የመንግስት የስራ ፈጠራ እቅድ ሁለት ገፅታዎች | ኤኮኖሚ | DW | 15.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የመንግስት የስራ ፈጠራ እቅድ ሁለት ገፅታዎች

ከ7.3 ቢሊዮን የአለማችን ህዝብ 1.8 ቢሊዮኑ ከ10 እስክ 24 እድሜ ያላቸዉ ወጣቶች መሆናቸዉን የተባባሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ በህዳር 2007 ዓ.ም. ያወጣዉ ዘገባ ያመለክታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:37

ስራ አጥናት ተፅኖ በኢትዮጵያ

የፖሊሲ አዉጭዎች ዉሳኔን መሰረት አድርጎ የወጣቶች አቅም ወይም ጉልበት የየትኛዉም አገር ኢኮኖሚ ጥሩ ወይም አስከፊ አስተዋፅዖ ሊያደርግ እንደሚችል ዘገባዉ ያትታል።
 ከተጠቀሰዉ የወጣቶች ቁጥር ዉስጥም አብዛኛዎቹ በ48 ታዳጊ አገራት እንደሚገኙ ዘገባዉ ጠቅሶ በእነዚህ አገሮች ዉስጥ ያሉት ወጣቶችም አቅማቸዉ በድህነት፣ በአድሎና በመረጃ እጥረት እንደሚሰናከልም ያስረዳል። ይሁን እንጂ ተገቢ በሆነ መንገድ በትምህርታቸዉና ቀጣይ እጣፈንታቸዉ ላይ መዋዕ-ንዋይ ቢደረግ የወጣቶቹ ሃሳብና  ፈጠራዎች መጭዉን ጊዜ ይለዉጣል፣   
ይህ ካልሆነ ግን የወጣቶች የጤና አገልግሎት፣ ትምህርትና ስራ አጥነት አገርን ለዉድቀት ለመዳረግ አቅም እንዳለዉ ያሳስባል።

ከታዳጊዎቹ አገራት ተርታ የምትገኘው ኢትዮጵያም ከእነዚህ ተግዳሮቶች ማምለጥ አልቻለችም። ኢትዮጵያ  ከ100 ሚልዮን በላይ የህዝብ ብዛት እንዳላት መረጃዎች ይጠቁማሉ። የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አቶ ሙላቱ ተሾመ በፓርላማ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር  አገሪቱ በያዘችዉ ህዝብ ብዛት ከአፍርቃ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ጠቅሰው ከህዝቡም ብዛት ዉስጥ «ከግማሽ የማያንሱት በወጣት እድሜ ክልል» ዉስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በአገሪቱ ካሉት የወጣቶች ቁጥር ዉስጥ አብዛኛዉ ገጠራማ አከባቢ እንደሚኖሩና በገጠርም የሚኖሩት «መሬት አልባ» ስለሆኑ «በተወሰኑ መሰረታዊ ምክንያቶች» ወደ ከተማ እየፈለሱ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል። ይህ ወደ ከተማ የመጣዉ የወጣት ጉልበት በጊዜዉ «አስተማማኝ የስራና የገቢ ሁኔታ» ካልተሟላለት በአጋርቱ የታየዉ ተቃዉሞ መደገሙ አይቀሬ ነዉ ይላሉ።

በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተከሰተዉ ተቃዉሞ ወጣቶችን በብዙ ቁጥር እንዳሰለፉ ይነገራል። ለዚህ የፖለቲካ አለመረጋጋት የኢትዮጵያ መንግስት «እድገቱ በራሱ የፈጠራቸዉ አዳዲስ ፍላጎቶች እና አስቀድሞ በወጉ ያልተቀረፉ ችግሮች ተዳምረዉ አሁንም የወጣቶቹን ፍላጎት በሚፈለገዉ ደረጃ ማርካት አልተቻለም» የሚል አቋም ይዟል።

መቀመጫዉን ሎንዶን ያደረገዉ የብሪታንያዉ አጥኚ ተቋም ቻተም ሃዉስም የአገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የወጣቱን ጥም ማርካት እንዳልቻለ ይተቻል። በተቋሙ አጥኝ የሆኑት ጄሰን ሞስሊ በኢትዮጵያ በየዓመቱ 600,000 ወጣቶች ስራ ፈላጊዉን ማሕበረሰብ እንደሚቀላቀሉ በፅሁፋቸዉ ጠቅሰዋል። መንግስት ባለፉት አስር ዓመታት ሐገሪቱ ሥላስመዘገበችዉ የኢኮኖሚ ዕድገት በሰፊዉ የሚናገረዉ በተጨባጭ ካለዉ የስራ እድል እዉነታ ጋር አለመጣጣሙ ለወጣቱ ትዉልድ ብዥታ መፍጠሩንም አጥኚዉ አብራርተዉ፤ ይሕም በወጣቱ ዘንድ ቅሬታን ኋላም ቁጣን ማስከተሉን ገልፀዋል።

ለዚህ ቁጣ መልስ ለመስጠት የኢትዮጵያ መንግስት  10 ቢሊየን ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ማዘጋጀቱን ገልጧል። ባለፈዉ ሳምንት «የኢትዮጵያ ወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ የማቋቋሚያ አዋጅ» ህግ ሆኖ ጸድቋል።

እቅዱ  በቅርቡ የተፈጠረዉን «ግርግር» ለማብረድ መንግስት የተዘጋጀ ነው የሚል ትችት ገጥሞታል። ይህ መንግስት የሚከተለዉ የልማት ርዕዮተ-አለም ነጥሎ ማየት ይከብዳል ሲሉ በሚንስትር ማዕረግ የመንግሥት የኮሙኒኬሼን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ብዙ ቁጥር ያላቸዉ ተማሪዎች መንግስት እያስተማርኩ ነዉ፣ ግን የስራ እድል በተፈለገዉ ደረጃ አልተፈጠረም የሚለዉን የዶክተር ነገሪ አቋም የኦሮሞ ፌዴራልስት ኮንግሬስ ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ ሙላቱ ጋማቹ ይጋሩታል። ይሁን እንጂ መንግስት የያዘዉ የትምህርት ፖሊስ ለኢኮኖሚዉ እድገት አስተዋፅዖ እያደረገ እንዳልሆነና ከስራ ፈጠራ ይልቅ መንግስት «በፖለቲካ ፈጠራ» ተጠምደዋል።

መንግስት 10 ብሊዮን ብር መድቦ ወጣቶችን ስራ ለማስያዝ ደፋ ቀና እያልኩ ነዉ የሚለዉን ለመታዘብና ወጣቶችን ለማነገር ከአዲስ አበባ በአራቱም አቅጣጫዎች፣ ማለትም በአዳማ፣ በአምቦ፣ በሱሉልታና በሰበታ መሰመሮች ተንቀሳቅሼ ነበር።

የፋብሪካዎች መናኸሪያ እየሆነች መምጣቷ የሚነገርላት የሰበታ ከተማ ወደ 400 የሚሆኑ ፋብሪካዎች ይገኛ።  ፋብሪካዎቹ አብዛኞቹ ወጣቶችና ሴቶች ለሆኑ፣ ከ50,000 በላይ ሰራተኞች፣ የስራ እድል መፍጠር እንደቻሉ የከተማዋ የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ወርቁ ዳባሌ ለዶይቼ ቬሌ ይናገራሉ። ለስራ ፈጠራ አምቺ ስለሆነች «የተማሩም ወይም ያልተማሩም ብዙ ወጣቶች ከተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች» ወደ ከተማዋ መጥተው ስራ ቢፈጥሩም እየጨመረ የመጣዉን የወጣት ቁጥር ግን ማስተናገድ አልቻለችም ሲሉም አቶ ወርቁ ይናገራሉ።
በኦሮሚያ ክልል ለወጣቶች ስራ ፈጠራ ተብሎ ከተመደበዉ 6,6 ቢሊዮን ብር ዉስጥ ከተማዋ ድርሻ እንደሚኖራትም የኮምዩንኬሽን ፅ/ቤት ኃላፊው ጠቅሰዋል።

ከተማዋ ለስራ ፈጠራ እያደረገች ያለችሁን እንቅስቃሴ እንድ ስሉ ያብራሩታል፣ «እናም በዚህ ዓመት ለዚህ ወጣት ቋሚ የስራ እድል ለመፍጠር ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ወይም ከኮሌጆች የወጡ፣ ትምህርታቸዉን ያቋረጡ ወይም ያልተማሩም አጣርተናል። ያጣራንዉም ወደ 12,000 ሰዎች ናቸዉ። እነሱም ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ እናስገባቸዋለን። በክልል ደረጃ መንግስት ለስራ እድል የሚመድበዉን መቶ ከመቶ ስራ ላይ እናዉላለን። እንደ ከተማችንም ወደ 101 የሚሆኑ ፕሮጄክቶች አሉን። ለእነዚህ ፕሮጄክቶች ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ አቅደናል።»

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ተወልዳ ያደገች ወጣት ማስቱ ጉታ ከጥቂት ዓመት በፊት በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሚስራታ፣ ሊቢያ፣ ለስራ ተጉዛ እንደተመለሰች ትናገራለች። ትንሽም ቢሆን አጠራቅማ ይዛ በመጣችዉ ገንዘብ በሰበታ ከተማ ፑል ማጫወቻ ቤት መክፈቷንም ለዶይቼ ቬሌ ትናገራለች። የቀኑን የገበያ ሁኔታ ታሳቢ አድርጎ በቀን ከ100 ብር እስከ 150 ብር እንደምታገኝም ተናግራለች።

ብቻዋን ከምትሰራ ተደራጅታ መንግስት አሁን በያዘዉ እቅድ መታቀፍ እንደምትፈልግም እንዲህ ስትል ትናገራለች፣ «መንግስት ለወጣቶች እንዲህ ያለ እቅድ መያዙ በጣም የሚያስደስት ነዉ። ወጣቶች ተደራጅተን የበለጠ እንድንሰራ ችግሮች ናቸዉ የተባሉት፣ ለምሳሌ የመሬት እጥረት፣ መንግስት ቢያመቻችልን ጥሩ ነዉ። ብቻዬን ፑል ከምሰራ ተደራጅተን አንድ ላይ ብንሰራ ሌሎችንም ለማነሳሳት ይረዳኛል፣ ሌሎችም ስራ ለመፍጠር እቅድ አለኝ።»

መንግስት በዚህ በያዘዉ የስራ ፈጠራ እቅድ ወጣቱን ለማደራጀት ያስቀመጣቸው ቅድመ-ሁኔታዎች አስቸጋር እንደሚሆንበት በሰበታ ከተማ የባጃጅ አሽከርካር የሆነዉ ወጣት አለም ሙሊሳ አሳቡን አጋርቶኛል።

ቅድመ-ሁኔታዎቹን በተመለከተ ባለፈዉ ሳምንት የፀደቀዉ አዋጅ ወጣቶቹ «ከፈንዱ ብድር ለማግኘት የንብረት ዋስትና እንዲያቀርቡ ሳይጠየቁ፣ ከፈንዱ ለሚያገኙት ብድር ሃላፊነት እንዲወሰዱ ለማስቻል እርስ በርሳቸዉ ዋስ መሆን» እንደምችሉም ያትታል።

ከዚህም ባለፈ ይህ የመንግስት የስራ እድል ፈጠራ ፕሮግራም ፍትኃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ያደርጋል፣ ወጣቱም ራሱ ከዚህ ከፍትኃዊ ሃብት ክፍፍል ተጠቃሚ ይሆናል ሲሉ ዶክተር ነገሪ አክለዉ ይናገራሉ። ወጣቱ በኢኮኖሚ ጉልበቱ ሲጠነክር በፖለትካ ተሳትፏቸዉም እየጠነከረ ይሄዳልም ይላሉ።

ይሁን እንጂ የኦፌኮዉ ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ ሙላቱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአንድ ጊዜ 10 ቢሊዮን ብር በመመደብ የሚስተካከል ሳይሆን መንግስት ለስራ ፈጠራዉ ለሚያደርገዉ የገንዘብ ፈሰስ ዉጤቱን በመሬት ላይ ማየት መቻል አለበት ይላሉ።

የህዝብ ቁጥር እየጨመረ በሔደ ቁጥር የሚመገብ አፍም ወይም ሆድም እየበዛ እንድሚሄድ የተፈጥሯዊ እዉነታ ነዉ። ይህ እየበዛ የምሄድ አፍም ሆነ ሆድ ካለዉ ተፈጥራዊ ሃብት ጋር ካልተመጣጠነም ማህበራዊ ቀዉስ ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎች ያስረዳሉ። እየጨመረ ለመጣዉ የወጣቱ ቁጥር እየጨመረ ለሚሔደዉ ስራ አጥነት ስራ ፈጠራዉ መፍትሔ ይሆን?

መርጋ ዮናስ

አርያም ተክሌ
 

Audios and videos on the topic