የመስከረም 10 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ  | ስፖርት | DW | 20.09.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የመስከረም 10 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ 

የማንቸስተር ዩናይትዱ ግብ ጠባቂ ዳቪድ ዴ ኼአ ቡድኑን ባለቀ ሰአት ነጥብ ከመጣል ታድጓል። ጄሲ ሊንጋርድ ወደ ዳግም ብቃቱ የተመለሰ ይመስላል። በሻምፒዮንስ ሊግ ድል የቀናው ሊቨርፑል የመሪነቱን ስፍራ ተቆናጧል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዴንማርክ ኮፐንሃገን ውስጥ በተከናወነ የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር በወንድም በሴትም ድል ቀንቷቸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:18

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየሚየር ሊግ የማንቸስተር ዩናይትዱ ግብ ጠባቂ ዳቪድ ዴ ኼአ ቡድኑን ባለቀ ሰአት ነጥብ ከመጣል ታድጓል። ጄሲ ሊንጋርድ ወደ ዳግም ብቃቱ የተመለሰ ይመስላል። በሻምፒዮንስ ሊግ ድል የቀናው ሊቨርፑል የመሪነቱን ስፍራ ተቆናጧል። ከቸልሲ ጋር የአንደኛነቱን ደረጃ በተመሳሳይ ነጥብ እና የግብ ክፍያ ተቆናጠዋል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ክብረወሰን መስበር ችሏል። አሊያንትስ አሬና ውስጥ ቦሁምን 7 ለ0 ባንኮታኮቱበት ግጥሚያም ይኸው ፖላንዳዊ የግብ ቀበኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዴንማርክ ኮፐንሃገን ውስጥ በተከናወነ የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር በወንድም በሴትም ድል ቀንቷቸዋል።

አትሌቲክስ

ዴንማርክ ኮፐንሃገን ውስጥ ትናንት በተከናወነው የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንድም በሴትም ድል ቀንቷቸዋል። በሴቶች ፉክክር አትሌት ፀሐይ ገመቹ ያሸነፈችው አዲስ ክብረወሰን በመስበር ነው። ርቀቱን ለማጠናቀቅ የፈጀባት 1:05:08 ሲኾን፤ ከዛሬ ሦስት ዓመት በትውልደ ኢትዮጵያዊት ሆላንዳዊቷ አትሌት ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን በሰባት ሰከንዶች ማሻሻል ችላለች። በትናንቱ ውድድር ሁለተኛ የወጣችውም ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሐዊ ፈይሳ ናት፤ ውድድሩን ያጠናቀቀችውም ከፀሐይ በ33 ሰኮንዶች ተበልጣ ነው። በውድሩ ከመላው ዓለም ወደ 20,000 የሚጠጉ ተወዳዳሪዎች እንደተሳተፉ ተዘግቧል። በተመሳሳይ የወንዶች ሩጫ ከኬንያዊ አትሌት ብርቱ ፉክክር ገጥሞት የነበረው ኢትዮጵያዊው አትሌት አምደ-ወርቅ ዋለልኝ 59 ሰከንድ ከ10 ሰከንዶች በመሮጥ አሸናፊ ኾኗል። ኬኒያዊው ኬኔዝ ሬንጁ በ2 ሰከንዶች ብቻ ተበልጦ የሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል። የሦስተኛ ደረጃውንም የያዘው ኬኒያዊው አትሌት ዳንኤል ማታይኮ ነው። አንደኛ ከወጣው አምደ-ወርቅ በ15 ሰከንዶች ተበልጧል።  

የፊታችን እሁድ በሚካሄደው የበርሊን ማራቶን 25,000 ሰዎች እንደሚሳተፉበት አዘጋጆቹ ዐስታወቁ። የበርሊን ማራቶን የኮሮና ወረርሽን ከተከሰተ ወዲህ የሚደረግ ግዙፉ የማራቶን ውድድር እንደሆነ ተገልጿል። አምና ሊደረግ ታቅዶ የነበረው ውድድር በዓለም አቀፍ ደረጃ ብርቱ ጉዳት ባደረሰው የኮሮና ወረርሽኝ ሳብያ ሳይካሄድ ቀርቷል። በውድድሩ   «አሁንም ድረስ የስፖርት ከተማ መሆናችንን ለተቀረው ዓለም የምናሳይበት ውድድር ነው» ሲሉ የበርሊን ከተማ የውድድር አዘጋጁ ድርጅት ዳይሬክተር የርገን ሎክ ተናግረዋል። በውድድሩ ከሚሳተፉቱ «ከ90 በመቶ በላይ የጸረ ኮሮና ክትባት በሙሉ የተከተቡ አልያም በበሽታው ተይዘው ያገገሙ እንደሚሆኑ» የገለጹት አስተባባሪው የተቀሩት ተሳታፊዎች ከውድድሩ በፊት 48 ሰዓት ያልሞላው ከተሐዋሲው ነጻ የምርመራ ውጤት ማቅረብ ይኖርባቸዋል» ብለዋል። በተጨማሪም ተወዳዳሪዎች በውድድር መነሻ እና መጨረሻ ስፍራዎች የፊት መሸፈኛ ማስክ የማድረግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።  የ42,195 ኪ.ሜ በሚሸፍነው የመሮጫ ጎዳናዎች የሚታደሙ ተመልካቾችም በተመሳሳይ የፊት መሸፈኛ ማስክ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ተጠቁሟል። የበርሊን ማራቶን ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለ በኬንያዊው ኤሊውድ ኬፕቾጌ የተያዘውን የዓለም ክብረ ወሰን ለማሻሻል ሁለት ሰከንዶች ብቻ ዘግይቶ ያሸነፈበት የጎርጎሪዮሱ 2019 የቅርብ ጊዜ ውድድር ነበር። በውድድሩ ቀነኒሳ በቀለ 2;01;41 የገባበት ሰዓት ነበር። የዓለም ክብረወሰን በኬንያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌ በጎርጎሪዮሱ 2018 በርሊን ላይ በተደረገ ውድድር ነበር የተያዘው። ሰዓቱም 2;01;39 ነበር ። በዘንድሮው የበርሊን ውድድር ከስመ ጥር አትሌቶች እነማን እንደሚሳተፉ የጀርመን ዜና ምንጭ በዘገባው አልጠቀሰም። ውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ይደረጋል።

እግር ኳስ

ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሁለተኛ ዙር ግጥሚያዋን በቀጣይ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ታደርጋለች። ቡድኑ ለዚያ ዝግጅት ልምምዱን ለማድረግ ከአራት ቀናት በኋላ ወደ ባሕር ዳር ያቀናል። ለዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታው ምን ያህል ዝግጅት እየተደረገ ነው? ምን አይነት ውጤትስ መጠበቅ ይቻላል? የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ብሔራዊ ቡድኑ ጥሩ ልምምድ እያደረገ እንደሆነ እና በጥሩ መነቃቃት መንፈስ ላይ እናዳለ ተናግረዋል።

በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ድል የቀናው ሊቨርፑል በፕሬሚየር ሊጉም መሪነቱን ተረክቧል። በሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ባሳለፍነው ረቡዕ የጣሊያኑ ሚላንን 3 ለ2 የረታው ሊቨርፑል በፕሬሚየ ርሊጉም ድል ቀንቶታል። ከትናንት በስትያ ባደረገው ግጥሚያ ብርቱ ተፎካካሪ የነበረው የፓትሪክ ቪዬራ ቡድን ክሪስታል ፓላስን 3 ለ0 አሸንፏል። ለሊቨርፑል ቀዳሚዋን ግብ ከግቡ በስተቀን ጠርዝ በአስቸጋሪ ኹኔታ መትቶ ከመረብ ያሳረፈው ሳዲዮ ማኔ ነው። በ43ኛው ደቂቃ ላይ። ከእረፍት መልስ ክሪስታል ፓላሶች ግብ ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ሊሳካላቸው ግን አልቻለም። ሞሐመድ ሳላህ 73ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛውን ግብ ለሊቨርፑል ሲያስቆጥር ለአሰልጣኝ ፓትሪክ ቪዬራ እና ቡድኑ ክሪስታል ፓላስ ተስፋ አስቆራጭ ነበር። በ89ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ናቢ ዴኮ ኪዬታ ከግቡ ፊት ለፊት ከ30 ሜትር ርቀት አካባቢ በቀጥታ የመታት ኳስ ከመረብ አርፋለች። ኬታ ግቧን ካስቆጠረ በኋላ ምንም አይነት የደስታ ስሜት አላሳየም፤ እንደ ሌሎቹ ተጨዋቾች አልጨፈረም። በአንጻሩ ሞሐመድ ሳላኅ ግቧን ካስቆጠረ በኋላ መለያ ልብሱን በማውለቁ ቢጫ ካርድ ዐይቶ ነበር። በሊግ የካራባዎ ግጥሚያም ነገ ማታ ከኖርዊች ጋር ጨዋታ ይኖረዋል።

 

ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ባደረገው ወሳኝ ግጥሚያ ዌስትሐም ዩናይትድን 2 ለ1 ድል አድርጓል። በዚያም ነጥቡን ከሊቨርፑል እና ቸልሲ ጋር ማስተካከል ችሏል። በግብ ክፍያ ልዩነት ብቻ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል። በትናንቱ ግጥሚያ ባለቀ ሰአት ዌስት ሐም ዩናይትዶች ያገኙትን የፍጹም ቅጣት ምት ፍጹም ቅጣት ምቱን ለመምታት ብቻ ተቀይሮ የገባው ማርክ ኖብል ኳሷን በቀጥታ ለግብ ጠባቂው ዳቪድ ዴኼኣ አሳቅፎት ጨዋታው 2 ለ1 ተጠናቋል። ለዌስትሀም ዩናይትድ ቀዳሚዋን ግብ በ30ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ሳይድ ቤንራሃም ነው። ብዙም ሳይቆይ ግን በ35 ኛው ደቂቃ ላይ ማንቸስተር ዩናይትድን አቻ የምታደርገውን ግብ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ማስቆጠር ችሏል። ተቀይሮ የገባው ጄሲ ሊንጋርድ ድንቅ በሚባል ኹኔታ የማሸነፊያዋን ግብ 89ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል።

ትናንት ቶትንሀምን የገጠመው ቸልሲ በቲያጎ ሲልቫ 49ኛው ደቂቃ ላይ፤ በንጎሎ ካንቴ 57ኛው እንዲሁም አንቶኒዮ ሩዲገር 92ኛው ደቂቃ ላይ በተቆጠሩ ሦስት ግቦች ድል አድርጓል። በዚህም በነጥብም በግብ ክፍያም ከሊቨርፑላ ጋር ተስተካክሏል። በሌላ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ዛሬ ማታ ባርሴሎና ከግራናዳ ጋር ይፋለማል።  በጣሊያን ሴኢአ ደግሞ ናፖሊ ኡዲኒዜን ይገጥማል።

በቡንደስሊጋው ባየርን ሙይንሽን ቦኹምን 7 ለ0 ባንኮታኮተበት ግጥሚያ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ 43ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ቦኹምን ያሸነፉበት ግጥሚያ ባየርን ሙይንሽን ለ13 ጊዜያት በተከታታይ ድል ያደረገበት ነው። ከዚህ ቀደም ጌርድ ሙይለር እና ዩፕ ኼዩንከስ 12ጊዜያት በመደዳ ማሸነፍ ችለው ነበር። ባየርን ሙይንሽን ባርሴሎናን በሻምፒዮንስ ሊግ 3 ለ0 ካሸነፈ በኋላ ያገኘው ድል ነው። ላይፕትሲሽንም ካንኮታኮተ አንድ ሳምንት በኋላ የተገኘ ሌላ ድንቅ ድል ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ 

Audios and videos on the topic