የመለያ ምርጫ በሴኔጋል | አፍሪቃ | DW | 24.03.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የመለያ ምርጫ በሴኔጋል

ሴኔጋል ውስጥ በነገው ዕለት በሚደረገው ሁለተኛ ዙር ምርጫ በፕሬዚደንት አብዱላይ ዋድ አንጻር የሚፎካከሩት የተቃዋሚው ወገን ዕጩ ማኪ ሳል ጥሩ የማሸነፍ ዕድል እንዳለቸው ተሰማ።

ማኪ ሳል ከተቃዋሚው ወገን ብቻ ሳይሆን ካንዳንድ የሲቭሉ ማህበረሰብ ክፍልም ድጋፍ አግኝተዋል። አንድ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ከሁለት የሥልጣን ዘመን በላይ መቆየት እንደማይችል የሚያዘውን የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ በመጣስ ለሦስተኛ ጊዜ በዕጩነት የቀረቡት የሰማንያ አምስት ዓመቱ አብዱላይ ዋድ በሥልጣን ለመቆየት የሚቻላቸውን ሁሉ ለመድረግ ቆርጠው የተነሱ ነው የሚመስለው። ይህ ጥረታቸውም ምናልባት በሀገሪቱ ሁከት ሊያስነሳ ይችል ይሆናል በሚል አንዳንዶች መስጋታቸው ባይቀርም፡ ዋድ የመጀመሪያውን ዙር ውጤት በመቀበላቸው፡ ካንዳንድ ተናጠል ግጭቶች በስተቀር የተፈራው ሁከት እንዳይነሳ ድርሻ ማበርከቱን የተቃዋሚ ቡድኖችንና የሲቭል ማህበረሰቦች የተጠቃለለበት ንቅናቄ ሀያ ሦስት የተባለው ድርህት ቃል አቀባይ አብደል አዚዝ ዲዩፕ አስረድተዋል።
« ምርጫው በሰላም ይካሄድ ዘንድ የሀገር አስተዳደሩ ሚንስቴር የፕሬዚደንት አብዱላይ ዋድ ደጋፊዎችን ጦር መሣሪያ ትጥቅ እንዲያስፈታ ጠይቀናል። ቆመጥ የያዙና የሼኽ ቤትዮ ቲውን የሀይማኖት ቡድን አባላት በመሆናቸው እነሱን መለየቱ አይከብድም። »


ሼኽ ቤትዮ ቲውን ፕሬዚደንት ዋድ አባል የሆኑበት የሙሪዴን ወንድማማችነት የሀይማኖት ቡድን መሪ ሲሆኑ፡ ቀስቃሽ በመሆንም ይታወቃሉ። በሙሪዴን ቡድን ድጋፍ ላይ ጥገኛ የሆኑት ፕሬዚደንት ዋድ መመረጣቸው እንደማይቀር በእርግጠኝነት ሲናገሩ መሰማታቸው ራሱ የነገውን ምርጫ ሂደት ትክክለኛነትን አጠራጣሪ አድርጎታል።
የነገው ምርጫ ከሁከት ነፃ እንዲሆን ከተፈለገ የተቃውሞው ወገንና ሲቭሉ ማህበረሰብ ግጭት በሚቀሰቅሱ ወገኖች ወጥመድ ውስጥ መግባት እንደሌለባቸው የፕሬዚደንቱ የዴሞክራቲክ ሶሻሊስት ፓርቲቃል አቀባይ ባባካር ጌይ አስገንዝበዋል።
ለሦስተኛ ጊዜ መመረጥ የሚፈልጉት አብዱላይ ዋድ ይህንኑ ዕቅዳቸውን የማይደግፉትን ወገኖች ለማረጋጋት ሲሉ ከጥቂት ጊዜ በፊት በሰጡት መግለጫ ላይ ቢመረጡ ቀጣዮቹን ሦስት ዓመታት ብቻ በሥልጣን እንደሚቆዩ አስታውቀዋል። ዋድ እነዚህኑ ሦስት ዓመታት ልጃቸውን ካሪም ወደ ሥልጣኑ ኮርቻ ለማምጣት ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ ብዙዎቹ የሴኔጋል ዜጎች ሰግተዋል። በሴኔጋል ዜጎች ዘንድ እጅግ የተጠሉትና ከመንግሥት ካዝና ብዙ ገንዘብ ለግል ጥቅም አባክነዋል የሚባሉት ካሪም የመብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ኃላፊ ሳሉ በሀገሪቱ ባለፈው ዓመት ለታየው የኮሬንቲ እጥረትና መጥፋት ተጠያቂ ናቸው በሚልም ይወቀሳሉ።


ይህ ሕዝቡ በመሪው ላይ የሚያሰማው ቅሬታ ሁሉ የተቃዋሚው ወገንና የሲቭሉ ማህበረሰብ ድጋፍ ያላቸውን የዋድ ተፎካካሪ ማኪ ሳል የመመረጥ ዕድልን እንዳመቻቸ የነፃነትና የስራ ፓርቲ አባልና የመንግሥታዊ ያልሆነው ለልማት የቆመው ድርጅት ሊቀመንበር አማኮዱ ዲዩፍ ገልጸዋል።
« የፕሬዚደንቱ ተፎካካሪ ሥልጣን ከያዙ፡ ሰፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ይፈጥራሉ። የሚከተሉት ፖሊሲም የተለያዩትን ፓርቲዎች ዕቅዶችን ያካተተ ይሆናል። ስለዚህ ይህ ፖሊሲያቸው ለሴኔጋል ሕዝብ ፍላጎት ትኩረት የሚሰጥ እንደሚሆን እንተማመናለን። »
በሙስና አንጻር በያዙት አቋማቸው ችግር ሲያጋጥማቸው ተቃውሞውን ወገን የተቀላቀሉት የማዕድንና የሀገር አስተዳደር ፡ በ ሁለት ሺህ ሰባት ደግሞ በጠቅላይ ሚንስትርነት ያገለገሉት የሀምሳ አንድ ዓመቱ ማኪ ሳል ካላሸነፉ ግን ዋድ በምንም ዓይነት መንገድ ሥልጣን መቆየት እንደሌለባቸው የዩኒቨርሲቲ መምህርና የሲቭል ማህበረሰብ አባል አብዱልአዚዝ ኬቤ አስታውቀዋል።
« ይህን ለማከላከል ቀጣዮቹን ሀያ አምስት ዓመታት ሙሉ ተቃውሞ ማድረግ ቢኖርብ፡ ማድረጋችን አይቀርም። ሀገሪቱን እንዲገዙ ዕድል አንሰጣቸውም። »
አንዳንዶች እንዲህ ቢሉም በኮትዲቯር በመጨረሻው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በኋላ በአሸናፊና በተሸናፊ ዕጩዎች መካከል የተፈጠረው ዓይነቱ ሁከት በሴኔጋል ይደገማል ብለው አያምኑም።

አርያም ተክሌ

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic

 • ቀን 24.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14QrQ
 • ቀን 24.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14QrQ