1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመሬት መንቀጥቀጥ

ሰኞ፣ መስከረም 27 2017

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጂኦፊዚክስ እና ስፔስ ሳይንስ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ በአፋር ክልል ፈንታሌ ተራራ ላይ በ4.9 ሬክተር ስኬል የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጡ፤ “ለነዋሪዎች አስጊ አይደለም” ሲሉ ትናንት ምሽት ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ገልጸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4lVmR
Äthiopien Dire Dawa Eigentumswohnungen
ምስል Mesay Teklu/DW

የመሬት መንቀጥቀጥ

በትናንት ምሽት አፋር ክልል ውስጥ በሚገኘው ፈንታሌ ተራራ ያጋጠመውን የመሬት መንቀጥቀጥ ተከተትሎ አዲስ አበባ ድረስ ዘልቆ በተሰማው ንዝረት በመዲናዋ በተለይም የጋራ መኖሪያ ህንጻዎች ውስጥ ንዝረቱ ከፍተኛ ድንጋጤን በመፍጠሩ በርካታ ነዋሪዎች ቤተሰቦቻቸውን ይዘው በመውረድ ከህንጻዎች ራቅ ብለው ሲቀመጡ ታይተዋል፡፡     
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦ ፊዝክስ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋምም በመረጃው ይህንኑን አረጋግጧል። የአሜሪካ መንግሥት ኦፊሴላዊ የመሬት መንቀጥቀጥ ድረ-ገፅም መታሃራ አካባቢ መካከለኛ የሚባል የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን አስታውቆ፤ ይህም 10 ኪሎ ሜትር ግድም ጥልቀት የነበረው ነው ብሏል። የተከሰተው መንቀጥቀጥ ንዝረቱ ከ380 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ መሰማቱንም በድረ ገጹ አሳውቋል፡፡

ርዕደ መሬት እና ሳይንሳዊ እውነታዎቹ
የአደጋው መጠንና ስጋቱ
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ከተማ ነዋሪም ከሰሞኑ በተደጋጋሚ ሲከሰት ከነበረው የመሬት መንቀጥቀጡ የሚያስከትለው ንዝረት የትናት ምሽቱ አስደንጋጭና ከባድ ነበር ነው ያሉት፡፡ በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ ቀበሌ የመሬት መሰነጣተቅናየቤቶች መፍረስም አደጋ መስተዋሉን ጠቁመዋል፡፡ “በከተማው እንቅስቃሴው ከባድ ቢሆንም ጉዳት አላደረሰም፡፡ ይህም በተደጋጋሚ ስሜቱን የምንሰማ ሲሆን 20 ቀናት ግድም ሆኖታልም” ያሉት የአዋሽ ከተማ ነዋሪ የትንንት ምሽቱ የከፋ እና ስሜቱን ከሌላው ጊዜ ረዘም ብሎ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ ከከተማው ውጪ አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ውስጥ ሳቡሬ በሚባል ቀበሌ የመሬት መሰነጣጠቅና የቤቶች ምፍረስ ጉዳቶችም መከሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በተለያዩ ሃገራት የሚታየው የተፈጥሮ አደጋ የብዙዎች ስጋት ሆኗል።
በዚያው አቅራቢያ የመሬት መንቀጥቀጡ ከተከሰተበት ስፍራ 30 ኪ.ሜ ላይ በምገኘው የኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን መታሃራ ከተማ ውስጥም የተሰማው የንዝረት መጠን ከባድ እንደ ነበር የመታሃራ ከተማ ነዋሪ አስረድተዋል፡፡ “ማታ መታሃራ ሙሉን ከባድ የመሬት እንቅስቃሴ ስለነበር ድንጋጤው ከባድ ነው” ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጂኦፊዚክስ እና ስፔስ ሳይንስ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ በአፋር ክልል ፈንታሌ ተራራ ላይ በ4.9 ሬክተር ስኬል የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጡ፤ “ለነዋሪዎች አስጊ አይደለም” ሲሉ ትናንት ምሽት ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ገልጸዋል፡፡ ባለሙያው የአዋሽ ፈንታሌው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት ስሜት አዲስ አበባ ድረስ መሰማቱን አረጋግጠዋል።
በመሬት መንቀጥቀጡ የደረሰ ጉዳትና የነዋሪዎች ድንጋጤ

የመሬት መንቀጥቀጥ በሰሜን ኢትዮጵያ
የመታሃራ ከተማ ነዋሪው አስተያየት ሰጪ የመሬት መንቀጥቀጡ በተከሰተበት አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ ቀበሌ ጉዳት ቢደርስም በመታሃራ ከተማ እቃዎችን የጣለና ጣራዎችን ያንቃቃ ከባድ የንዝረት ስሜት ቢፈጥርም የከፋ ጉዳት ግን አልደረሰም ነው ያሉት፡፡ “የመሬት መሰነጣጠቅና ግርግዳዎች መፍረስን ጨምሮ ከባድ ጉዳት የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጡ በተከሰተበት ተራራ አከባቢ ነው” ያሉት አስተያየት ሰጪው በመታሃራ እሁድ ምሽቱን ከሆቴሎች እና መኖሪያ ቤቶች ሰዎች ሸሽተው መውጣታቸውንና ጣራዎች በመንቃቃት እቃዎች መውደቃቸውን ገልጸዋል፡፡
የመሬት ንዝረቱ በአዳማም መሰማቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ “ቀበሌ 09 105 ወንጂ ማዞሪያ የሚባል የጋራ መኖሪያ ቤቶች አከባቢ ንዝረት ነበር” ብለዋል፡፡

ርዕደ መሬት በዳውሮ ዞን
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳት አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ንጋቱ ማሞ በትናንት ምሽት በተሰማው ንዝረት አዲስ አበባ ውስጥ በተለይም የጋራ መኖሪያ ቤቶች አከባቢ ከሚኖሩ በርካታ ነዋሪዎች በመጣው ስጋት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች እስከማሰማራት ቢደረስም ያጋጠመው አደጋ ግን አለመመዝገቡን ተናግረዋል፡፡ “በተለይም የጋራ መኖሪያ ቤቶች አከባቢ ይመስለኛል ጉዳቱ ያጋጠማቸው፤ ነገር ግን እስካሁን ደርሷል የተባለ ጉዳት እኛ ጋር አልመጣም” ነው ያሉት፡፡
ሥዩም ገቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ