የመሰንቆና የክራር ድግስ በጀርመን ከተማ | ባህል | DW | 22.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የመሰንቆና የክራር ድግስ በጀርመን ከተማ

በያዝነዉ የጎርጎረሳዉያኑ 2015 ዓ,ም የመጀመርያ የሙዚቃ ድግሳችን የኢትዮጵያን የአዝማሪ ሙዚቃን በቀጥታ ለማስደመጥ ቀርበናል፤ ሲል ነበር WDR የተሰኘዉ የጀርመኑ የራድዮ ጣብያ ሲያስደምጥ የነበረዉ ዝግጅት።

ባለፈዉ ሳምንት ረቡዕ የጀርመኑ WDR 3 የተሰኘዉ የራድዮ ጣብያ ከጀርመኗ የቢለፌልድ ከተማ በቀጥታ ስርጭት ለሁለት ሰዓት ያህል የክራር የመሰንቆ እና ከበሮ እንዲሁም የኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ብሄር ብሄረሰቦች አልባሳትና ዉዝዋዜን ያካተተ ዉብ የሙዚቃ መድረክ በማዘጋጀት ለተመልካቾች በሰፊ አዳራሽ ለአድማጮቹ ደግሞ በጆሮ አድርሶአል።

በዕለቱ ዝግጅታችን በለፈዉ ሳምንት በሰሜን ምስራቅ ኖርዝ ራይን ዊስት ፋልያ ግዛት ላይ በምትገኘዉ በቢለፊልድ ከተማ የታየዉን የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ ድግስ እናስቃኛለን።

የራድዮ ጣብያችን ካለበት ከቦን ከተማ 220 ኪሎ ሜትር ላይ በምትገኘዉ በቢለፌልድ ከተማ የሚገኘዉ WDR- 3 የተሰኘዉ የጀርመኑ ራድዮ ጣብያ የኢትዮጵያን ጥንታዊ የሙዚቃ መሣርያና ሙዚቃዋን ከመድረክ በቀጥታ ሥርጭት ለሁለት ሰዓታት ለጀርመናዉያን አድማጮች ሊያደርስ በዝግጅት ላይ መሆኑ መነገር የተጀመረዉ ገና ወራቶች ሲቀሩት ነበር። በራድዮና በድረ-ገፆች « የቡና መገኛዋ ፤ የረጅም ርቀት ሯጮቹ መፍለቅያዋ ሃገር የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ጥንታዊዉን የአፍሪቃ የሙዚቃ መሣርያቸዉን ይዘዉ አራት ቅኝታቸዉን ያስተዋዉቁናል የሚል ማስታወቂያ ነበር የቀረበው ።

የኢትዮጵያ ሙዚቃ በምዕራብ አፍሪቃ ወይም በደቡባዊ አፍሪቃ የሚደመጠዉ አይነት ሙዚቃ አይደለም፤ አልያም በዛንዚባር ወይም ደግሞ የዓረብኛም አይነት የሙዚቃ ቅላፄም የለዉም እንደዉ ብቻ በቅኝ ግዛት ሃገር ባህል ያልተበረዘ ኢትዮጵያዊ ሙዚቃ ብቻ ሲሉ ነበር የአድማጮችን ቀልብ አንጠልጥለዉ የከረሙት። ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ቅኝ ያልተገዛች ብቸኛዋ ሃገርም በመሆንዋ ንፁህ የአፍሪቃ ሙዚቃ የሚደመጥባት ሃገር መሆንዋም በዚሁ የሙዚቃ ድግስ ላይ ተነግሮላታል። እጅግ ግዙፍ የሆነዉ አዳራሽ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቷል፤ እንደዉም የመግብያ ትኬት ተሸጦ በማለቁ የተመለሱት ሰዎች ቁጥር ጥቂት እንዳልሆነም ተነግሮአል። በዚሁ አዳራሽ የነበረዉ የኢትዮጵያዊና የኤርትራዊ ቁጥር በአጠቃላይ ቢበዛ ከ 15 አይበልጥም ነበር ። የተቀሩት እድምተኞች ግን ጀርመናዉያን ብቻ ነበሩ። ዝግጅቱ በቀጥታ በራድዮ ስለሚተላለፍ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ሊሆን ሲል ታዳሚዉ በዝያ በተንጣለለ አዳራሽ ገብቶ ቦታ ቦታዉን ይዟል። የራድዮ የስርጭት መስመሩ ወደ ሙዚቃ አዳራሹ ተዛዉሮ እንደተሰጠ በአዳራሹ የሚቀርበዉን ሙዚቃ በማስተርጎም እንዲሁም በራድዮ ለአድማጮች የምሽቱን መድረክ በመምራት ማስተዋወቅ ጀርመናዊትዋ የመድረክ መሪ ንግግሯን ጀመረች።

የዛሬዉ ዝግጅታችን ከመቶ ዓመታት በላይ እድሜ ያለዉን የኢትዮጵያን አዝማሪ ሙዚቃ ነዉ። በመጀመርያዉ ክፍል ዝግጅት በበርሊን ነዋሪ የሆነችዋን የእዉቁ የፒያኖ ተጫዋች የተፈራ መኮንን ልጅ ባለ ክራርዋን ማርታ ተፈራን እናደምጣለን ስትል መቅረፀ ድምፁን አስተላለፈች ለከያኒዋ።

ወጣትዋ የክራር ተጫዋች ማርታ ተፈራ በትዝታ አንቺ ሆዬ አንባሰልና ትዝታ ክራር ቅኝት ታዳሚዉን አስደስታ በደማቅ ጭብጨባ ከመድረክ እንደወረደች በእስራኤል ነዋሪ የሆነዉ ታዋቂዉ ባለመሰንቆ ደጀን ማንችሎት ተተካ በርግጥ በቢለፌልድ ብዙ ኢትዮጵያዉያን ባለመኖራቸዉ በአዳራሹ ድግሱን ለማየት ባይመጡም በጀርመን ያላችሁ ወገኖቼ እንደምን አላችሁ ሲል ነበር ሙዚቃዉን የጀመረዉ።

ጀርመንን ለሁለት የከፈለዉ የበርሊን ግንብን ያፈረሱ፤ በመኪና ሥራቸዉ የሚታወቁና ለዓለም ሰላም ምሳሌዎቹ ሲል ጀርመናዉያኑን አሞገሰ ባለመሰንቆዉ ደጀን ማንችሎት። ድግሱ ሙዚቃ የቀረበበት ብቻ ሳይሆን የጀርመን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ የተንፀባረቀበትም ነበር። የዉጭ ዝርያ ያላቸዉን የሚጠላዉ ፒጊዳ የተባለዉን ስብስብ በመቃወም የተዜመ ሙዚቃም ተደምጦአል።

የባለማሲንቆዉ ደጀን ማንችሎት ዝግጅቱን አጠናቆ ከመድረክ ሲወርድ ጭብጨባዉ የጋለ ነበር።በርካታ የመድረኩ ታዳሚዎች ዜማዉን መዉደዳቸዉን ተናግረዋል ፤ የሙዚቃ አስተማሪ እንደሆኑ የነገሩን ጀርመናዊት ሞኒካ ፊር ደጀንና ማሲንቆን በመተዋወቂ ደስታ ተሰምቶኛል ሲሉ ነበር በመቅረብ ያነጋገሩን፤

« በመሰንቆ ተጫዋቹ በደጀን የሙዚቃ አቀራረብ እጅግ ነዉ የተማረኩት፤ በዘፈኑ ዉስጥ ብዙ መልክቶች ነበሩት። እና ደጀን መልክቱን ከሙዚቃዉ ጋር አቆራኝቶና ህይወት ሰጥቶ ለአድማጩ አድርሶአል። በርግጥ በሙዚቃዉ ዉስጥ ያለዉ ግጥም ሙሉ በሙሉ ባይገባኝም አንዳንድ ቃላቶች ስለገቡኝ ስለምን እያዜመ እንደሆን ተረድቻለሁ። ከልቡ እያዜምም ስለነበር ሰዉነቱ እጁ ሁሉ እየተንቀሳቀስ ነበር። ስለ ፔጊዳ ፤ ስለ ፓሪስ ፤ አሜሪካ፤ሃንቡርግ፤በርሊን፤ብሪመን እያለ ሲያዜም ምን እያዜመ እንደሆነ በሰዉነቱ እንቅስቃሴ ሁሉ ነዉ አድማጮቹ ተመልካቾቹ እንዲረዱት ያደረገዉ፤ ደግሞ ሙዚቃዉ እያሳሳቀ መልክት አድራሽ አይነት መሆኑን ሁሉ በሙዚቃዉ አስረድቶኛል። በዚህም ደጀንን ሲያዜም በማድመጤ ከሁሉ በላይ ደጀንን በመተዋወቄተደስቻለሁ»

ሁለት ተወዛዋዥ አንድ ባለ ክራር አንድ ባለከበሮ እንዲሁም አንዲት ድምፃዊት በአጠቃላይ አምስት አባላትን የያዘዉ «ክራር ኮለክቲቭ» የተሰኘዉና መቀመጫዉን በብሪታንያ ያደረገዉ የኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን የሙዚቃ ድግሱን ካደመቁት መካከል ነበሩ።

የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቡችን ሙዚቃና ዉዝዋዜ እንዲሁም አልባሳትን ለምሽቱ ታዳሚዎች ያሳየዉ የለንደኑ ክራር ኮሌክቲቭ ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን መሪ ወጣት ተመስገን ዘለቀ ቡድኑ የኢትጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ጭፈራና አልባሳት በተለይ ለምዕራቡ ዓለም እየዞረ ማስተዋወቅ ከጀመረ ወደ አስር ዓመታት እንደሆነዉ ገልፆልናል። የቡድኑ አባላት በስደት ዓለም ሙዚቃን እንደ ዋና ስራቸዉ ባይዙትም ሙዚቃ እንዲሰሩ በታዘዙ ጊዜ ሰዓታቸዉን አስማምተዉ ሙዚቃን በተለያዩ የምዕራብ ሃገራት እንደሚያሳዩ ገልፆአል። በዚህም ቡድኑ ከበርሊን እስከ ኒዮርክ ከአዉስትራልያ እስከ ህንድ ፤ ከካናዳ እስከ አየርላንድ መጓዙን ገልጾልናል።

የክራር ኮሌክቲቭ ቡድን ተወዛዋዥ ወጣት ተመስገን መለሰ በተለይ ጡሩምባ እየነፋ ወደ መድረክ ሲገባ ተመልካችን አስደምሞ ነበር፤ በዉዝዋዜዉና የተለያዩ አልባሳትን ከዳንስ አጋሩ ጋር አድርገዉ በመድረክ ማሳየታቸዉ፤ የኢትዮጵያ ባህላዊ ዳንስም ሆነ ልብስ ዉብ መሆኑን አስመስክረዋል።

በጀርመኑ የራድዮ ጣብያ WDR 3 የቢለፊልዱ የባህል መድረክ ዋና አዘጋጅ ዶክተር ቨርነር ፉር በኢትዮጵያዉያኑ ሙዚቃና መደነቃቸዉን ተናግረዋል። «በጣም አስደናቂ ዝግጅት ነበር። የኢትዮጵያ ባህላዊ ዳንስ እና ሙዚቃ እንዲህ ነዉ ብዬ ገምቼ አላዉቅም ነበር። ለመጀመርያ ግዜ ዛሬ ማየቴ ነዉ። ለነገሩ ይህ የኛ የባህላዊ ሙዚቃ ስርጭት መረሃ-ግብራችንም እንዲህ አይነቶቹን የማይታወቁ ማኅበረሰብ ሙዚቃና ዉዝዋዜን ለህብረተሰቡ ማስተዋወቅ ነዉ። የኢትዮጵያ ሙዚቃ በምዕራብ አፍሪቃ የሚደመጠዉ ዓይነት ሙዚቃ አልያም በደቡባዊ አፍሪቃ የሚታየዉ ዓይነት ሙዚቃ ወይም ደግሞ በምስራቅ አፍሪቃ ለምሳሌ በዛንዚባር የሚታየዉ አይነት የዓረብ ሙዚቃ ዓይነት ሳይሆን ኢትዮጵያ ያላት ባህላዊ የሙዚቃ እና የሙዚቃ መሳርያዎችዋ ለየት ያሉ ናቸዉ። በዚህም ብዙዎች ጀርመናዉያን ለማየት ለማወቅ ጉጉት ስለነበራቸዉ ነዉ ኢትዮጵያዉያን ሙዚቀኞችን የጋበዝነዉ።»

በቢሊፊልድ ከተማ የሚጘኑ ነዋሪዎች ኢትዮጵያያን የባህል ሙዚቃ ባህላዊዉን ዉዝዋዜና የተለያዩ አልባሳት በመተዋወቃቸዉ መደነቃቸዉን መደሰታቸዉን ከዝግጅቱ በኋላ ይህን መድረክ ላዘጋጁት እንዲሁም ለከያንያኑ ገልፀዋል ። ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic