዦች መሆናቸዉን ለማስረገጥ፤ ከሁሉም በላይ በገንዘብ ክምር የደነደነ ክብር ዝናቸዉ፣ በዚያች ደሐ ሐገር ትንሽ  ሐራጥቃ እንደማይደፈር ለማረጋገጥ ከሕዳር 2014 ጀምሮ እንደዛቱት፣ የዚያን ቀን ጀመሩት።መጋቢት 26 2015 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)።ሰነዓ።አሜሪካ ሰራሾቹ የሳዑዲ አረቢያ የጦር ጄቶች አሜሪካ ሰራሹን ቦምብ-ሚሳዬል ሰነዓ አዉሮፕላን ማረፊያ አጠገብ ዘረገፉት።የያሲር አል ሐብሺ ዉዶች አለቁ፣ ሐብት ንብረቱ ወደመ፣ የሆነዉን ያወቀዉ ግን ዘግይቶ ነዉ።
«እራሴን እንደሳትኩ ሆስፒታል ደረስኩ።እንደተመታሁ ያወቅሁት በሶስተኛዉ ቀን ስነቃ  ነዉ።ጭንቅላቴ ላይ ነዉ የተመታሁት፣

ወገቤ፤ በተለይም ሰረሰሬ ላይም ቆስያለሁ።»
ሐብሺና ብዙ ጎረቤቶቹ አካላቸዉ ጎድሎ፣ሕሊናቸዉ ነፍሮም ከሰመመናቸዉ ነቁ።ብዙ ዉዶቻቸዉን ግን  ዳግም ማየት አልቻሉም።የሐብሺ የልብ ስብራት  ዘንድሮ በአምስተኛ ዓመቱም አል ጠገገም።የሶስት ልጆቹን ፎቶ ግራፍ እያገለበጠ ይተከዛል፤ ያነባል፤ ሳግ-እሕሁ መለስ ሲልለት ደግሞ ስማቸዉን ይጠራል።
                                  
«መጋቢት 26,2015 አዉሮፕላን ማረፊያዉን ለምምታት ያለመ የተባለዉ የአዉሮፕላን ድብደባ የእኔንና የጎረቤቶችን ቤቶች ነዉ ያወደመዉ።3ቱም ልጆቼ ተገደዋል።አምር፤ አላዕ እና አይሻ።አምር 18 ዓመቱ ነበር።አላዕ 14፣ ሴቷ ልጄ ደግሞ 11 ዓመት ነበረች።»
የዩናይትድ ስቴትስ ምርጥ ተቃጊ ጄቶች፤ዘመናይ ሚሳዬል፣ ቦምቦችን ለመታጠቅ ለአረብ ቅምጥሎች በርግጥ የሚገድ አይደለም።በቢሊዮነ-ቢሊዮናት የሚቆጠር ዶላር የከሰከሱበትን ጦር መሳሪያ፣የሚያስተኩሱበትን ኢላማ በትክክል የሚያዉቅ ወታደር በቅጡ አለማሰልጠናቸዉ እንጂ ድንቁ።
በ1968 ማብቂያ  የያኔዉ የቱኒዚያ ፕሬዝደንት ሐቢብ ቡርጊባ የግብፁን ዝነኛ ብሔረተኛ መሪ ገማል አብድናስርን ለማነጋገር ካይሮ የገቡት ግብፅ  በየመኑም ፣በስድስት ቀኑም ጦርቶች ከደረሰባት ከፍተኛ ኪሳራ እንድታንሰራራ ናስር በሚጣጣሩበት ወቅት ነበር።
ናስር ለእንግዳቸዉ

የአሜሪካኖችንና የእስራኤሎችን አንድነት፣ የአረቦችን የጋራ ችግር፤ ችግሩን ለማስወገድ በጋራ የመቆሙን አስፈላጊነት በሚተነትኑበት መሐል  ቡርጊባ ያቋርጧቸዉና «እንዲያዉ አይገርምም አሏቸዉ» ጋዜጠኛ መሐመድ ሐይከል እንደፃፈዉ።
«ምኑ?» ጠየቁ ናስር።
«እኔ አጭር ሆኜ ስፈጠር እርስዎ እንደዚሕ ረጅም መሆንዎ»  ቡርጊባ መለሱ።

ከፍልስጤም እስራኤሎች በመለስ፣ በዘመናችን መካከለኛዉ ምሥራቅን የሚያብጡት የአብዛኞቹ ጦርነቶች ሰበብ-ምክንይቶች የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት፣የመልከዓ-ምድር-ፖለቲካዊ (Geopolitics) ጥቅም፣የሱኒ-ሺዓ ሐራጥቃዎች ጠብ፣የኢራን እና የእስራኤል-አሜሪካ ቁርቁስ ተብለዉ የሚዘረዘሩ ናቸዉ።
የየጦርነቶቹ ምክንያቶችን ሁሉ የሚያሾሩት ግን ከነናስር ዘመን ከብዙ ምዕተ-ዓመታት በፊት እንደነበረዉ ሁሉ ዛሬም የግለሰቦች ክብር፤ በልጦ የመታየት እልሕና ወግ ነዉ።
የየመኑ ጦርነትም የተለየ ታሪክ የለዉም።የአሜሪካ ኢራኖች ቁርቁስ፣የሪያድ-ዛይዲዎች ጠብ ነፀብራቅ መሆኑ በርግጥ አላነጋገረም።በይፋ የተባለዉም ከሞላ ጎደል ይኸዉ ነዉ።
                                            
«የየመን ሕጋዊ መንግሥትን ከዉድቀት ለማዳንና ከዉጪ ሚሊሺያዎች ከሚደርስበት አደጋ ለመከላከል የሚያስፈልገዉን ሁሉ እናደርጋለን።የሚሊሺያ ቡድን ቦልስቲክ ሚሳዬል፣ከባድ የጦር መሳሪያ፤ አየር ኃይልን ሲታጠቁ ወይም ለመታጠቅ መድረሱን እያየን ነዉ።»በዋሽግተን የያኔዉ የሳዑዲ አረቢያ አምባሳደር አብድል አል ጀባር።መጋቢት 26፣ 2015። 
ሪያዶች የወረራዉን ምክንያት፤ ዓላማና ግብ ከዚያዉ ከሪያድ፤ ለሕባቸዉ፤በወረራዉ ለሚጎዳዉ የመናዊ ወይም ለአካባቢያቸዉ ከመግለጥ ይልቅ በአምባሳደራቸዉ በኩል ከዋሽግተን ማስነገራቸዉ፤ «ጠላቶቻቸዉን ለማሳነስ  መሞከራቸዉ ከተነገረዉ ምክንያት ጀርባ ያለዉን ምክንያት ጠቁሟል።
አምባሰደሩ «ሚሊሺያ ቡድን» ያሉት የአንሳሩላሕ  (የሁቲ)፣ «ዓለም አቀፍ» የሚባል ዕዉቅና ተነፈገዉ እንጂ ከሕዳር 2014 ጀምሮ የመንግሥትን መዋቅርን የያዘ ኃይል-ነበር።ዛሬም።
መሐመድ ቢን ሰልማን ያኔ እንደ ምክትል አልጋወራሽ በጣሙን እንደ መከላከያ ሚንስትር ያዘመቱት ጦር በወራት ዉስጥ እኒያን

የዛይዲ ሚሊሺያ መሪዎችን ማንቁርት ፈጥርቆ እንደሚያመጣላቸዉ እርግጠኛ ነበሩ። 
የዚያ ደሐ፣አናሳ ሐራጥቃ ሚሊሺያ መሪ አብዱል ማሊክ ባደርዲን አል-ሁቲ ከእግራቸዉ ስር ተደፍተዉ ማረኝ እያሉ የሚለምኑበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ወጣቱ ልዑል፣የኋላዉ አልጋወራሽ ተስፋ ነበራቸዉ።
እርግጠኛ ለሆኑበት ምኞት፣ለክብር፤ እልሐቸዉ እርካታ «አምባሳደራቸዉ» እንዳሉት ለድል ለሚያስፈልገዉ ነገር ሁሉ፤ ገንዘቡን ከባንክ-ካዝና፤ ነዳጁን ከርጉርጓድ እያዛቁ፣ ለቦምብ፤ሚሳዬል ጥይት-መትረየስ፤ ለአማካሪ-ቅጥረኛ ይበትኑት ያዙ።አንዲት ሳዑዲ አረቢያ ብቻ እስካለፈዉ ዓመት ድረስ ብቻ ከ50 እስከ 60 ቢሊዮን ዶላር አዉጥታለች።
ወደቦችን፤ ትምሕርት ቤቶችን፣ ሐኪም ቤቶችን፤ የመንገደኞች አዉቶብሶችን፤ የቀብር ስፍራዎችን ሳይቀር በቦምብ ሚሳዬል ያጋዩት ያዙ።ዛሬ የዓሊ ቃሲም ምፀት ለዶክተር ኢሳም ጛሊብ አሳሳቢ ክስተት ነዉ።
                                    
«የኮሮና ቫይረስ የመን ዉስጥ ከተሰራጨ ለመላ ሐገሪቱ ታላቅ ዉድመት ነዉ።ምክንያቱም የሕክምና ቁሳቁስ የለም።የሰለጠኑ ሐኪሞችና የጤና ባለሙያዎች የሉም።የጤና ማዕከላትስ የለም- በለይ በገጠር አካባቢዎች።»
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ በጦርነቱና ጦርነቱ ባስከተለዉ በሽታ 185 ሺሕ ሰዉ አልቋል።ከመቶ ሺሕ የሚልቀዉ ሰላማዊ ሰዉ ነዉ።ከወራሪዎቹ ሐገራት ከ5000 በላይ ሰዉ ተገድሏል።3000ሺዉ ወታደር ነዉ።
አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን አማካሪዎቻቸዉ በዉል ያልተገነዘቡት ሪያድ ላይ በዲስ ሥልጣን፤ በጎረምሳነት ትኩሳት የሚንተከተከዉ ለክብር ዝና «የፈለገዉን» የማድረግ እልሕ ከበረሐማዉ ድንበር ማዶ፤

በዚያች የጉጥ ስርጓጉጥ፤ የጉብታ፤ኮረብታ ከተማ ሰነዓም የሚፍለቀለቅ መሆኑን ነዉ።በጦርነት ኖረዉ በጦርነት የሞቱት የአባት እና የታላቅ ወንድማቸዉን ስልጣን የወረሱት አብዱል ማሊክ ባደርዲን አል-ሁቲ ዘመናይ ጦር መሳሪያ፤ ረቂቅ ስለላ፣ ከሁሉም በላይ የኃያላን ሙሉ ድጋፍ የሚንቆረቆርለትን ጦር በደሐ-ፅናት፤በፍፁም ቁርጠኝነት፤ ሞትን በናቀ ጀግንነት እንደመከቱ እነሆ አምስተኛ ዓመታቸዉን አለፉ።
                                            
«እኛ የምንታገለዉ ከአምባገነኖችን  ጋር ነዉ።ደቡብ ላሉ ወንድሞቻችን ጠላቶቻችን እንዳልሆናቸዉ እናረጋግጥላችኋለን።ይልቅዬ ለጋራ ሐገራችን ከናተ ጎን  እንሞትላችኋለን።»
ይላሉ አንዱ ባለስልጣናቸዉ መሐመድ አል ቡሻቲ።
ቀጠር ጦርነቱ ከተጀመረ ከወራት በኋላ በሪያድ-አቡዳቢዎች ተወግዛ ከዘመቻዉ ወጥላች። የጦርነቱ ጊዜ እየተራዘመ፣ የወራሪዎቹ የድል ተስፋ እየከሰመ፣  የሁቲዎች አይበገሬነት እየተረጋገጠ ሲመጣደግሞ  ከሳዑዲ አረቢያ ቀጥሎ በርካታ ጦር ያዘመተችዉ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዉጊያዉን አቁማለች።አዲሱ የሱዳን መንግስትም ወታደሮቹን ወደ ሐገሩ መልሷል ወይም ለመመለስ ቃል ገብቷል።
ሪያዶች ወረራዉን ሲጀምሩ እንደፎከሩት «የኢራን ተላላኪ» የሚሏቸዉን የዛይዲ ሚሊሺዎችን ማንበርከክ እንደማይችሉ በግልፅ አዉቀዉታል።አብድረቦ መንሱር ሐዲን ከሰነዓዉ መንበራቸዉ መመለስ እንደማይችሉም ጠንቅቀዉ ተረድተዉታል።በቤይሩት የካርኔጅ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ጥናት ማዕከል ባልደረባ አሕመድ ናጂ እንደሚሉት ሳዑዲ አረቢያዎች የመጀመሪያ ፍላጎት፣አላማቸዉ እንደማይሳካ ቢረድቱም፣ ጦርነቱን ማቆም ግን አይፈልግም።ምክንያት እልሕ እና ደቡባዊ ድንበራችን «ይደፈራል» የሚል ሥጋት።እና እንደተንታኞች ግምት ጦርነቱ ይቀጥላል።የመንን ኮኮሮና በፊት እንደለመደችዉ ትጠፋለች።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ
                                    


  
        

Audios and videos on the topic