የመስከረም 03 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ  | ስፖርት | DW | 13.09.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የመስከረም 03 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ 

የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞ ሳላኅ 100ኛ ግቡን ትናንት አስቆጥሯል። ከ12 ዓመታት በኋላ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ የተመለሰው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በፕሬሚየር ሊጉ ሁለተኛ ጨዋታው ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ለ7 ጊዜያት የዓለማችን ኮከብ የኾነው ሌዊስ ሐሚልተን ትናንት በውድድር ወቅት ለጥቂት ከከባድ አደጋ ተርፏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:55

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወነው የ5 ኪሎ ሜትር ውድድር ክብረወሰን ሰብራለች። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት በውድድር ወቅት ባደረገው ጫማ የመርገጫ ከፍታ ምክንያት የማራቶን ድሉ ተነጥቋል። የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞ ሳላኅ 100ኛ ግቡን ትናንት ሊድስ ዩናይድን ባሸነፉበት ግጥሚያ በመክፈቻው አስቆጥሯል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ታሪክ 100 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍም ሁለተኛው አፍሪቃዊ ተጨዋች ኾኗል። ከ12 ዓመታት በኋላ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ የተመለሰው ፖርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለማንቸስተር ዩናይትድ ሁለት ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ለ7 ጊዜያት የዓለማችን ኮከብ የኾነው ሌዊስ ሐሚልተን ትናንት በውድድር ወቅት ለጥቂት ከከባድ አደጋ ተርፏል።

አትሌቲክስ

ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ጨዋታዎች ቅኝት ከመሻገራችን በፊት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እና ቡድኖች በሳምንቱ መጨረሻ ያከናወኗቸውን ውድድሮች አጠር አድርገን እናሰማለን። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሠንበሬ ተፈሪ ትናንት በ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር የዓለም ክብረወሰን በመስበር አሸናፊ ኾናለች። ሠንበሬ ርቀቱን 14 ደቂቃ ከ30 ሰከንዶች በመሮጥ ያሸነፈችው ጀርመን ባየርን ግዛት ውስጥ ከኒውረንበርግ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው አነስተኛዋ የሔርሶጌናውራህ መንደር ውስጥ በተከናወነው ፉክክር ነው። ከዚህ ቀደም የርቀቱ ክብረወሰን ተይዞ የነበረው በኬንያዊቷ ቢያትሪስ ቼፕኮዬች ነበር። ሠንበሬ ክብረ ወሰኑን ያሻሻለችው በዐሥራ ሦስት ሰከንድ ነው። ኬኒያዊቷ የካቲት ወር ላይ ሞናኮ ውስጥ በተደረገው ፉክክር በአንድ ሰከንድ ልዩነት ክብረወሰኑን የነጠቀችው ከትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሆላንዳዊት ሲፋን ሐሰን ነበር። ሲፋን ከሁለት ዓመታት ግድም በፊት ተመሳሳዩን የ5 ኪሎ ሜትር ርቀት 14 ደቂቃ ከ44 ሰከንድ በመሮጥ ነበር ክብረወሰን ይዛ የቆየችው። አሁን ክብረወሰኑ በሠንበሬ ተፈሪ ተሰብሯል።

በሌላ የአትሌቲክስ ዜና፦ በኦስትሪያ ቪዬና የማራቶን ፉክክር ትናንት 2 ሰአት ከ09 ደቂቃ ከ22 ሰከንድ በመሮጥ አንደኛ ወጥቶ የነበረው ኢትዮጵያዊ አትሌት ደራራ ሑሪሳ ባደረገው የመሮጫ ጫማ ምክንያት ድሉ ተነጥቋል። አትሌት ደራራ አዲዳስ ባዘጋጀው የአዲዜሮ ፉክክር ላይ ተጫምቶት የነበረው ጫማ መርገጪያ ከ40 ሚሊ ሜትር ወፈር ያለ ነው በሚል ነው ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላ አሸናፊነቱ የተሰረዘው። እናም 2 ሰአት ከ09 ደቂቃ ከ25 ሰከንድ በመሮጥ በውድድሩ ሁለተኛ ወጥቶ የነበረው ኬኒያዊው አትሌት ሌዮናርድ ላንጋት አሸናፊ ኾኗል። ኢትዮጵያዊው አትሌት በተስፋ ጌታሁን እና ኬኒያዊው ኤድዊን ኮሴጂ በመሸጋሸግ የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

እግር ኳስ

በአፍሪቃ ሻምፒዮን ሊግ የእግር ኳስ ማጣሪያ የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያ ትናንት ባህር ዳር ከተማ ውስጥ በአል ሂላል 2 ለ0 ሲመራ የቆየው ፋሲል ከነማ ቡድን ሁለት እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል። ለፋሲል ከነማ በረከት ደስታ በ65ኛው እንዲሁም ኦኪ አፎላቢ በ78ኛው ደቂቃ ላይ ሁለቱን ግቦች ከመረብ አሳርፈዋል። ሞሐመድ አብደል ራማን ዮሲፍ በ23ኛው እንዲሁም ያሲር ሞዛሚል በ53ኛው ደቂቃዎች ላይ ባስቆጠሯቸው ግቦች የሱዳኑ አል ሂላል 2 ለ0 ሲመራ ነበር። ከእረፍት መልስ በተገኙ ሁለት ግቦች ግን ፋሲል ከነማ አቻ መውጣት ችሏል። በሌላ ውድድር፦ በካፍ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ግጥሚያ  የኢትዮጵያ ቡና በዩጋንዳው ሬቨኒው አውቶሪቲ የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። የመልሱን ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡና ቡድን የፊታችን እሁድ በሜዳው ያከናውናል።

ፕሬሚየር ሊግ

ሞ ሳላኅ ትናንት ሊቨርፑል ሊድስ ዩናይትድን 3 ለ0 ባሸነፈበት ግጥሚያ ያስቆጠረው የመክፈቻ ግብ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ 100 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ከዲዲዬር ድሮግባ ቀጥሎ ሁለተኛው አፍሪቃዊ አድርጎታል። የሁለት ጊዜያት የአፍሪቃ ኮከብ ተጨዋችነትን ማዕረግ የተቀዳጀው ግብጻዊው የሊቨርፑል አጥቂ ሞሐመድ ሳላኅ 100ኛ ግቡን ማስቆጠር የቻለው በ162ኛ ጨዋታው ነው። በዚህም ሞ ሳላኅ በፕሬሚየር ሊጉ ታሪክ 100 ግቦችን ባማስቆጠር አምስተኛው ፈጣን አጥቂ ኾኗል። አራተኛው ፈጣን አግቢ 100ኛ ግቡን በ160ኛ ጊዜ ሲሰለፍ ያስቆጠረው ቲዬሪ ኦንሪ ነው። ሠርጂዮ አጉዌሮ በ147 ጊዜ ተሰላፊነቱ መቶኛ ግቡን ሲያስቆጥር፤ ሐሪ ኬን በ141ኛ ተሰላፊነቱ መቶኛዋን ግብ ከመረብ በማሳረፍ የሁለተኛ ደረጃን ይይዛል። ከሁሉም ተጨዋቾች 100ኛ ግቡን በፕሬሚየር ሊጉ በፍጥነት በማስቆጠር የሚመራው አለን ሺረር ነው።  አለን ሺረር 100ኛ ኳሱን ከመረብ ያሳረፈው በፕሬሚየር ሊጉ ለ124ኛ ጊዜ በተሰለፈበት ወቅት ነበር። ኢያን ራይት እና ሮቢ ፎለር በ173ኛ እና 175ኛ ተሰላፊነታቸው 100ኛ ግባቸውን በማስቆጠር ከሞ ሳላኅ ስር ይገኛሉ።

በትናንቱ ድል ሊቨርፑል ነጥብ እና የግብ ክፍያውን ከቸልሲ ጋር በማስተካከል የሁለተኛ ደረጃን ተጋርቷል። ሁለቱም 10 ነጥብ እና 9 የግብ ክፍያ አላቸው።  ማንቸስተር ዩናይትድ በተመሳሳይ 10 ነጥብ ኾኖም በ11 የግብ ክፍያ በአንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ከ12 ዓመታት በኋላ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ የተመለሰው ፖርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ግብ ማስቆጠር ጀምሯል። የ36 ዓመቱ አጥቂ ቅዳሜ ዕለት ማንቸስተር ዩናይትድ ኒውካስል ዩናይትድን 4 ለ1 ኩም ባደረገበት ግጥሚያ ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል። በዚያም አሁንም ድረስ የግብ ቀበኛነቱን አስመስክሯል። እንደ ቀድሞው በርካታ ተጨዋቾችን በኳስ ጥበቡ እያታለለ ባይሆንም ወዲያው ያገኛቸውን ኳሶች ከመረብ ማሳረፍ እንደሚችል ግን ዐሳይቷል። የመጀመሪያዋ ግብ የተቆጠረችው የኒውካስሉ ግብ ጠባቂ ፍሬዲ ውድማን ያጨናገፋትን ኳስ በፍጥነት ከተከላካይ አፈትልኮ በመውጣት በመምታት ነው።

ቡንደስሊጋ

ቅዳሜ ዕለት በተከናወኑ ግጥሚያዎች ቦሩስያ ዶርትሙንድ ባየር ሌቨርኩሰንን 4 ለ3 ድል በማድረግ ነጥቡን ወደ 9ኝ ከፍ አድርጓል።  አውግስቡርግ ከዑኒየን ቤርሊን ጋር ያለምንም ግብ ሲለያይ፤ ባየርን ሙይንሽን ላይፕትሲሽን በሰፋ የግብ ልዩነት 4 ለ1 አሸንፏል።  አሰልጣኝ ዩሊያን ናግልስማን የቀድሞ ቡድናቸውን በሰፋ የግብ ልዩነት ለማሸነፍ አልተቸገሩም። ላይፕትሲሽ ባለፉት አራት ግጥሚያዎቹ የቅዳሜው ሦስተኛ ሽንፈቱ ነበር። በዚህም በ3 ነጥብ ብቻ ተወስኖ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 10ነጥብ ያለው ባየርን ሙይንሽን በቮልፍስቡርግ በ2 ነጥብ ተበልጦ የሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ዘንድሮ ወደ ቡንደስሊጋው ያደገው ግሮይተር ፍዩርትስ በቮልፍስቡርግ እንዲሁም ሆፈንሃይም በማይንትስ 2 ለ 0 ተሸንፈዋል። እንደ ቦሩስያ ዶርትሙንድ 9 ነጥብ ያለው ማይንትስ በግብ ክፍያ ተበልጦ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 74ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ተጨዋቹ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተበት ኮሎኝ ከፍራይቡርግ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። ፍራይቡርግ አቻ የምታደርገውን ግብ በራፋኤል ያስቆጠረው ፍሎሪያን ካይንትስ በቀይ ካርድ ከተሰናበተ ከ15 ደቂቃ በኋላ ላይ ነው።

ትናንት በተከናወኑ የቡንደስ ሊጋ ግጥሚያዎች ደግሞ ሔርታ ቤርሊን ቦኹምን 3 ለ1 ድል አድርጓል። ከታችኛው ዲቪዚዮን በማደግ ዘንድሮ ቡንደስሊጋውን የተቀላቀለው አርሚኒያ ቢሌፌልድ በቦሩስያ ሞይንሽንግላድኅ 3 ለ1 ተሸንፏል። ቢሊፌልዶች እስከ 69ኛው ደቂቃ ድረስ አንድ እኩል በመሆን በቡንደስሊጋው ልምድ ያለው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድኅን አስጨንቀው አምሽተዋል። ሆኖም ቀዳሚዋን ግብ በ35ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ የነበረው ላርስ ሽቲንድል 69ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግቡን ከመረብ በማሳረፍ አርሚኒያ ቢሌፌልዶችን እጅ አሰጥቷል። ለአርሚኒያ ቢሌፌልድ አቻ የምታደርገውን ግብ የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ 47ኛ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ጃፓናዊው አማካይ ተጨዋች ማሳያ ኦኩጋዋ ነው።

ትናንት በተደረገ ሌላ ጨዋታ፦ 82ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ተጨዋቹ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተበት ሽቱትጋርት 88ኛው ደቂቃ ላይ ከመሸነፍ የታደገችውን ግብ አስቆጥሯል። ዖማር ማርሙሽ በ25 ሺህ ተመልካች ፊት ከመረብ ያሳረፋት ኳስ ቡድኑን አቻ ስታደርግ ለእሱም በቡንደስሊጋው ለሽቱትጋርት ያስቆጠራት የመጀመሪያ ግቡ ተደርጋ ተመዝግባለታለች።

«ግብ በማስቆጠሬ እና ነጥብ በመያዛችን እጅግ በጣም ነው ደስ ያለኝ። ግቡን ለማስቆጠር ሜዳ ውስጥ የቻልኩትን ሁሉ አድርጌያለሁ። በቡንደስሊጋው የመጀመሪያ ግቤን ለማስቆጠር ይህቺን ቀን ሳልማት ነበር፤ ይኸው ዛሬ ተሳክቷል። ግን ደግሞ ከቡድኔ ጋር ሦስት ነጥብ ይዘን ወጥተን ቢሆን ኖሮ ይበልጥ ደስ ባለኝ ነበር።»

አሰልጣኙ ሜዳ ውስጥ አቅሜን ማሳየት እንዳለብኝ በደንብ መክሮኝ ነበር ያለው ግብጻዊው ዖማር፦ ያን ከቡድኑ ጋር ማድረግ በመቻሉም መደሰቱን ገልጧል። ግብጻዊ ካናዳዊው አጥቂ ከቮልፍስቡርግ በውሰት ወደ ሽቱትጋርት ከመጣ ዛሬ ገና 14ኛ ቀኑ ነው።

የሜዳ ቴኒስ

በሜዳ ቴኒስ ታላቅ የፍጻሜ ውድድር ክብረ ወሰን ለመስበር አልሞ የነበረው ሠርቢያዊው የዓለማችን ድንቅ አትሌት ኖቫክ ጄኮቪች ሽንፈት ገጠመው። እንደ ሮጄር ፌዴሬር እና ራፋ ናዳል በታላቅ የፍጻሜ ውድድሮች ለ20 ጊዜያት አሸናፊ የሆነው ኖቫክ ጄኮቪች በሦስት ዙር ውድድር ነው ትናንት የተሸነፈው። ሩስያዊው ዳኒል ሜድቬዴቭ የ34 ዓመቱ የሜዳ ቴኒስ ኮከብን በተከታታይ ሦስት ዙር በተመሳሳይ ውጤት 4ለ6 አሸንፎታል። ኖቫክ ጄኮቪች ከሦስት ወራት በኋላ በሚከፈተው ሌላኛው ዙር የአውስትራሊያ የፍጻሜ ውድድር ምናልባትም ሕልሙን ዕውን ለማድረግ ይቻለውም ይሆናል። እስከዚያው ድረስ ግን ከተቀናቃኞቹ እኩል በያዘው ነጥብ መቆየቱ አይቀርም።

የመኪና ሽቅድምድም

በጣሊያን የግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን ትናንት ለጥቂት ከከባድ አደጋ ተረፈ። አደጋው የተከሰተው በመጀመሪያው ዙር ላይ የሬድ ቡል አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን በሬድ ቡል የውድድር ተሽከርካሪው የሌዊስ ሐሚልተን መኪናን በጠርዝ በኩል በመግጨቱ ነው። በግጭቱም የማክስ መኪና መርሴዲሱ ላይ ከፍ ብላ በመውጣት የሌዊስ ሐሚልተን የራስ መከላከያ የብረት ቁርን ገጭታለች። ለወትሮው የራስ መከላከያ ማድረግን የሚቃወመው ሌዊስ ሐሚልተን በትናንትናው ዕለት የራስ መከላከያ ማድረጉ ሊደርስበት ይችል ከነበረው ብርቱ አደጋ ታድጎታል። ሁለቱ ተፎካካሪዎች ከሁለት ወራት በፊትም በነበረው የብሪታንያ ግራንድ ፕሪ ሽቅድምድም ተጋጭተው ማክስ ፈርሽታፐን ለሐኪም ቤት ተዳርጎ ነበር። የትናንቱ አደጋ የተከሰተው በአንጻራዊነት ዝግ ባለ ፍጥነት ላይ ቢሆንም የውድድሩ የደኅንነት ባለሞያዎች አደጋውን በተመለከተ ምርመራ እያደረጉ ነው። መሰል አደጋዎች በተደጋጋሚ መከሰታቸው ያሳሰበው የመርሴዲስ ቡድን የፎርሙላ አንድ ውድድሮች ላይ ለውጥ ሊኖር ይገባል ሲል ጥሪ አሰምቷል።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic