የመሐመድ ሙርሲ ሞት እና የግብጽ ፖለቲካ | አፍሪቃ | DW | 18.06.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የመሐመድ ሙርሲ ሞት እና የግብጽ ፖለቲካ

የመሐመድ ሙርሲ ድንገተኛ ሞት የሙስሊም ወንድማማቾች ንቅናቄ ፍልስፍና አቀንቃኞች ከፖለቲካ እንዲርቁ አሊያም የበለጠ ተጠናክረው ሥርዓቱን ለመለወጥ፣ ለዓላማው ለመታገል ቁርጠኛ እንዲሆኑ ሊያደርጋቸው እንደሚችል በአንካራ የማኅበራዊ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት የትምህርት ማዕከል በመምህርነት የሚያገለግሉት ዶክተር ሙከርም ሚፍታህ ይናገራሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:20

የመሐመድ ሙርሲ ሞት እና የግብጽ ፖለቲካ

ትናንት በድንገት ሕይወታቸው ያለፈው የቀድሞው የግብፅ ፕሬዝዳንት መሐመድ ሙርሲ ሥርዓተ-ቀብር ተፈጽሟል። በካይሮ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ ሳሉ ድንገት ተዝለፍልፈው ከወደቁ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የሙርሲ ሥርዓተ-ቀብር ሲፈጸም ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ ነበር። የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቤተሰቦች በካይሮ ከተማ የቶራ እስር ቤት ውስጥ በሚገኝ መስጊድ የተደረገውን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት እና ሥርዓተ ቀብራቸውን መታደማቸውን ከሙርሲ ጠበቆች አንዱ የሆኑት አብዱል ሙነይም አብደል ማቅሱድ ተናግረዋል።

የመሐመድ ሙርሲ ልጅ አሕመድ እንደተናገሩት የአገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሻርቂያ ግዛት በሚገኘው የትውልድ መንደራቸው በሚገኝ የቤተሰቦቻቸው የመቃብር ሥፍራ እንዳያርፉ ክልከላ አድርገዋል። አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው ጋዜጠኞች የቀብር ሥነ-ሥርዓቱን እንዳይከታተሉ ፎቶ ግራፍም እንዳያነሱ የጸጥታ አስከባሪዎች ክልከላ አድርገዋል። ጋዜጠኞች ወደ ሙርሲ የትውልድ ከተማ መጓዝም ተከልክለዋል። የ67 አመቱ መሐመድ ሙርሲ አሁን በሕግ የታገደውን የሙስሊም ወንድማማቾች የፖለቲካ ንቅናቄ በመወከል በጎርጎሮሳዊው 2012 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ አሸንፈው የግብፅ ፕሬዝዳንት ሆነው ነበር። ከአንድ አመት መሪነት በኋላ በአገሪቱ ጦር ከሥልጣናቸው የወረዱት ሙርሲ በእስር ላይ በነበሩባቸው አመታት የስኳር ሕመም ነበረባቸው። በተደጋጋሚ በጠባብ ክፍል ታስረው እንዲቆዩ የተደረጉት ሙርሲ ከጎብኚዎቻቸው እንዳይገናኙ ክልከላ ተደርጎባቸው ቆይቷል። ሙስሊም ወንድማማቾች ንቅናቄ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሙርሲን ለአመታት በአስከፊ ሁኔታ በእስር ላይ በማቆየት "ገድሏቸዋል" ሲል ከሷል።
ለመሆኑ የሙርሲ ድንገተኛ ሞት በግብፅ ፖለቲካ ላይ ምን ተፅዕኖ ያሳድራል? እሸቴ በቀለ በአንካራ የማኅበራዊ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት የትምህርት ማዕከል በመምህርነት የሚያገለግሉት ዶክተር ሙከርም ሚፍታህን በጉዳዩ ላይ በስልክ አነጋግሯቸዋል።

ቃለ-ምልልሱን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ 
 

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ 

Audios and videos on the topic