የመንግስታቱ ድርጅት 79ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ማጠቃለያ
ማክሰኞ፣ መስከረም 21 2017ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ከፊቱ የተደቀኑትን ውስብስብ ፈተናዎች መቅረፍ የሚችለው፣በጋራ በመስራት መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዚዳንት አስገነዘቡ።ፕሬዚዳንቱ ፊሊሞን ያንግ፣79ኛውን የድርጅቱን ጠቅላላ ጉባዔ ኒውዮርክ ውስጥ ትናንት ሲዘጉ ባደረጉት ንግግር ዓለም አቀፋዊ አንድነትን ጠይቀዋል። የዘንድሮው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ባለፉት ስድስት ቀናት፣ የዓለም አቀፉን ማኀበረሰብ በሚያጋጥሙ አንገብጋቢ ተግዳሮቶች ላይ ሲመክር ሰንብቷል።
የጠቅላላ ጉባዔው ፕሬዚዳንት ጥሪ
የጠቅላላ ጉባዔው ፕሬዚዳንት ፊሊሞን ያንግ፣ስብሰባውን ትናንት ሲዘጉ ባደረጉት ንግግር፣በዓለማችን እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን በተመለከተ አስቸኳይ የሰላም አስፈላጊነትን አሳስበዋል።በጋዛ፣ሊባኖስ፣ሱዳንና ዩክሬን የሚካሄዱ ግጭቶችን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ይኼ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ሙሉ ዝርዝር እንደማያሳይ አውስተዋል።ባለፉት ጥቂት ቀናት፣ሊባኖስ ውስጥ በእስራኤልና ኢዝቦላህ መኻል የታየው ከፍተኛ የሆነ የኀይል እርምጃ፣በመካከለኛው ምስራቅ ሁሉን አቀፍ ጦርነት የመቀስቀስ አደጋ እንዳለው ሚስተር ያንግ አስጠንቅቀዋል።ይህ መቆም አለበት የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ መቆም ያለበትም አሁን ነው ብለዋል።
ዓለም አቀፋዊ አንድነት
ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ፣ በፊቱ ያሉትን ውስብስብና ተስፋ አስቆራጭ ፈተናዎች መጋፈጥና ማሸነፍ የሚችለው፣በጋራ በመስራት ብቻ መሆኑንም ሚስተር ያንግ አስጽንኦት ሰጥተውታል።
"በመነጋገር፣በመደማመጥና በጋራ እርምጃ ብቻ ሁላችንንም የሚጠቅሙ መፍትሔዎችን ማግኘት እንችላለን።"በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነት፣ለሰላም መሻሻል፣ዘላቂ ልማትና ሰብዓዊ ክብር በሁሉም ቦታ የሚለው የ79ኛው ጠቅላላ ጉባዔ መሪ ቃል፣መርሕ ብቻ ሳይሆን የተግባር ጥሪ መሆኑን፣ ፕሬዚዳንቱ አስገንዝበዋል።
የድርጅቱ የተሰሚነት ጥያቄ
እዚህ ዩናይትድስቴትስ የሚገኘው የአትላንቲክ ካውንስል የቀድሞ ከፍተኛ ባልደረባ፣ አቶ ገብርኤል ንጋቱ፣የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ጉልዕ ሚና ሲጫወት ቢቆይም፣በቅርብ ዓመታት ግን የተሰሚነትና ተቀባይነት ችግር እንደተደቀነበት ለዶይቸ ቨለ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።
"በቅርብ ጊዜ ባለፉት 10 -15 ዓመታት፣ይህ ድርጅት ማንነቱን፣ እና ተሰሚነቱን እና ተቀባይነቱን እያጣ መጥተል።ጦርነት ሲኖር ወታደር አሁን የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ኀይል እየተባለ፣ዳርፉር አለ፣ ሶማሊያ አለ፣ ማሊ በየቦታው አለ፤ሰላም ለማስጠበቅ ይጣጣራል፤ ግን እንደ ድሮው የሞራል ኀያልነቱ እየደከመ መጣ።እነኚህ ትላልቅ ሃገሮች የተባበሩት መንግስታት ውሳኔ እየናቁ የማይቀበሉበት ደረጃ ላይ ደርሷል።"
የኢትዮጵያ ተሳትፎና ሚና
ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀ-ሥላሴ በተመራ የልዑካን ቡድን፣በበኒው ዮርክ በተካኼደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባዔ ላይ ስትሳተፍ ሰንብታለች።የመንግስታቱ ድርጅትን ከመሰረቱት ሃገሮች መኻከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፣በድርጅቱ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የምትታወቅ ሃገር መሆኗን አቶ ገብርኤል አመልክተዋል።
"የተባበሩት መንግስታትን መድረክ በቅጡ ተጠቅማ የኢትዮጵያን ጥቅምና ክብር አስጠብቃለች፤በንጉሡም ጊዜ በደርግም ዘመን ቢሆን የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና፣የኢራቅ ወረራ በነበረበት ጊዜ ሁሉ በወሳኝ ወሳኝ ጉዳዮች፣ጊዜዎችና ቦታዎች ላይ ንቁ ተሣትፎ አድርጋለች።ይህንን ድርጅት አጎልብታለች ፣ብዙ አስተዋጽኦ አድርጋለች።በመንግስታቱ ድርጅት መሳተፍ ብቻ ሳይሆን በየትም ሆና አስተናግዳ አስተባብራ ብዙ ሚና ተጫውታለች ኢትዮጵያ።ከአፍሪቃ ሃገሮች ከማናቸውም በላይ አስተዋጽኦ አድርጋለች፤በእዛም ያህል ደግሞ ተጠቃሚ ሆናለች።"ብለዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ