የመቶ ዓመት ሕልም | አፍሪቃ | DW | 20.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የመቶ ዓመት ሕልም

ደራሲ ናቸዉ።ፈላስፋ ናቸዉ።የመብት ተሟጋች ናቸዉ።ዊልያም ኤድዋርድ በርግሐርት ዱ ቦይስ።ፅፈዉ አልቀሩም።ዕዉቀት፣ስም ዝናቸዉን በሙሉ ተጠቅመዉ ለጥቁሮች መብት መታገያ ገንዘብ ያሰባስቡ ያዙ።ጉባኤ ጠሩም።የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ሹማምንት እንዲረዷቸዉ ጠየቁ።መልሱ ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ዓይነት ነበር

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:54

የአፍሪቃ አንድነት የመጀመሪያዉ ጉባኤ 100ኛ ዓመት

የአፍሪቃ አንድነት (ፓን አፍሪካን) የሚለዉ ፅንሠ-ሐሳብ ጥቁር ሕዝብን የሚያሰባስብ የድርጅት ቅርፅ ከያዘ ትናንት አንድ መቶ ዓመቱን ደፈነ።የካቲት 19,1919 ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ፓሪስ ፈረንሳይ የተሰየመዉ የአፍሪቃ አንድነት ጉባኤ (ፓን አፍሪካን ኮንግረስ) አፍሪቃዉያን ከቅኝ አገዛዝ እንዲላቀቁና የመላዉ ጥቁር ሕዝብ  ክብር እንዲጠበቅ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።የDW ዳንኤል ፔልስ እንደፃፈዉ አፍሪቃዉያን ግን የመስራቾቹን ዉጥን ገቢር ለማድረግ አሁንም ብዙ ይቀራቸዋል።የፔልስን ዘገባ ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።
ሕዳር 1918 ጀርመን ተሸነፈች።የመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት አበቃ።አሸናፊዎቹ ዓለምን በሚሹት መንገድ ለማደራጀት በድል ማግሥት ቬርሴይ-ፈረንሳይ ዉስጥ ተሰበሰቡ።200 ሚሊዮን የሚገመተዉን ጥቁር ሕዝብ ዕጣ-ፈንታ ግን ድል አድራጊዎቹ ከቁብ አልቆጠሩትም።
ዱ ቦይስ ግን ወገናቸዉን እንደዓለም ገዢዎች ሊረሱት አልቻሉም።«200 ሚሊዮን የሚገመተዉ ጥቁር ሕዝብ በዚሕ ታላቅ የለዉጥ ሒደት አለመወከሉ» ፃፉ ዱ ቦይስ «ታላቅ ድቀት ነዉ።» ዱ ቦይስ አዲስ በሚዋቀረዉ የዓለም ሥርዓት ዉስጥ አፍሪቃ እንድትወከል ይፈልጉ ነበር» ይላሉ በኒዮርኩ የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃ ጥናት ፕሮፌሰር ማማዱ ዱዩፍ።
ጥቁር አሜሪካዊ ናቸዉ።ደራሲ ናቸዉ።ፈላስፋ ናቸዉ።የመብት ተሟጋች ናቸዉ።ዊልያም ኤድዋርድ በርግሐርት ዱ ቦይስ።ፅፈዉ አልቀሩም።

ዕዉቀት፣ስም ዝናቸዉን በሙሉ ተጠቅመዉ ለጥቁሮች መብት መታገያ ገንዘብ ያሰባስቡ ያዙ።ጉባኤ ጠሩም።የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ሹማምንት እንዲረዷቸዉ ጠየቁ።መልሱ ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ዓይነት ነበር።በፈረንሳይ ምክር ቤት ብቸኛዉ ጥቁር እንደራሴ ብሌስ ዲያኝ ግን «አለሁ» አሏቿዉ።
የፈረንሳዮችን ፈቃድ ማግኘት፣ ቅኝ ከሚገዙ የአፍሪቃ ሐገራት ጉባኤተኞችን መሰብሰብ፣ በነፃነት መነጋገሩም ሁሉም ከባድ ነበር።ግን ዱ ቦይስና ዲያኝ እጅ አልሰጡም።ተሳካ።57 ተሳታፊዎች ለመጀመሪያዉ የአፍሪቃ አንድነት ጉባኤዉ ተሰበሰቡ።ፓሪስ።
«እነዚሕ ጥቁር መሪዎች የሚያራምዱት ሐሳብ  (የዓለምን የፖለቲካ ሥርዓት) ለመቅረፅ በሚደረገዉ ዉይይት አፍሪቃ መወከል አለባት የሚል ነበር።የአፍሪቃ ጉዳይ በጥቁሮች መቅረብ አለበት የሚል ነበር።ይሕ ዉክልና አፍሪቃ ከአንደኛዉ የዓለም ጦርነት በኋላ በሚኖረዉ ሥርት እንድትሳተፍ ይረዳልታል ባዮች ነበሩ።»
ቅኝ ገዢዎች በተለይም የብሪታንያ ገዢዎች የጥቁሮቹን ጉባኤ በአይነ ቁራኛ ይከታተሉት ነበር።ጉባኤተኞቹም ቅኝ ገዢዎች ጥያቄያቸዉን በቀላሉ እንደማይቀበሏቸዉ ጠንቅቀዉ ያዉቁታል።በበርሊኑ የሁምቦልት ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃ ታሪክ አጥኚ ፕሮፌሰር አንድሪያስ ኤከርት እንደሚሉት በተለይ ዱ ቦይስ  የቅኝ ገዢዎቹን አቋም አስቀድመዉ ቢያዉቁትም ዝም ብሎ መቀመጥ መፍትሔ እንደማይሆንም አላጣቱም።«የአዉሮጳና የሰሜን አሜሪካ ፖለቲከኞች ለቅኝ ተገዢዎቹ ነፃነት እንደማይፈቅዱ አስቀድመዉ አዉቀዉታል።ይሁንና የቅኝ ተገዢዎቹ ስቃይና ሰቆቃ እንዲሻሻል ለመጠየቅ (ለመታገል) አጋጣሚዉን ለመጠቀም ሞክረዋል።»
የመጀመሪያዉ የአፍሪቃ አንድነት ጉባኤ (ፓን አፍሪካ ኮንግረስ)  በሰወስተኛ ቀኑ ተጠናቀቀ።የአቋም መግለጫዉ፣ አፍሪቃዉያን ቀስ በቀስ የራሳቸዉን አስተዳደር እንዲመሰርቱ፣ ሐሳባቸዉን በነፃነት የመግለፅ፣የመሬት

ባለቤትነትና የመማር መብታቸዉ እንዲከበር ይጠይቃል።በአፍሪቃ ታሪክ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ክስተቶች አንዱ ይሉታል ፕሮፌሰር ዲዩፍ«ይሕ በጣም ጠቃሚ ሥፍራ የሚሰጠዉ ክስተትነዉ።ምክንያቱም፣አፍሪቃዉያንና የአፍሪቃ ዝርያ ያላቸዉ ሰዎች ዓለም አቀፍ ንቅናቄ መፍጠር የጀመሩበት ወቅት ነበርና።ይሕ ንቅናቄ በድርድሩ ላይ ቀጥተኛ ተፅኖ አልነበረዉም ግን በሁለቱ ጦርነቶች መሐል በነበረዉ ጊዜ ወሳኝ ሚና የተጫወተዉን ንቅናቄ ፈጥሯል።»
የአፍሪቃ አንድነት ጉባኤ ከዚያ በኋላ ለንደን፤ኒዮርክ፣ማንቸንስተር ተደርጓል።ኋላ የየሐገራቸዉ የነፃነት ታጋይና መሪ ለመሆን የበቁት የኬንያዉ ጆሞ ኬንያታና የጋናዉ ክዋሚ ንኩሩማ የዚሕ ጉባኤ ዉጤቶች ናቸዉ።ንኩሩማ አክራ ዉስጥ ጉባኤዉን አስተናግደዋል።የዛሬዉ የአፍሪቃ ሕብረትም ትናንት መቶ ዓመት የደፈነዉ የአፍሪቃ አንድነት እሳቤ ዉጤት ነዉ።የሕብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ሙሳ ፋኪ በዘንድሮዉ የጎርጎርያኑ 2019 ዘመን መለወጫም ሕብረታቸዉ የአፍሪቃን አንድነት ለማጠናከር እንደሚጥር ቃል ገብተዋል።ገቢራዊነቱ ግን አሁንም «ሩቅ» ይመስላል። 

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ
 

Audios and videos on the topic