የመልካም አስተዳደር ሽልማት ለናሚቢያ ፕሬዚደንት | አፍሪቃ | DW | 03.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የመልካም አስተዳደር ሽልማት ለናሚቢያ ፕሬዚደንት

የሞ ኢብራሂም ድርጅት የመልካም አስተዳደር ሽልማቱን ትናንት እንደገና ለአንድ አፍሪቃዊ መሪ ሰጠ። የድርጅቱ ሽልማት ሰጪ ኮሚቴ እንዳስታወቀው፣ ዘንድሮ ለዚሁ ሽልማት የበቁት ተሰናባቹ የናሚቢያ ፕሬዚደንት ሂፊኬፑንዬ ፖሀምባ ናቸው።

የሞ ኢብራሂም ድርጅት በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሥልጣን በመያዝ መልካም አስተዳደርን ላራመዱ እና የሥልጣን ዘመናቸው ሲያበቃም ከሥልጣን ለወረዱ አፍሪቃውያን መሪዎች ሽልማት መስጠት የጀመረው እአአ በ 2007 ዓም ነው። ለዚሁ የድርጅቱ የመልካም አስተዳደር ሽልማት በዕጩነት ሊቀርቡ የሚችሉ የቀድሞ አፍሪቃውያን መሪዎች ግን በአህጉሩ በቀላሉ እንደማይገኙ ድርጅቱ ካለፉት ዓመታት ተሞክሮው በመነሳት ገልጾዋል። ምክንያቱም ፣ ይላል ድርጅቱ፣ ብዙዎቹ በአገሮቻቸው ስርዓት ዴሞክራሲን ከመትከል፣ የሕግ የበላይነትን ከማስከበር እና የሕዝባቸውን ኑሮ ከማሻሻል ይልቅ ትኩረታቸውን የሚያሳርፉት በስልጣን የሚቆዩበትን ጊዜ ለማራዘም እና ራሳቸውን ለማበልፀግ በሚችሉበት ተግባር ላይ ነው። በዕጩ መጥፋት የተነሳም ሽልማቱ ባለፉት ዓመታት ለአንድም የቀድሞ አፍሪቃዊ መሪ አልተሰጠም ነበር።

በዚህም የተነሳ፣ አንድ የቀድሞ አፍሪቃዊ መሪ ከ2011 ዓም ወዲህ ይህንኑ በዓለም ትልቁ መሆኑ የሚነገርለትን ባለ አምስት ሚልዮን ዶላር ሽልማት ሲያገኝ እአአ የፊታችን መጋቢት 21፣ 2015 ዓም ስልጣናቸውን የሚለቁት የናሚቢያ ፕሬዚደንት ሂፌኬፑንዬ ፖሀምባ የመጀመሪያው ናቸው። የድርጅቱ ባለቤት ትውልደ ሱዳኑ ብሪታንያዊ የሞባይል ባለተቋም ሞ ኢብራሂም ፖሀምባ ለሽልማቱ ትክክለኛው ሰው ናቸው በሚል ሽልማቱ ትናንት በኬንያ መዲና ናይሮቢ ይፋ ሲሆን አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

« ፖሀምባ በተገቢው ሰዓት ስልጣናቸውን ለቀዋል። አንዳንዶች በሚያሳዝን ሁኔታ እንደሚያደርጉት በስልጣን ለመቆየት ሲሉ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ወይም ሌላ ዘዴ ለማፈላለግ አልሞከሩም። »

በዚሁ የድርጅቱ ውሳኔ ሽልማቱ ለሶስተኛ ጊዜ ለአንድ የደቡባዊ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ተሰጥቶዋል። እንደሚታወሰው፣ የቀድሞው የሞዛምቢክ ፕሬዚደንት ዮአኪም ቺሳኖ በ2007፣ የቀድሞው የቦትስዋና ፕሬዚደንት ፌስቱስ ሞጌ ደግሞ በ2008 ዓም የድርጅቱን የመልካም አስተዳደር ሽልማት አግኝተዋል። በ2011 ዓም የኬፕ ቬርዴ ፕሬዚደንት ፔድሮ ፔሬስ ተሸላሚ ሆነዋል።

ናሚቢያን ባለፉት አሥር ዓመታት የመሩት የ79 ዓመቱ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ፖሀምባ ከ18 ቀናት በኋላ የሀገር አመራሩን ስልጣን ለጠቅላይ ሚንስትር ሄግ ጌይንጎብ ያስረክባሉ። ፖሀምባ በሀገራቸው ዴሞክራሲያዊውን ሂደት በማራመዳቸው እና የሕዝባቸውን ኑሮ በማሻሻላቸው ለሽልማት መብቃታቸውን የሽልማት ሰጪው ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሳሊም አህመድ ሳሊም አስታውቀዋል።

« ዴሞክራሲን ለማስፋፋት የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። የሕዝባቸውንም የኑሮ ደረጃ አሻሽለዋል። ናሚቢያ ትንሽ ሀገር ብትሆንም፣ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ናት፣ እና ፕሬዚደንቱ በሥልጣን ዘመናቸው ይህንን ሀብቷን በሚገባ አስተዳድረዋል። «ኤች አይ ቪ» ን ለመሳሰሉ አሳሳቢ ማህበራዊ ችግሮችም መፍትሔ በመሻቱ ተግባር በተጫወቱት ሚናቸው ለሌሎች አርአያ መሆን ችለዋል። ትምህርትን አሻሽለዋል። ባጠቃላይ ለሀገራቸው በቆራጥነት እና በቅንነት ብዙ መልካም አድርገዋል። »

እአአ በ1959 ዓም ለናሚቢያ ነፃነት የታገለውን በምሕፃሩ «ስዋፖ» የተባለውን የደቡብ አፍሪቃ ሕዝቦች ድርጅትን የተቀላቀሉት ፖሀምባ ሀገራቸው በ1990 ነፃነቷን ካገኘች እና በፕሬዚደንት ሳም ንዮማ መንግሥት በተለያዩ ሚንስቴሮች ውስጥ ካገለገሉ በኋላ በ2005 ዓም 75% የመራጩን ድምፅ በማግኘት አገልግለዋል። ፖሀምባ በአመራር ዘመናቸው የሀገሪቱን አንድነት መጠበቃቸው፣ እንዲሁም፣ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ልማቷን አርአያ ሊሆን በሚችል መንገድ ማሳደጋቸው እንደሚያስመሠግናቸውም ሞ ኢብራሂም አመልክተዋል።

« ትኩረታቸውን በወጣቱ ትውልድ ላይ ያሳረፉት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ስልጣን ላይ የመጡት ሚስተር ፖሀምባ መሀይምነትን ለማጥፋት የታገሉ፣ በንዑሱ የልማት ደረጃ ላይ የነበረችውን ሀገራቸውን ወደ መካከለኛ ገቢ ሀገራት መዳዳ ያሰለፉ ሁሉን ለማስማማት የሞከሩ ፕሬዚደንት ነበሩ። የተቃዋሚ ፖለቲካ ቡድኖችን አላገለሉም። ይከተሉት በነበረው መርሀግብራቸው ላይ፣ ሁሉንም ወገኖች አሳትፈዋል። ይህ ደግሞ ግሩም ነው። »

የፖለቲካ ፓርቲዎች ውዝግባቸውን አዘውትረው በኃይሉ ተግባር ለማስወገድ በሚጥሩባት ወይም በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ የጭቆና እና የክትትሉ አሰራር በሚታይባት አፍሪቃ ውስጥ በናሚቢያ በፖሀምባ አመራር ወቅት የተስፋፋው የፕሬስ ነፃነት እና አስተያየት በነፃ የመግለጽ አሰራር የሚሞገስ መሆኑን በመዲናይቱ ዊንድሁክ የሚገኘው የሕዝብ ፖሊሲ ምርምር ተቋም ተንታኝ ግራሀም ሆፕውድ አስታውቀዋል፣ ይሁንና፣ በናሚቢያ 50% የደረሰው የወጣቶች ስራ አጥነት ባስቸኳይ መፍትሔ የሚያሻው አሳሳቢ ችግር መሆኑን ሳይጠቁሙ አላለፉም።

ሞ ኢብራሂም የዘንድሮው የመልካም አስተዳደር ተሸላሚ ትናንት በናይሮቢ ይፋ በተደረገበት ጊዜ አፍሪቃ ከሰፊው ሕዝብ ውስጥ ብዙ የማታውቃቸው አስደናቂ መሪዎች እንዳሏት በማስታወስ፣ አፍሪቃውያን እነዚህኑ ጀግኖቻቸውን ፈልገው እንዲያወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic