የሕግ የበላይነትን እዚህ በጉልበት፣ እዚያ በልመና | ኢትዮጵያ | DW | 22.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የሕግ የበላይነትን እዚህ በጉልበት፣ እዚያ በልመና

የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሒደቱ በምዕራብ ወለጋ ከኦነግ ጋር እና በለገጣፎ-ለገዳዲ ከሰነድ አልባ ቤት ገንቢዎች ጋር በምን ዓይነት መንገድ እየተካሔደ እንደሆነ በአጭሩ መግለጽ አስተማሪ ሊሆን ይችላል።

በሰላማዊ ፖለቲካ ተሳትፎ ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ኦነግ-ሸኔ የጦር ክንፍ በምዕራብ ወለጋ የቀበሌ አስተዳደሮችን በኃይል በራሱ ሰዎች እስከመተካት ደርሶ ነበር። ከደርዘን በላይ ባንኮችን “ኦነግ ነን” ያሉ ታጣቂዎች እዚያው አካባቢ ዘርፈዋል፤ በጉጂ አሁንም ድረስ ኦነግ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ተሰምቷል። ነገር ግን ኦነግ ይህንን ሁሉ የሕግ ጥሰት ሲያደርስ ሽማግሌ ነው የተላከበት። ምክንያቱ ግልጽ ነው፤ ኦነግ በአንድ በኩል የታጠቀ፣ በሌላ በኩል ብዙ ደጋፊ ያለው ቡድን ነው።

በተቃራኒው በለገጣፎ «በመሬት ወረራ» ወይም በተለምዶ አጠራሩ «የጨረቃ ቤት» (ሰነድ አልባ ቤቶች) የገነቡ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ቤታቸው ዓይናቸው እያየ «በግሬደር» ፈርሷል። ሌሎች አካባቢዎች በግጭቶች ሳቢያ የተፈናቀሉት መልሰው ሳይቋቋሙ፥ በመንግሥት እርምጃ እነዚህ ቤተሰቦችም ቤት አልባ፣ ተፈናቃይ ሆነዋል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ይህንን ያደረግኩት «የሕግ ማስከበር ኃላፊነት ስላለብኝ ነው» ብሏል። ከላይ በተመለከትነው መሠረት እነዚህ ሰዎች «ሲቪል» ናቸው፣ የተደራጀ ደጋፊም የላቸውም። ስለዚህ ለነዚህ ሰዎች መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ በጉልበት እርምጃ መውሰድ የሕግ የበላይነትን የማስከበሪያ መንገድ ሆነ።

«የጨረቃ ቤት» ድሮ እና ዘንድሮ

በፊት በፊት፣ የጨረቃ ቤቶች (ሕጋዊ ዕውቅና የሌላቸው ነገር ግን ቤት ፈላጊዎች ባዶ ቦታ ፈልገው የሚገነቧቸው ቤቶች) የሚሠሩት ሌሊት ሌሊት ነበር። ሥማቸውንም ያገኙት ከዚያው ነው። ይህን የሚያደርጉበት ዋነኛው ምክንያት ቀን ቀን ከሠሩ የሕግ አስከባሪ አካላት ስለሚያገኟቸው እና ስለሚያስቆሟቸው ነበር። ሠርተው ከተገኙ በኋላ ግን ቤትን ያህል ነገር ማስፈረስ ስለሚከብድ ሕጋዊ የሚሆኑበት መንገድ ይፈለግ ነበር። በዚህ ምክንያት የጨረቃ ቤት መሥራት ልምድ/ባሕል እየሆነ መጥቷል። ይሁን እንጂ አሁን ያለው አካሔድ ተቃራኒ ነው።

አሁን አሁን «ሰነድ አልባ» (እንደ ጨረቃ ቤቶች ያለ ሕጋዊ ዕውቅና የሚገነቡ ቤቶች) የሚገነቡት ሌሊት ሳይሆን በቀን ነው። ብዙ ጊዜ የቀበሌዎቹ አስተዳደሮች እያዩ እና ጥቃቅን የገንዘብ ጉርሻ እየተቀበሉ ሲገነባ ዝም ይላሉ። ደላሎቹም መሬቱን ከገበሬዎች ወደ ሰነድ አልባ ቤት ገንቢዎቹ ሲሸጡ ሌላ ቦታ ተገንብተው መንደር ከሆኑ በኋላ ዕውቅና ያገኙ ቤቶችን እንደምሳሌ እያሳዩ «የናንተም ዕውቅና ማግኘቱ አይቀርም፤ ዋናው ገንብቶ መገኘት ነው» አያሉ ይገፋፏቸዋል። ሌሎች የመንግሥት ተቋማትም ተባባሪ ይሆናሉ፣ የኤሌክትሪክ እና የውኃ አገልግሎት ያቀርቡላቸዋል። መንገድ ይጠርጉላቸዋል።

ይሄ ሁሉ ከሆነ በኋላ በድንገተኛ ዘመቻ እና በአጭር ጊዜያት ማስታወቂያ «ማስተር ፕላኑ» ስለማይፈቅድ ተነሱ ይባላል። ስንት ጊዜ የኖሩበትን ቤትና መንደር በቀላሉ ለመልቀቅ የሚቸገሩት ሰዎች ዕቃቸውን ላለማውጣት ይወስናሉ፤ የመንግሥት ግሬደሮች ቤቶቹን ከነዕቃቸው ያፈርሳሉ። ለገጣፎ የሆነው ይሔ ነው። ሌሎችም ጋር ሲሆን የነበረው እና ወደ ፊትም ሊቀጥል የሚችለው ይኸው ነው። ከዚህ በፊት ድርጊቱ ደም መፋሰስ ያስከተለበት ሁኔታ ነበር። በሃና ማርያም ቤታቸው የሚፈርስባቸው ሰዎች ከፖሊሶች ጋር ተታኩሰው የሰዎች ሕይወት መቀጠፉ አይዘነጋም።

መፍትሔው «ዶግማዊነት»ን መተው ነው

ኦነግ ትጥቅ ያነሳው «አገር ቤት ውስጥ ያለው የፖለቲካ ምኅዳር በመጥበቡ እና በሰላማዊ መንገድ ፖለቲካዊ ግብን ማስፈፀም ባለመቻሉ ነው» በሚል፥ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ በማሰብ በመንግሥት በኩል ምኅዳሩን ነጻ በማድረግ፣ ስለ ለውጡ ለማሳመን ጥረት በማድረግ እና ሲያጠፋም በመታገስ፣ ለጥፋቱም/ጉዳቱም ተጠያቂ ባለማድረግ የፖለቲካ ቡድኑ በስርዓቱ ላይ እምነቱን አዳብሮ ወደ ሰላማዊነት እንዲመለስ እየተደረገ ያለው ጥረት ከሕግ የበላይነት አንፃር አያስኬድም። ከሰላም እና ከሽግግር ጊዜ መፍትሔነት አንፃር ግን ተቀባይነት ያለው ጉዳይ ስለሆነ ብዙኃን አልተቃወሙትም።

የሰነድ አልባ ቤት ገንቢዎችም ጉዳይ ከዚህ የተለየ አይደለም። ሰዎቹ በከተሞች ያለው የቤት ኪራይ ውድነት፣ የራስን ቤት መገንባት የሚቻልባቸው ዕድሎች መጥበብ ላይ የካድሬዎች እና የደላሎች ሽንገላ አታልሏቸው እነዚህን ቤቶች መገንባታቸው ይታወቃል። ለዚህ መንግሥትም መሠረታዊ አቅርቦቶችን በማሟላቱ ከፊል ዕውቅና የተሰጣቸው ስለመሰላቸው ብዙ መዋዕለ ንዋይ እያወጡ ቤታቸውን አስፈፋፍተዋል። መንግሥት እነዚህን ቤት ገንቢዎችም ሊመለከታቸው የሚገባው ኦነግን ከተመለከተበት ዓይን በተለየ አይደለም። ይህንን ብዙ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰበት፣ የመንግሥት የፖሊሲ እና አፈፃፀም ችግር የፈጠረው፣ ብሎም የማፍረሱ ውጤት እልፍ ቤተሰቦችን ሜዳ ላይ የሚበትን ጉዳይ እንደተራ የሕግ የበላይነትን ማስከበር መታየት የለበትም። የሕግ የበላይነት ጉዳይ የተጣሰው ገና ቤቶቹ መገንባት ሲጀምሩ ነው። አሁን የተደራጁ መንደሮች ከሆኑ በኋላ የሚወሰደው የማፍረስ ዘመቻ ስህተትን በስህተት የማረም ሙከራ ነው። የሚሻለው መፍትሔ የማስተካከያ ፖሊሲ መቅረፅ ነው።

ሕግም ይሁን «ማስተር ፕላን» የማይቀየሩ ወይም የማይሻሻሉ ቅዱስ ቃሎች አይደሉም። ለዜጎች ጥቅም እና ምቾት ሲባል እንደአስፈላጊነቱ ሊከለሱ እና ሊቀየሩ ይችላሉ። ሰነድ አልባ ቤቶቹ የሰፈሩበት ቦታ «በፍፁም መንደር መሆን የለበትም» የሚያስብል ነገር ቢገኝ እንኳን፣ በመንግሥት እና በነዋሪዎቹ ትብብር አማራጭ የመኖሪያ ስፍራ በማዘጋጀት በጋራ የእርምት እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።

በፍቃዱ ኃይሉ

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሐፊው እንጂ የ«DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።

ተዛማጅ ዘገባዎች