የመርዛማ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር በኢትዮጵያ | ኢትዮጵያ | DW | 12.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የመርዛማ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ  በአዳዲስ መንገዶች ግንባታዎች ሂደት ጥንቃቄ የጎደለው የመርዛማ ቆሻሻዎች አወጋገድ የህጻናት  የሞት መጠን እንዲጨምር አድርጓል  ሲል አንድ ጥናት አመለከተ።የለንደን ኩይንስ ሜሪ ዩንቨርሲቲና  የደበሊን ትሪኒቲ ዩንቨርሲቲ ባደረጉት ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባን ከጎረቤት ሀገራት ጋር  በሚያገናኙ ታላላቅ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:15
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:15 ደቂቃ

«የመርዛማ ቆሻሻ አወጋገድ ቁጥጥር ያስፈልጋል»


 የመንገድ  ግንባታዎች ወቅት የሚደረገዉ  ህግን ያልተከተለ የመርዛማ ቆሻሻዎች አወጋገድ  በህጻናት  ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አለዉ። ይህም  የህፃናት የሞት መጠን እንዲጨምር ያደርጋል ሲል ባለፈው ወር አጋማሽ ይፋ የሆነዉ ጥናት ይፋ  አድርጓል።

የኩይንስ ዩንቨርሲቲ የኢኮኖሚ መምህር ደክተር ካታሪና ጆናዮሊ ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት በግንባታ ወቅት በሚደረግ የመርዛማ ቆሻሻወች  አወጋገድ  ሳቢያ የሚከሰተዉ የበሽታና የሞት መጠን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በልማት ወደ ኋላ በቀሩ ሀገራት ከፍተኛ ነዉ።በጎርጎሮሳዉያኑ በ2000 ፣በ2005 እና በ2010 በተካሄዱ የመንገድ ግንባታዎች ላይ ያተኮሩ መረጃዎችን በመሰብሰብና  በመተንተን በመንገድ ግንባታ ወቅት ለመርዛማ ንጥረ ነገሮች መጋለጥ ከበሽታና ከሞት መጠን ጋር ያለዉን ትስስር  ለመረዳት እንደቻሉ ተመራማሪዋ አስረድተዋል።
 «በመጀመሪያ ጥናታችን ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገነቡ መንገዶች ከህፃናት ሞት ጋር ያለዉን ትስስር በጠቅላላ የሚመለከት አይደለም።እኛ በጥናቱ ያየነዉ ትልቅ ችግር አዲስ አበባን ከጅቡቲና ከሶማሊያ ጋር በሚያገናኙ መንገዶችን ላይ ብቻ ነዉ ።እናም እነዚህ የመንገድ ግንባታወች  በህፃናት ሞት ላይ ያለቸዉን ተፅዕኖ በጥናታችን ተገንዝበናል። የመርዛማ ቆሻሻዎች አወጋገድ ችግርንም አይተናል።»

ከ2005 እስከ 2011 በሁለት ዙር በተሰበሰበ የስነ ህዝብና የጤና መረጃች  መሰረት የተካሄደ ነዉ በተባለዉ በዚህ  ጥናት በአዋቂዎችና በልጆች የጤና እክል ሲያስከትል የጨቅላ ህፃናትን ሞት ደግሞ እንዲጨምር ያደርጋል ተብሏል። በአዳዲስ የመንገድ ግንባታ ጣቢያዎች በ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት የምትገኝ አንዲት እናት የምትወልደዉ ህፃን የመሞት እድሉ 3 በመቶ ይጨምራልም ተብሏል።ከ 5 አመት እድሜ በታች ያሉ ህጻናትም ልጆችም በደም ዉስጥ የሚገኝን የሂሞግሎቢን መጠን በመቀነስ ለከፍተኛ የደም ማነስ በሽታ  እንደሚያጋልጥ በጥናቱ ተጠቅሷል። እንደ ጥናቱ  የወባ በሽታ፣ ኤች አይቪ ኤድስና የሳንባ ነቀርሳ  በሽታዎች በአንድ ላይ ሆነዉ በድሃ ሀገራት ከሚያደርሱት የጉዳት መጠን ጋር ሲነፃጸር  በ 3 እጥፍ  ብልጫ አለዉ።በዚህም ሳቢያ መርዛማ  ነገሮችን በህገ ወጥ መንገድ ማስወገድ በህብረተሰብ ላይ ከሚያደርሰዉ ጉዳት አንፃር ከአደገኛ ተላላፊ ወንጀሎች አንዱ ነዉ ሲሉ ተመራማሪወቹ አስምረዉበታል።በአፍሪካ የመሰረተ ልማት ግንባታ በከፍተኛ ደረጃ የዉጭ ባለሀብቶችን በመሳብ ላይ ቢሆንም  ከግንባዎቹ ጋር ተያይዞ የአካባቢዉን ህብረተሰብ የሚጎዱ ህገ ወጥ የመርዛማ  ቆሻሻዎች አወጋገድን ለመከላከል ተገቢ የቁጥጥርና  የጥንቃቄ  ስራ ያስፈልጋል  ሲሉ ተመራማሪዋ ይመክራሉ።


«በጥናቱ ማmቃለያ እንዳስቀመጥነዉ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ  በየትኛዉም አይነት የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራ ላይ ቁጥጥር ያስፈልጋል። አሁን መንገዶቹን ብቻ ነዉ ያየነዉ ነገር ግን ይህ የመርዛማ ቆሻሻዎች አወጋገድ ችግር ፤በህንፃ ግንባታወች፣በግድቦች፣በድልድይ ስራ፣በባቡር መንገዶችና በሌሎች መሰረተ ልማት ስራወች ላይም ሊከሰት ይችላል።ስለዚህ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ የቁጥጥርና የክትትል ስራ ያስፈልጋል።» 

ጥናቱ አዲስ አበባን  ከጅቡቲ ከሶማሊያ ከኤርትራ ከሱዳን ና ኬንያ ጋር በሚያስተሳስሯት መንገዶች ላይ የተደረገ ቢሆንም ችግሩ ግን ሀገሪቱን  ከጅቡቲና ከሶማሊያ ጋር ከሚያገናኙ ዋና መንገዶች ጋር ብቻ የተያያዘ መሆኑ ተመልክቷል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአደገኛ ዕፆችና  ብክለት ዝዉዉር ጽ/ቤት  በጎርጎሮሳዊዉ 2009 ባወጣዉ መረጃ መሰረት ምስራቅ አፍሪካ ከመርዛማ ንጥረ ነገሮች ብክለት ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ስጋት ስር የሚገኝ  ቀጠና ሆኖ ተመዝግቧል። በጥናቱን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንን አስተያየት ለማካተት  በተደጋጋሚ ስልክ ብንደዉልም ሊሳካልን አልቻለም።

 

ፀሐይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic