የሕገ መንግሥታዊ ምክር ቤት ምርጫ በሊቢያ | አፍሪቃ | DW | 15.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሕገ መንግሥታዊ ምክር ቤት ምርጫ በሊቢያ

በሊቢያ እአአ የፊታችን የካቲት 20፣ 2014 ዓም አዲስ ምክር ቤት ይመረጣል። ከያካባቢው 20 አባላት፣ ባጠቃላይ 60 አባላት የሚጠቃለሉበት ይኸው ምክር ቤት በሚቀጥሉት ወራት ለሀገሪቱ አዲስ ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ስራ ይጠብቀዋል። ይህ ስራው ቀላል እንደማይሆን እና የምርጫው ሂደትም በተረጋጋ ሁኔታ መከናወኑ እንደሚያጠራጥር ታዛቢዎች ገምተዋል።

በሊቢያ እአአ ለህዳር ፣ 2013 ዓም ታቅዶ የነበረው እና ብዙ ጊዜ መገፋት የተገደደው ሕገ መንግሥታዊው ምክር ቤት ምርጫ አሁን እአአ የፊታችን የካቲት 20፣ 2014 ዓም እንዲካሄድ መወሰኑ አዎንታዊ ርምጃ ሆኖ ታይቷል። ይሁንና፣ ባለፈው ሀምሌ፣ 2012 ሀገሪቱ በተደረገው ምክር ቤታዊ ምርጫ ለመሳተፍ ያኔ በተመዘገበው 2,8 ሚልዮን መራጭ ሕዝብ አንፃር፣ ለሕገ መንግሥታዊው ምክር ቤታዊ ምርጫ የተመዘገበው ሕዝብ ቁጥር 1,7 ሚልዮን ብቻ መሆኑ ብዙዎችን ሳያሳስብ አልቀረም።

የባሰው ግን በሕገ መንግሥታዊው ምክር ቤት ሁለት መንበሮች የተያዘላቸው በሰሜን ምዕራባዊ ሊቢያ የሚኖሩት አማዚግ የተባሉት የበርበር ጎሣ አባላት ለምርጫው ተወዳዳሪ አለመላካቸው ነው። ተወዳዳሪ ከመላካቸው በፊት በሐገ መንግሥቱ ውስጥ መብታቸው እንደሚጠበቅ የሚያረጋግጥላቸው ዋስትና ጠይቀዋል።

ይኸው ውሳኔ የአማዚግ ከንቲባ የሆኑትን እና የመዲናይቱ ትሪፖሊን በመወከል በዕጩነት የቀረቡትን ሞራድ ብላል ቅር አሰኝቶዋል።

« በአማዚግ ብዙ ጓደኞች አሉኝ። በዚሁ ውሳኔአቸው ስህተት የሰሩ ይመስለኛል። 60 አባላት ለሚኖሩት ምክር ቤት ዕጩዎቻቸውን መላክ ይገባቸዋል። »

ለሕገ መንግሥቱ አርቃቂ ምክር ቤት በዕጩነት ለመወዳደር ልዩ ዲፕሎማ እንደማያስፈልገው ያመለከቱት በጠበቃነት ሙያ የሚሰሩት እና በተወዳዳሪነት የቀረቡት መሀመድ ቱሚ የተለያዩ ጎሣዎች በምክር ቤቱ የሚወከሉበት ድርጊት በምክር ቤቱን ስራ ላይ ችግር እንደማይፈጥር አስታውቀዋል።

« የሚመረጡት 60 ዎቹ ሕጉን፣ ሕገ መንግሥታዊውን መብት ወይም መሰል ጉዳዮችን የግድ ማወቅ የለባቸውም። ተመራጮች፣ ኮሚቴው በሚሰራበት ደንብ መሠረት፣ ሊረዱዋቸው የሚችሉ ሌሎች ሰዎችን ወይም የሕገ መንግሥት ፕሮፌሰሮችን ከመላ ዓለም ሊያሰባስቡ እና የተባበሩት መንግሥታትን የመሳሰሉ ድርጅቶችን ርዳታ ሊጠይቁ ይችላሉ። »

አንዱ ተወዳዳሪ የሆኑት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፕሮፌሰሩ ሉብና ሙንታሰር ለምሳሌ ስለ ሕግ አንድም ዕውቀት የላቸውም። ይህ ግን የሊቢያ የወደፊት ሕገ መንግሥት ምን ሊመስል እንደሚገባው አስተያየት እንዳኖራቸው ሊያግዳቸው አይችልም።

« ሁኔታዎችን በዝርዝር ያስቀመጠ ሕገ መንግሥት እንዲሆን ነው የምጠይቀው። ማንም እንደፈለገው ሊተረጉማቸው የሚችሉ አንቀጾች እንዲሠፍሩ አልፈልግም። የቱኒዝያን ሞዴል የተከተለ ቢሆን ይመረጣል። የግብፃውያኑን ሕገ መንግሥትም ጥሩ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። »

በሀገሪቱ የሽግግር ምክር ቤት ዕቅድ መሠረት፣ ረቂቁ ሕገ መንግሥት እስከ ፊታችን ክረምት ወራት ድረስ በሬፈረንደም መፀደቅ ይኖርበታል። ይህን ተከትሎ በሀገሪቱ አጠቃላይ ምርጫ ሊካሄድ ይችላል።

አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic