የሕጻናት ካንሰር መባባስ | ጤና እና አካባቢ | DW | 14.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የሕጻናት ካንሰር መባባስ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ካንሰር ያስከተለዉ ጫና በማያጠራጥር መልኩ እየጨመረ መሄዱ እየተነገረ ነዉ። ለምሳሌ ጎረቤት ኬንያ ዉስጥ ካንሰር የሰዎችን ህይወት ከሚቀጥፉ ዋና ዋና የጤና እክሎች በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። እንደ አዋቂዎች ለመንስኤዉ ምክንያት ሊሰጥለት ያልቻለዉ ደግሞ በካንሰር የሚጠቁ ሕጻናት ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:46

የካንሰር ታማሚ ሕጻናት

ኬንያ ዉስጥ በየዓመቱ ቢያንስ 28 ሺህ ሰዎች ከካንሰር ጋር በተገናኙ ዉስብስብ የጤና እክሎች ህይወታቸዉን እንደሚያጡ የኬንያ የካንሰር ማኅበር ያመለክታል። የኬንያ ባለስልጣናት እና የጤና ጉዳይ ተሟጋቾች በካንሰር ከሚጠቁት ዜጎች የሕጻናቱ ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ለምሥራቅ አፍሪቃዊቱ ሀገር የጤና ጥበቃ ሥርዓት ከፍተኛ ጫና ፈጥሮበታል። ዲቦራ ሞዲ በሀገሪቱ ካንሰርን አስመልክቶ ህዝቡ ግንዛቤ እንዲያገኝ በመሥራት ላይ የሚገኘዉ መንግሥታዊ ያልሆነዉ የኬንያ ካንሰር ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ናቸዉ ።

«በአሁኑ ጊዜ ካንሰር የሚያስፈልገዉን ተገቢ ትኩረት ማግኘት የሚገባዉ የዚች ሀገር ሸክም የሆነ የጤና ችግር ሆኗል። ምክንያቱም በየዓመቱ 28 ሺህ ዜጎችን በዚህ ምክንያት እያጣን ነዉ። እነዚህ ደግሞ ተመዝግበዉ ያታወቁ ናቸዉ። በካንሰር መያዛቸዉ ያልታወቀላቸዉ እና ሳይመዘገቡ በየቤታቸዉ የሚሞቱትስ? ስለዚህ ካንሰር መሆን የሚገባዉ ቦታ ላይ መቀመጥ አለበት፤ ኬንያ ዉስጥ ገዳይ በሽታ ነዉ።»

ይፋዊ ሰነዶች እንደሚያሳዩት ኬንያ ዉስጥ ከልብ እና የደም ቧምቧ ጋር በተገናኘ በሽታ እንዲሁም በተላላፊ በሽታዎች ከሚሞተዉ ሰዉ ቀጥሎ በሦስተኛነት ካንሰር ግንባር ቀደም ቀሳፊ በሽታ ሆኗል። ለካንሰር ህመምተኞች ተገቢዉን ህክምና የሚሰጠዉ የቴክሳስ ካንሰር ማዕከል ከፍተኛ የካንሰር ሃኪም ዶክተር ካተሪን ናዮንጌሳ እንደሚሉት ሲመረመሩ ካንሰር የሚገኝባቸዉ ዜጎች ቁጥር እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

«የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ ነዉ። በአሁኑ ሰዓትም HIV ከሚያስከትለዉ ሞት ይልቅ በካንሰር የሚሞተዉ ሰዉ ቁጥር ከፍ ብሏል። ከ40 ሚሊየን በሚበልጥ ህዝብ ባላት ሀገር በየዓመቱ 40 ሚሊየን የሚደርስ የካንሰር ታማሚ እየተገኘ ነዉ። ይህ ግን ተገቢዉን የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን እንዳላገኘ እንገምታለን። ምክንያቱም በየጊዜዉ በገጠሩ አካባቢ የሚገኘዉን የካንሰር ታማሚ ቁጥር የሚመዘግብ ብሔራዊ የመመዝገቢያ ስልት የለንም። በዚያ ላይ አብዛኞቹ እንደነዚህ ያሉት የካንሰር ታማሚዎችም በመተት ለዚህ ተዳርገዋል ተብሎ ስለሚታመን እንደካንሰር ታማሚ ጉዳያቸዉ አይመዘገብም።»

በኬንያ ዋነኛዉ በሆነዉ እና ታማሚዎች ለከፍተኛ ህክምና በሚላኩበት የኬንያታ ብሔራዊ ሆስፒታልም የሚሠሩት የካንሰር ከፍተኛ ሃኪም እንደሚሉትም አብዛኞቹ በምርመራ የሚደረስባቸዉ የካንሰር ችግሮች፤ ታማሚዎቹ በሽታዉ ከጠናባቸዉ በኋላ ለህክምና በመሄዳቸዉ ምክንያት ከሚድኑት የሚያልፉት እንዲበረክቱ ምክንያት ሆኗል።

«ሀገራችንን ስንመለከት በየዓመቱ 40 ሺ የካንሰር ታማሚዎችን በምርመራ ብናገኝም ፤ 28 ሺህ የሚሆኑትን ማትረፍ አንችልም። እናም ከታማሚዎቹ አብዛኞቹ ይሞታሉ ማለት ነዉ።ይህ የሆነዉም ችግሩ የሚታወቀዉ ባለቀ ሰዓት ነዉ።»

በሌላ በኩል ካንሰር የአዋቂዎች ማለትም በዕድሜ የገፉ ሰዎች በሽታ እንደሆነ ቢታሰብም ኬንያ ዉስጥ የካንተር ታማሚ ሕጻናት ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መሄዱም ይነገራል። ለዚህ በምክንያትነት ከሚነሱት መካከል የአኗኗር ልማድ እየተቀየረ መሄድ የሚለዉ በዋናነት ይጠቀሳል። ዶክተር ናዮንጌሳ ሰዎች ለካንሰር የሚያጋልጡ ምክንያቶችን ጠንቅቀዉ ማወቅ ይኖርባቸዋል ነዉ የሚሉት።

«የአኗኗር ሁኔታን ስንመለከት፤ ምናልባት ወላጆች የምዕራቡን ዓለም የአኗኗር ስልት የቀዱ ከሆነ፤ ማለትም ለምሳሌ ቤተሰቦች የሚያጨሱ ከሆነ፣ ቤት ዉስጥ ሊያጨሱ ይችላሉ፤ ይህ አደጋ ነዉ። የጭንቅላት ዕጢን ብንመለከት፤ ልጆች ላይ መገኘቱ የተለመደ ሆኗል፤ ለምሳሌ ልጆቹ ላይ ዝንጋታ፣ ወይም በትክክል መራመድ አለመቻል፣ ሲከሰት ማንም ቢሆን የጭንቅላት ዕጢ ይሆናል ብሎ አይገምትም። አሁን የህክምና መሣሪያዉ ተሻሽሏል፤ የጭንቅላት ዕጢ ዉስጡ መኖሩን ማየት ይቻላል፤ ሌላዉ ምክንያት ደግሞ በዘር የተወረሰ ሊሆን ይችላል።»

ኬንያ ዉስጥ ልጆች ላይ በብዛት የሚገኘዉ የካንሰር ዓይነት የደም ካንሰር ነዉ። በተሰባሰቡ የደም ሴሎች ምክንያት የሚመጣዉ የካንሰር ዓይነት እና የጭንቅላት ዕጢ ነዉ። ኢትዮጵያ ስንመለከት በተመሳሳይ የደም ካንሰር ታማሚ ሕጻናት ቁጥር ከፍ እንደሚል ነዉ ከኢትዮጵያ የማቲዎስ ወንዱ የካንሰር ማኅበረሰብ መሥራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንዱ በቀለ የተረዳነዉ።

ኬንያዊቱ የካንሰር ከፍተኛ ሃኪም ዶክተር ናዮንጌሳ አዋቂዎቹ የካንሰር ታማሚዎች ወደህክምና የሚሄዱት በሰዎች የህክምና ርዳታ መፍትሄ ለማግኘት አዳጋች የሆነ ደረጃ ላይ ሲደርሱ እንደሆነ ጠቅሰዋል። አቶ ወንዱም ተመሳሳይ ችግር ኢትዮጵያ ዉስጥም እንደሚታይ ነዉ የጠቆሙት።

Bakterien Zellen Virus

የካንሰር ሴል

ኢትዮጵያ ዉስጥ በየዓመቱ እስከ 60 ሺህ የካንሰር ታማሚዎች በምርመራ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል አቶ ወንዱ እንደገለጹልን 6 ሺህ የሚሆኑት ሕጻናት ናቸዉ። የሕጻናት የካንሰር ታማሚዎች በሽታዉ ብዙም ሳይጠነክርባቸዉ ወላጆች ወደ ሀኪም ቤት ስለሚወስዱ ታክመዉ የመዳን ዕድላቸዉ ከአዋቂዎች ጋር ሲነጻፀር የተሻለ በመሆኑ በዚህ ረገድ የሚደረገዉን ጥረት ዊጤታማ ለማድረግ አንድ መርሃግብር በቅርቡ ማቀዳቸዉንም ጠቁመዋል።

ይህ የባለሙያዎቹ የምክክር ጉባኤም በህክምናዉ ረገድ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ምን መሥራት እንደሚገባ የሚታይበት አጋጣሚ እንደሚሆን ነዉ አቶ ወንዱ የገለፁት። በቀጣይም የሚከናወኑ ዕቅዶችም አላቸዉ። እስካሁን ግን ዋናዉ ህክምና ለልጆቹ የሚሰጠዉ በአዲስ አበባዉ ጥቁር አንበሳ ሃኪም ቤት ነዉ። ሀኪም ቤቱ ባለዉ ዉሱን አቅም ምክንያትም ለታማሚዎቹ ሁሉ የሚበቃ አልጋዎች አይኖሩም። ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ማኅበረሰብ ታዲያ በተለይ ሕጻናቱ ሕክምናዉን መከታተል እንዲችሉ ድጋፉን በመስጠት ላይ ነዉ።

በዚህ ብቻ አያበቃም ሃኪም ቤቱ ምግብ ለታማሚዎቹ ሕጻናት ብቻ ነዉ የሚያቀርበዉ፤ የወላጆችን ቀለብ የመቻሉ ኃላፊነትም እነሱ ላይ ነዉ። እንዲያም ሆኖ ግን የበኩላቸዉን ለማድረግ ጥረታቸዉን መቀጠላቸዉን፤ ለእነሱ ትልቁ ነገርም የሕጻናቱ ህይወት መትረፍ ነዉ። በነገራችን ላይ በበለፀገዉ ዓለም ከ10 የካንሰር ታማሚ ሕጻናት ሰባቱ በህክምና ይድናሉ። በተቃራኒዉ ኬንያ ዉስጥ ከ10 ታማሚ ሕጻናት አንዱ ነዉ የመትረፍ ዕድሉ ያለዉ። ካንሰር በጊዜዉ ከተደረሰበት በህክምና ሊረዳ ብሎም ሊድን የሚችል መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ደጋግመዉ ያስረዳሉ።

 ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች