የመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የኪይቭ ጉብኝት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 23.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የኪይቭ ጉብኝት

ዛሬ ወደ ኪይቭ የተጓዙት የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፕሮሼንኮ ጋር ተገናኝተው ተወያዩ። ይህ በእንዲህ እንዳለ የርዳታ ቁሳቁስ የጫኑት የሩስያ ከባድ ተሽከርካሪዎች በሙሉ ከምስራቅ ዩክሬይን መዉጣታቸዉ ተነገረ።

ዛሬ ወደ ኪይቭ የተጓዙት የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፕሮሼንኮ ጋር ተገናኝተው ተወያዩ። ሜርክል ወደ ኪዬቭ የተጓዙት በምስራቅ ዩክሬን እና ሩስያ ስላለዉ ከፍተኛ ዉጥረት እና ግጭት አንድ የመፍትሄ ሃሳብ ላይ ለመድረስ ነው። መራሂተ መንግስቷ፤ የዩክሬይን ቀዉስ ከተቀሰቀሰ ወደህ ወደ ኪይቭ ሲጓዙ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ መሆኑ ነዉ። ዩክሬይን ከፍተኛ ችግር ዉስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት የመራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ወደ ኪይቭ ማምራት፤ ለሰላም ማስፈኑ ጥረት አንድ ተስፋ እንደሆነም ተመልክቶአል። የጀርመን መንግሥት ዋንኛ ዓላማ እንደ መጀመርያዉ ግዜ የሰላም ጥረት ሁሉ ፤ የዩክሬይን መንግሥት ወታደሮች እና መፍቀረ ሩስያኑ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርሱ ጥረት ማድረግ ነዉ ። መራሂተ መንግሥቷ ዛሬ ማታ ወደ ጀርመን ከመመለሳቸዉ በፊት ከዩክሬኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አርሴናይ ያዙንቺክ ጋርም እንደሚገኛኙ ታዉቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አወዛጋቢ እንደሆኑ የተነገረላቸዉ፤ የርዳታ ቁሳቁስ የጫኑት የሩስያ ከባድ ተሽከርካሪዎች ከምስራቅ ዩክሬይን መዉጣታቸዉ ተነገረ። የአዉሮጳ የደህንነት እና የትብብር ድርጅት እንዳስታወቀዉ፤ ከሩስያ ወደ ዩክሬይን ገብተዉ የነበሩት ሁሉም ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ሩስያ ተመልሰዋል። የሩስያዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት በበኩሉ ተሽከርካሪዎቹ የሰብዓዊ ርዳታ ለማድረስ የታለመበት ቦታ ላይ ደርሰዉ ጭነቱን አራግፈዋል ሲል ገልጿል ። ሩስያ ትናንት ዓርብ ያለ ዩክሬይን ፍቃድ ወደ 280 የሚጠጉት የጭነት ተሽከርካሪዎችን ድንበር ተሻግራ ወደ ዩክሬይን ማስገባትዋ ይታወቃል። ይህን የሩስያ ርምጃ፤ ከዩክሬንን ጨምሮ ከአዉሮጳዉ ኅብረት፤ ከተመድ እንዲሁም ከዩኤስ አሜሪካ ከፍተኛ ነቀፌታን ቀስቅሶ ነበር። የዩክሬንን ድንበር ዘልቀዉ የገቡት ሩስያ ከባድ ተሽከርካሪዎች ፤ ለመፍቀሬ ሩስያኑ፤ የጦር መሳርያ በማጓጓዝ ላይ ናቸዉ ሲል ኪይቭ ላይ የሚገኘዉ የዩክሬይኑ መንግሥት፤ ጥርጣሬዉን ይገልፃል። ሩስያ በበኩልዋ በሉጋንስ በጦርነቱ ለተጎዱ ነዋሪዎች የሰብዓዊ ርዳታ ማድረስዋን ነዉ የገለፀችዉ ።

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ