የመስከረም 24 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ  | ስፖርት | DW | 04.10.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የመስከረም 24 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ 

በለንደን ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲና ሊቨርፑል ድንቅ ጨዋታ ዐሳይተዋል። የሊቨርፑሉ ሞሐመድ ሳላኅ ከ6 በላይ ተጨዋቾችን አታሎ ከመረብ ያሳረፋት ኳስ በሳምንቱ ከታዩ አስደማሚ ግቦች በልዩ ሁኔታ ልትመዘገብ ይገባል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙይንሽን ያልተጠበቀ ሽንፈት ገጥሞታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:23

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በለንደን ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል ድንቅ የሚባል ጨዋታ ዐሳይተዋል። የሊቨርፑሉ ሞሐመድ ሳላኅ ከስድስት በላይ ተጨዋቾችን አታሎ ከመረብ ያሳረፋት ኳስ በሳምንቱ ከታዩ አስደማሚ ግቦች በልዩ ሁኔታ ልትመዘገብ ይገባል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙይንሽን ያልተጠበቀ ሽንፈት ገጥሞታል። በደረጃ ሰንጠረዡ ታች በሚገኝ ቡድን ነው ኃያሉ ባየርን ሙይንሽን ጉድ የሆነው። የዩናይትድ ስቴትስ የሴቶች እግር ኳስ አመራር በወሲብ ቅሌት መነጋገሪያ ኾኗል። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን ጉዳዩ ላይ ቅድመ ምርመራ መጀመሩን ዐሳውቋል።

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባለፈው ሳምንት በቤርሊን ማራቶን ካገኙት ድል በተጨማ በለንደን ማራቶንም አሸናፊ ሆነዋል። ትናንት በተከናወነው የለንድን ማራቶን የወንዶች የሩጫ ፉክክር፦ ኢትዮጵያዊው ሲሳይ ለማ እና ሞስነት ገረመው አንደኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል። በሴቶች ተመሳሳይ ርቀት ኬንያዊቷ ጆይሲሊን ጄፕኮስጌይ ውድድሩን በበላይነት አጠናቃለች። ጆይሲሊን ጄፕኮስጌይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተወዳደረችበትን የለንደን ማራቶን በአሸናፊነት ያጠናቀቀችው 02 ሰዓት ከ17 ደቂቃ ከ43 ሰከንድ በመሮጥ ነው። ኢትዮጵያውያቱ አትሌት ደጊቱ አዝመራው እና አሸቴ በከሬ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሆነው አጠናቀዋል። ደጊቱ ውድሩን ለማጠናቀቅ 2 ሰአት ከ17 ደቂቃ ከ58 ሰከንድ ሲፈጅባት፤ አሸቴ በከሬ ደግሞ 2 ሰአት ከ18 ደቂቃ ከ18 ሰከንዶች በመሮጥ ነው የሦስተኛ ደረጃን የያዘችው።

በወንዶች የማራቶን ሩጫ ፉክክር ባለፈው ዓመት ሦስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ሲሳይ በዘንድሮው የማራቶን ሩጫ አንደኛ የሆነው በ2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ01 ሰከንድ በመሮጥ ነው። በትናንቱ ፉክክር፦ ከሲሳይ 27 ሰከንዶች ዘግይቶ ውድድሩን የጨረሰው ኬንያዊው ቪንሰንት ኪፕቹማ ሁለተኛ ወጥቷል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሞስነት ገረመው ውድድሩን ያጠናቀቀው በሦስተኛነት ነው።

በሌላ የ10 ሺህ ሜትር የሩጫ ፉክክር ደግሞ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የባሕሬን ሯጭ ቃልኪዳን ገዛኸኝ ጄኔቫ ውስጥ 29 ደቂቃ ከ38 ሰከንዶች በመሮጥ አሸናፊ ሆናለች።አትሌት ቃልኪዳን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2017 በኬኒያዊቷ ጆሲሊኔ ጄፕኮስጌይ ተይዞ የቆየውን የዓለም ክብረወሰን በአምስት ሰከንዶች አሻሽላለች።ቃልኪዳን ገዛኸኝ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የ10 ሺህ ሜትር የሩጫ ፉክክር ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የሆላንድ ሯጭ ሲፋን ሐሰንን በመከተል የብር ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው።

በወንዶች የጄኔቫው የ10 ሺሕ ሜትር ውድድር ቀደም ሲል በግማሽ ማራቶን የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነው ኪቢዎት ካንዲ 26 ደቂቃ ከ51 ሰከንድ በመሮጥ አሸንፏል።

ፕሬሚየር ሊግ

በሳምንቱ መጨረሻ ከተከናወኑ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች የትናንቱ የማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል ግጥሚያ የበርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል። በመጀመሪያው አጋማሽ ማንቸስተር ሲቲ ባየለበት ግጥሚያ ሁለቱም ቡድኖች ያለምንም ግብ ረፍት ቢወጡም ከእረፍት መልስ በየርገን ክሎፕ የሚመራው ሊቨርፑል ድክመቶቹን አሻሽሎ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ሞክሯል።  በ59ኛው ደቂቃ ላይም ሳዲዮ ማኔ የመጀመሪያዋን ግብ በማስቆጠር አንፊልድ ውስጥ የተሰባሰቡ የሊቨርፑል ደጋፊዎችን እፎይ አሰኝቷል። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ በ69ኛው ደቂቃ ላይ ፊል ፎዴን በግሩም ሁኔታ ከመረብ በማሳረፍ ለማንቸስተር ሲቲ ደጋፊዎች ደስታን ለሊቨርፑል ደግሞ ዳግም ስጋት አጭሯል። ፎዴን በዕለቱ ግጥሚያ በፈጣን እና ጥበብ በተሞላበት እንቅስቃሴው የሊቨርፑል ተከላካዮችን ሲያስጨንቅ ቆይቷል። ምናልባትም ተጨማሪ ግቦችን ማግባት ይችልም ነበር። 

ብርቱ ፉክክር በታየበት የትናንቱ ግጥሚያ በ76ኛው ደቂቃ ላይ ሊቨርፑል ዳግም መሪቱን ጨብጦ ነበር። ከኩርቲስ ጆነስ የተሻገረለትን ኳስ ሞሐመድ ሳላህ ከስድስት በላይ ተጨዋቾችን በማታለል ከግቡ በስተግራ በኩል የላካት ኳስ ከመረብ ያረፈችው በድንቅ ሁኔታ ነበር። ሙሐመድ ሳላኅ ልዩ ብቃቱን አስመስክሯል። በፕሬሚየር ሊጉ በርካታ ግቦችን ካስቆጠሩ አፍሪቃዊ ተጨዋቾች ተርታ ቀዳሚ ለመሆንም ጫፍ ደርሷል። ቀደም ሲል የቸልሲን መለያ ለብሶ ይጫወት የነበረው የአይቮሪ ኮስቱ አጥቂ ዲዲየር ድሮግባ ጫማውን የሰቀለው በፕሬሚየር ሊጉ 104 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ነው። በዚህም ከአፍሪቃውያን ተጨዋቾች የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አግቢ ነው። ሞሐመድ ሳላኅ የትናንት ድንቅ ግቡ 103ኛ ሆኖ ተመዝግቦለታል። 

ሊቨርፑል የትናንቱን ወሳኝ ጨዋታ በማሸነፍ ነጥቡን ከፍ አድርጉ መሪነቱን ሊቆናጠጥ ነው የሚለው ስጋት በማንቸስተር ሲቲዎች መካከል ባየለበት እና አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ እጅግ በተበሳጩበት ቅጽበት ኬቪን ደ ብሩይኔ ታድጓቸዋል። በቀጥታ ወደ ግብ የመታትን ኳስ ምናልባት አሊሰን ቤከር ሊያጨናግፋት በቻለ ነበር። ሆኖም ግን ኳሷ በሊቨርፑሉ ተከላካይ ጆኤል ማቲፕ ደረት መጨረፏ ከግብ ጠባቂው ቁጥጥር ውጪ በመሆን በቀጥታ መረብ ላይ አርፋለች። በዚህም ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ ሁለት እኩል በመለያየት ነጥብ ተጋርተዋል።

ቅዳሜ ዕለት ሳውዝሐምፕተንን በሰፋ የግብ ልዩነት 3 ለ1 ድል ያደረገው ቸልሲ በ16 ነጥብ የፕሬሚየር ሊግ መሪነቱን ተቆናጧል። እስካሁን በተደረጉ 7 የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች አንድም ጊዜ ሽንፈት ያልገጠመው ሊቨርፑል ከቸልሲ በአንድ ነጥብ ብቻ ተብልጦ የሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ትናንት ከሊቨርፑል ጋር ነጥብ የተጋራው ማንቸስተር ሲቲ በ14 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማንቸስተር ዩናይትድ ዐርብ ዕለት ከኤቨርተን ጋር ባደረገው ግጥሚያ አንድ እኩል ተለያይቷል። በዚህም መሠረት ማንቸስተር ዩናይትድ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ተመሳሳይ 14 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ ልዩነት ብቻ የአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች አንድ አንድ ጊዜ ብቻ ያሸነፉት በርንሌይ እና ኒውካስል 18ኛ እና 19ኛ ደረጃ ላይ ሰፍረዋል። በአንድ ነጥቡ ብቻ የተወሰነው ኖርዊች ሲቲ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 20ኛ ላይ ይገኛል።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ የሳምንቱ መጨረሻ ጨዋታዎች የባየርን ሙይንሽን በፍራንክፉርት መሸነፍ የደረጃ ሠንጠረዥ መሪውን ደጋፊዎች አስደንግጧል። ያለፈው የውድድር ዘመን የቡንደስሊጋ ዋንጫ ባለቤት ባየርን ሙይንሽን ትናንት በፍራንክፉርት 2 ለ1 ተሸንፎ ነጥብ በመጣሉ ከባየርን ሌቨርኩሰን ጋር በነጥብ ተስተካክሏል። ተመሳሳይ 16 ነጥብ ያለው ባየርን ሌቨርኩሰን በባየርን ሙይንሽን የሚበለጠው በግብ ክፍያ ብቻ ነው። ባየርን ሌቨርኩሰን ቢሌፌልድን 4 ለ0 ማሸነፉ እጅግ ጠቅሞታል። አሁን በባየርን ሙይንሽን የሚበለጠው በ4 የግብ ክፍያ ብቻ ነው። ሁለቱም 16 ነጥብ ይዘዋል።

ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ፍራይቡርግ 15 ነጥብ ይዘው በግብ ክፍያም ተመሳሳይ ናቸው። ሁለቱም 6 የግብ ክፍያ አላቸው። ሆኖም በርካት ግቦችን አስቆጥሮ በርካታ ግቦች የተቆጠሩበት ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ከፍራይቡርግ በልጦ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቅዳሜ ዕለት አውግስቡርግን 2 ለ1 አሸንፏል። ሔርታ ቤርሊንን ከትናንት በስትያ 2 ለ1 ያሸነፈው ፍራይቡርግ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 13 ነጥብ ያለው ቮልፍስቡርግ 5 ደረጃን ተቆናጧል። ቅዳሜ ዕለት በቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ የ3 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። ላይፕትሲሽ ቦኹምን 3 ለ0 ሲያሸንፍ፤ ሆፈንሃይም በሽቱትጋርት የ3 ለ1 ሽንፈት ቀምሷል። ማይንትስ በዑኒዮን ቤርሊን ትናንት 2 ለ1 ተሸንፏል። ላይፕትሲሽ እስካሁን ባደረጋቸው የቡንደስሊጋ ጨዋታዎች 10 ነጥብ በመሰብሰብ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት ድል የቀናው ዑኒዮን ቤርሊን ላይፕትሲሽን በ2 ነጥብ በልጦ የ7ኛ ደረጃን ይዟል። ኮሎኝ በተመሳሳይ 12 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የወሲብ ቅሌት በዩናይትድ ስቴትስ የሴቶች ቡድን

የዩናይትድ ስቴትስ እግር ኳስ በወሲብ ቅሌት የተነሳ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።  ቅሌቱ ባስከተለው ጣጣ የሀገሪቱ ብሔራዊ የሴቶች እግር ኳስ ሊግ (NWSL) ኮሚሽነር ሊዛ ቤይርድ ሥልጣናቸውን ለቅቀዋል። ሊጉ አዲስ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መሰየሙንም ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ከኮሚሽነሯ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የሰሜን ካሮላይን ከሬጅ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ፖል ሪሌይ፦ «በቀላሉ የማይታይ አጉል ጠባይ» ዐሳይተዋል በሚል ከቡድኑ መሰናበታቸው ተዘግቧል። የ58 ዓመቱ ፖል ሪሌይ መጠነ ሰፊ ወሲባዊ ቅሌቶችን ፈጽመዋል ሲል አትሌቲክስ ስፖርት መዘገቡን ተከትሎ ነበር ባለፈው ሐሙስ ከሥልጣናቸው መነሳታቸው የተነገረው። ዐርብ ዕለት ደግሞ ኮሚሽነሯ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው ተገልጧል።

አሰልጣኙ በርካታ ተጨዋቾች ወሲብ እንዲፈጽሙ፤ አንዳንድ ምሽቶች ላይ ደግሞ ተጨዋቾች አለቅጥ አብረዋቸው አልኮል እንዲጠጡ ማስገደዳቸውም ተዘግቧል። በቀረበው ክስ ላይ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን (FIFA) ቅድመ ምርመራ መጀመሩን ዐስታውቋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች