1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመሬት መንቀጥቀጥና የአዲስ አበባ ሕንጻዎች

ረቡዕ፣ ጥቅምት 13 2017

አዲስ አበባ የመሬት መንቀጥቀጥ ያሰጋታል ከሚባሉት ከተሞች መካከል አንዷ ናት። ባለፉት ሁለት ሳምንት ብቻ በአዋሽ አካባቢ የተከሰቱትን ሦስት የመሬት መንቀጥቀጦች ተከትሎ የመዲናቱ መናጥ በከተማዋ ላሉት ትላልቅ ሕንፃዎች ስጋት ሊሆንባቸው እንደሚችል ይነገራል።

https://p.dw.com/p/4m9YE
አዲስ አበባ
ሕንጻዎቿ እየበረከቱና ከፍታቸው እየጨመረ የሄደባት አዲስ አበባ ምስል Joerg Boethling/IMAGO

የመሬት መንቀጥቀጥ

የርዕደ መሬት በከፍተኛ ደረጃ ሊያጠቃቸው ከሚችሉ እንደ አዋሽ ያሉ ቦታዎች እና ለመሬት መንቀጥቀጡ ቅርበት ያላቸው እንደ አዲስ አበባ አይነት ከተሞች ላይ የተገነቡ ሕንፃዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ካልሆኑ በስተቀር ለአደጋ እጅግ ተጋላጭ ናቸው። በመሆኑም በእነዚህ አካባቢዎች የሚሠሩ ሕንፃዎች ይህንን የተፈጥሮ ሀይል መቋቋም እንዲችሉ የተቀመጠውን የሕንፃ አሠራር ሕግ እና ደንብ ማሟላት ይኖርባቸዋል።

በርግጥ ተፈጥሮ ሀይል የሚያስከትለው የመሪት መንቀጥቀጥም ሆነ መናጥ ጫና መጠን እንደ የአካባቢው ይለያያል። አንድ ሕንፃ ከመገንባቱ በፊት አካባቢው በምን ያህል ሀይል እና መጠን ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭ ነው የሚለው ከታወቀ በኋላ ነው ሕንፃው የሚሰራበት የቁሳቁስ ዓይነት እና መጠን የሚወሰነው ሲሉ ዶቼቪሌ ያነጋገራቸው የሲቪል ምህንድስና ባለሙያው ፕሮፊሰር አስራት ወርቁ ይናገራሉ።  

እሳቸው እንደሚሉትም ሕንፃ ሢሠራ ማነኛውም ዲዛይን በሌላ ሁለተኛ እኛ ሦስተኛ ወገን ይታያል። ለዚህ ምክንያቱ ሕንፃው ችገር እንዳይፈጥር ነው። ይህንን ደግሞ የሚመለከተው አካል ማረጋገጥ ይኖርበታል።

አዋሽ ፈንታሌ ላይ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥሳቢያ በ130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው አዲስ አበባ ውስጥ የተከሰተው ተደጋጋሚ የመሬት መናጥን ተከትሎ አንዳንድ ነዋሪዎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች «ቤትታችን ተሰነጠቀ» ማለታቸው የመዲናይቱ ሕንፃዎችን ጥራት ጥያቄ ውስጥ አይከተውም ወይ በማለት የተጠየቁት መሀንዲሱ ፤ በሩቅ ቦታ ላይ በአነስተኛ መጠን በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ እንደተባለው ሕንጻዎች ጉዳት ደርሶባቸው ከሆነ ጉዳዩ እንደሚያሳስባቸው ነው ያመለከቱት። ሆኖም ግን ከንዝረቱ መጠን ዝቅተኛነት የተነሳ በአዲስ አበባ ሕንጻዎች ላይ ጉዳት ይደርሳል ለማለት እንደሚከብዳቸውም አመልክተው፤ ሆኖም ግን ከዚህ ከፍ ያለ መንቀጥቀጥ ቢከሰት ችግር አይደርስም ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል።

እስካሁን በሠሩባቸው ወቅቶች ከመሬት መንቀጥቀጥ ጋር ተያይዞ ችግር የተከሰተበት ሕንፃ የለም ያሉት የሲቪል ምህንድስና ባለሙያው ፕሮፊሰር አስራት፣ ነገር ግን አንድ ሕንፃ ተውጠናቆ ለአገልግሎት ከመዋሉ በፊት የሕንፃ አሠራር ሕግ እና ደንብን አሟልቶ መጠናቀቁ መፈተሽ እንደሚኖርበት አመልክተዋል።

ሃና ደምሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ