የመልካሳ የምርምር ማዕከል የ50 ዓመት ጉዞ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 28.08.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የመልካሳ የምርምር ማዕከል የ50 ዓመት ጉዞ

በኢትዮጵያ በግብርና ምርምር ላይ ከተሰማሩ ተቋማት አንዱ የሆነው የመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የወርቅ ኢዩቤልዩ በዓሉን ከማክሰኞ ጀምሮ በማክበር ላይ ይገኛል። ማዕከሉ ለህብረተሰቡ ጉልህ የምርምር ውጤቶች ማበርከቱን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከማዕከሉ የወጡት የቦሎቄ እና ማሽላ ዝርያዎች ለብዙ ተጠቃሚዎች መዳረሳቸውንም ይገልጻሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:44

የመልካሳ የምርምር ማዕከል የ50 ዓመት ጉዞ

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ስር ካሉ 20 የምርምር ማዕከላት መካከል አንደኛው የተመሰረተው የአዋሽ ወንዝን ተንተርሶ ነው። ይህ የምርምር ማዕከል የዛሬ 50 ዓመት ስራውን አሀዱ ያለው አምስት ሄክታር በማይበልጥ ቦታ ላይ ነበር። የአካባቢውን መጠሪያ ተውሶ መልካሳ የሚል ስያሜን የያዘው ማዕከሉ ቀድመውት ከተመሰረቱ አምስት የግብርና ምርምር ማዕከላት በተለየ ዘርፍ ላይ እንዲያተኩር ተደረገ።

በአጼ ኃይለስላሴ የስልጣን ዘመን የተመሰረቱት እኒያ የምርምር ማዕከላት በወረር፣ ባኮ፣ ሆለታ፣ ደብረዘይት እና ጅማ ላይ የተቋቋሙ ነበሩ። የወረሩ በጥጥ እና በቆላ ቅባት እህሎች፣ የባኮው በተትረፈረፈ የበቆሎ ምርት፣ የሆለታው ደግሞ ለደጋማው የሀገሪቱ ክፍል የሚሆኑ የሰብል እና የእንስሳት ዝርያዎች በማውጣት የታወቁ ናቸው። 

በዚያን ጊዜ የግብርና ኮሌጅ ከነበረው ከዓለማያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ጋር የተቆራኘው የደብረዘይቱ የምርምር ማዕከል በጤፍ፣ በዳቦ ስንዴ፣ በሽንብራ እና ምስር ዝርያዎች ስሙ የገነነ ነው። የጅማ ግብርና ኮሌጅ አካል የነበረው የጅማ የግብርና ምርምር ማዕከልም በቡና ምርምር ስሙን ተክሏል። ከአዳማ ከተማ 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለው መልካሳ የግብርና ምርምር ማዕከል ሲቋቋም ምንን ታሳቢ አድርጎ ነበር? በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዮት የዕውቀት ማኔጅመንት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ አበበ ቅሩብ ምላሽ አላቸው። 

ከመዲናይቱ አዲስ አበባ 117 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአነስተኛ ስፍራ ስራውን የጀመረው የመልካሳ የግብርና ምርምር ማዕከል አሁን በ275 ሄክታር ላይ ተሰንራፍቷል። በአምስት ሰራተኞች ስራውን የጀመረው የምርምር ማዕከሉ አሁን በውስጡ የያዘው የሰለጠነ የሰው ኃይል ብቻ 160 ደርሷል። ማዕከሉ ሲጠነሰስ የጀመረውን የአትክልት ልማት ምርምር አሁንም ቀጥሎበታል። የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር በድሩ በሺር በቅርብ ዓመታትም በዚህ ዘርፍ ለህብረተሰቡ ያደረሳቸው የምርምር ውጤቶች እንዳሉ ይናገራሉ። 

የመልካሳ የግብርና ምርምር ማዕከል በተለያዩ የሰብል እና ጥርጣሬ ዝርያዎች ላይም ምርምሮች ሲያከናውን ቆይቷል። ለቆላማ እና ዝናብ አጥር ለሚባሉ አካባቢዎች የሚስማሙ በምርምር ያወጣቸው ዝርያዎቹ በአርሶ አደሮች ዘንድ ተወዳጅ መሆናቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከማዕከሉ የወጡ የማሽላ የምርምር ውጤቶች በቆላማ እና ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ነባር ዝርያዎችን ሁሉ እስከመተካት መድረሳቸውን በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት አቶ አበበ ይገልጻሉ። የምርምር ማዕከሉ በቦሎቄ ዝርያዎቹም ላቅ ያለ ውጤት ማስመዝገቡን ባለሙያው ያስረዳሉ። የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር በድሩ ይህንኑ ያረጋግጣሉ። 

በዚህ ሳምንት የወርቅ ኢዬቤልዩን እያከበረ ያለው የመልካሳ የግብርና ምርምር ማዕከል ከጥቂት ዓመታት በፊት በቦሎቄ እና ማሽላ የምርምር ውጤቶቹ ከቀድሞው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የወርቅ ሽልማት ተበርክቶለታል። የጥራጥሬ እና ሰብል ዝርያዎቹ ሽልማት ያገኙት “በአርሶ አደሮች ምርት ላይ ምን ያህል በጎ ተጽዕኖ አምጥተዋል” የሚለው በባለሙያዎች ተፈትሾ እንደሆነ ዶ/ር በድሩ ያብራራሉ። 

አንድን አዲስ የአትክልት፣ የሰብል አሊያም የጥርጣሬ ዝርያ ለማውጣት የሚፈጀው የምርምር ጊዜ ታዲያ ቀላል አይደለም። “እስከ 10 ዓመት ድረስ የሚወስዱ ምርምሮች ይኖራሉ” የሚሉት ዶ/ር በድሩ አማካይ የምርምር ጊዜያት ግን ከአምስት እስከ ሰባት ዓመታት እንደሆነ ይገልጻሉ። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከአንድ የምርምር ውጤት በላይ እንደማያወጡ የሚገልጹት የማዕከሉ ዳይሬክተር ምክንያቱን እንዲህ ያስረዳሉ።

እንደ ዶ/ር በድሩ ገለጻ ከአንድ በላይ የምርምር ዝርያ ማውጣቱ ዋናው ጥያቄ ሊሆን አይገባም። ይልቁንም መታየት ያለበት “የወጣው ምን ያህል ጥቅም ላይ ይውላል የሚለው ነው” ይላሉ። በእነርሱ የምርምር ማዕከል በኩል የሚወጡ አዳዲስ ዝርያዎችን እንደሚፈለገው ለአርሶ አደሩ ተዳርሶ እንደው  ሲጠየቁ “እንደተፈለገው አልደረሰም፤ አይደርስምም” ሲሉ ምላሽ ይሰጣሉ። 

“ይህን ችግር ለመፍታት ብዙ ጊዜ ተሞክሯል” የሚሉት ዶ/ር በድሩ “የምርምር ውጤቶችን አባዝቶ ለህብረተሰቡ ማድረስ ላይ አሁንም ችግር አለ” ይላሉ። ኢትዮጵያ በፌደራል ደረጃ 20፣ በክልሎች ደግሞ ከ60 የሚልቁ የግብርና ምርምር ማዕከላትን ይዛ የህዝቧን የምግብ እጥረት ማቃለል የሚችሉ የምርምር ውጤቶችን በስፋት ማዳረስ ከተሳናት እንደ መልካሳ ያሉ ማዕከላት ታዲያ ውጤታማነታቸው ምኑ ላይ ነው? የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ባለሙያው አቶ አበበ “ችግሩ የምርምር ማዕከላቱ ጋር አይደለም” ባይ ናቸው። 

ሙሉ መሰናዶውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ 

Audios and videos on the topic