የሕይወት ዘመን ሽልማት ለድምጻዊ ማሕሙድ አህመድ | ባህል | DW | 09.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የሕይወት ዘመን ሽልማት ለድምጻዊ ማሕሙድ አህመድ

«በሙዚቃዉ ዓለም 56 ዓመት ሆነኝ። ሕዝብ ያለዉን ፍቅርና ያለዉን አክብሮት ገልፆልኛል። እኔ በዶይቼ ቬለም በኩል እንዲደርስልኝ የምፈልገዉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአንተነት ወደ አንቱነት ላደረሰኝ በጠቅላላ አክብሮቱን ስለገለፀልኝ ትልቅ ባለ ዉለታዬ መሆኑን ነዉ። አሁንም ዋሴም ጠበቃዬም የኢትዮጵያ ሕዝብ ነዉ።»

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:19

ሕዝብ ያለዉን ፍቅርና ያለዉን አክብሮት ገልፆልኛል።

«እኔ በዶይቼ ቬለ በኩል እንዲደርስልኝ የምፈልገዉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአንተነት ወደ አንቱነት ስላደረሰኝ ለማመስገን እወዳለሁ። በቃ ይኸዉ ነዉ» ይኸዉ ነዉ አለን፤ የትዝታዉ ንጉስ አንጋፋው ድምጻዊ የክብር ዶክተር ማሕሙድ አህመድ፤ ባለፈዉ ሳምንት ማብቅያ ላይ እዚህ በጀርመን ከተማ ከሚገኘዉ ከኢትዮጵያዉያን አርቲስቶች ማዕከል የሕይወት ዘመን የክብር ሽልማት ባገኘ ማግስት። የትዝታዉ ንጉስ ድምጻዊ ማሕሙድ አህመድ የኢትዮጵያን አርቲስቶች በሚደጉመዉ ማሕበር የዓመቱ ታላቅ ሰዉ ተብሎ ሲሸለም፤ ከጎኑ አንጋፋዉና ተወዳጁ ድምጻዊ ፀሃዬ ዮሐንስ፤ እንዲሁም አርቲስት አብርሐም ወልዴ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል። ድምጻዊ ማሕሙድ አህመድ የእለቱ ታላቅ ሰዉ ክብር ሽልማትን ሲቀበል፤ 76 ኛዉ የትዉልድ ቀኑም በድምቀት ተከብሮለታል።

Deutschland Auszeichnung für Mohamud Ahmed

የሕይወት ዘመን ተሸላሚዉ ድምጻዊ ማሕሙድ አህመድ ፤ በፍራንክፈርት ጀርመን

ማስታወቅያ «ታላቅ የሙዚቃ ፊስቲቫል በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ የኢትዮጵያ አርቲስቶች ማዕከል በዘንድሮዉ ዓመታዊ ዝግጅቱ አንጋፋውን የክብር ዶክተር አርቲስት ማሕሙድ አህመድን፤ የዓመቱ ታላቅ ሰዉ ሽልማት ይሸልማል።»   

በጀርመን እና አካባቢዋ በሚገኙ የአዉሮጳ ሃገራት ኢትዮጵያዉያን ይህችን ማስታወቅያ ሰምተዉ ድምጻዊ ማሕሙድ አህመድን እንኳን ለዚህ አበቃህ እናመሰግናለን ሊሉ ሲዘጋጁ ቀን ሲቆጥሩ ነዉ የሰነበቱት። የትዝታዉ ንጉስ አንጋፋው ድምጻዊ ማሕሙድ አህመድ በኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳይሆን በዓለም በተለይ ደግሞ በአዉሮጳ ሙዚቀኞች ዘንድም ታዋቂ ነዉ። ለዚህም ለክብሩ መግለጫ በተዘጋጀዉ አዳራሽ የነበረዉ ታዳሚ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን አዉሮጳዉያንም ነበሩ። ድምጻዊ ማሕሙድ አህመድ በፍራንክፈርት ጀርመን ከተማ ለክብሩ መስጫ ወደተዘጋጀዉ ሰፊ አዳራሽ ሲገባ የኢትዮጵያን ባንዲራ ባገለደሙ ጀርመናዉያ የማርሽ ባንድ ሙዚቀኞች  እየተመራ በክብር እንግድነት በተጋበዙት በድምጻዊ ፀሃይ ዩሐንስ እና አብርሐም ወልዴ ታጅቦ ነበር ወደ አዳራሹ የዘለቀዉ ። 

Deutschland Auszeichnung für Mohamud Ahmed

የሕይወት ዘመን ተሸላሚዉ ድምጻዊ ማሕሙድ አህመድ ፤ በፍራንክፈርት ጀርመን

ድምጻዊ የክብር ዶክተር ማሕሙድ አህመድ ጀርመን ከሚገኘዉ ከኢትዮጵያዉያን አርቲስቶች ማዕከል የሕይወት ዘመን የክብር ሽልማትን ለመቀበል ከመምጣቱ በፊት በዩናይትድ ስቴትስ የማኀበረ ግሩያን ዘረ ኢትዮጵያ 25ኛ ዓመት አንዱ የልዩ የክብር ተሸላሚ ነበር። ድምጻዊ ማሕሙድ አህመድ ለዚህ ክብር በመብቃቱ ደስታዉን በአክብሮት እንዲህ ነዉ የገለፀልን።

«መቼም የክብር ሽልማት ሲሰጥ ያለዉ ደስታ ምን ያህል እንደሆን ይታወቃል። እድሜ ያሳለፍክበት ታዉቆልህ፤ በዚህ እድሜ ሽልማትን ማግኘቱ ቀላል ነገር አይደለም። ባለፈዉ ሳምንትም ዋሽንግተን ዉስጥ ተሸልሜያለሁ። አሁንም እዚህ ጀርመን መጥቼ የጀርመን ኪነ-ጥበባት ማዕከል ባደረጉልኝ ጥሪ መሰረት ሽልማቴን ተቀብያለሁ።»

የማሕሙድ አህመድ ሙዚቃ ሲነሳ የድሬዋን ልጅ የከዚራ ስለ ውበቷ ሳያወራ፤ የሀረሯንም ሆነ የአዋሽ ማዶዋን ልጅ በምናቡ የማያስብ የለም። ከዝያም አለፍ ሲል፤ ካንቺ በቀር ሌላ ብሞት አልመኝም፤ ግን እስከ አሁን ድረስ አላወቅሽልኝም ብሎ የዘገየችበትን ሁሉ ጠይቆ የዓይኖቹን መራብ ሁሉ በሙዚቃዉ በጆሯችን አንቆርቁሮልናል። የፍራንክፈርቱ የኢትዮጵያ አርቲስቶች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ተፈሪ ፈቃደ ደግሞ ድምጻዊዉን ለሽልማት ሲያበቁ አዳራሹ ዉስጥ እንደ ማሕሙድ አህመድ የልጅነት ግዜ ሥራ  ጎንበስ ብለዉ የድምጻዊዉን ጫማ ጠርገዋል። ማሕሙድ አህመድ ልጅነቱን እንዲህ ያስታዉሳል።

ድምጻዊ ፀሃዬ ዮሐንስ፤ ፍራንክፈርት ጀርመን

ድምጻዊ ፀሃዬ ዮሐንስ፤ ፍራንክፈርት ጀርመን

«ወየጉድ እኔ በልጅነቴ የ 14 ዓመት ልጅ ሆኜ ለአምስት ዓመት ጫማ ጠርጌያለሁ። ከዝያ ደግሞ ከአናጢ ጋር አናጢ ሆኛለሁ፤ ከቀለም ቀቢ ጋር ቀለም ቀቢ ሆኛለሁ፤ ከኤሌትሪክ ሰራተኛ ጋር ኤሌትሪክ ሠራተኛ ሆኛለሁ፤ ከዝያ ወደ ወጥ ቤት ገብቼ በወጥ ቤትነት ስሠራ ከቆየሁ በኋላ ነዉ ወደ ዘፈን ዓለም የገባሁት።»

የኢትዮጵያ አርቲስቶች ማዕከል «ኤናክ» የሚል ስያሜን የያዘዉ የድርጅቱ ሊቀመነበር አቶ ተፈሪ ፈቃደ ድርጅቱ ዘንድሮ አንጋፋዉን ሙዚቀኛ ማሕሙድ አህመድን በመጋበዙ ኩራት ይሰማዋል ሲሉ ተናግረዋል። ድምጻዊዉ ስለሽልማቱ ያነበረዉን ስሜትም እንዲህ ነዉ የገለፁት። 

«የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኪነ-ጥበብ ማዕከል ኤናክ፤ በጀርመን የሚገኘዉ ማኅበራችን ታላቁን አርቲስት ተሸላሚ በማድረጉ ራሱ ማኅበሩ ታላቅ ኩራት ይሰማዋል። እንደነዚህ ዓይነት ታላላቅ አርቲስቶቻችን ስናከብራቸዉ ከመሰረቱ ከታች ጀምረን እስከላይ ላሉበት ጊዜ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የዋሉትን ዉለታ በማስታወስ አደረግነዉ። የተሟላ ይሆናል ብለን ስላሰብንም የጀመርነዉ ከነበረበት ከክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ የነበረበትን የኪነ-ጥበብ አነሳስ ነዉ። እዝያ ጋር ሃዘን ነበር የተሰማዉ። ቀደም ሲል አብረዉት የነበሩትን የጓደኞቹን ሙዚቃ በማቅረብ እንዲሁም ልዩ የክብር ዘብ አቀባበል በማድረግ እነዚህ ነገሮች ልዩ ስሜት እንዲፈጥሩበት አድርገናል። እንደዉም እንባ ሲተናነቀዉ አይቻለሁ። ያ ትክክለኛ የፈለግነዉ ነገር ነበር። በትዝታ እንዲያየዉ ነዉ ያንን ያደረግነዉ። ከዝያ በመቀጠል የልደት በዓሉን በማስመልከት ያዘጋጀነዉ ነገር ሲያይ ልዩ ደስታ ነበር የሚታይበት። እዚህ ጋር ያቅማችንን የሚያስደስት ነገር እንፍጠር በሚል የኬክ መቁረስ ፕሮግራም አድርገናል። በዝግጅታችን በጣም ተደስቶአል። ከዝያም ፕሮግራሙ እየደመቀ እየደመቀ ነዉ የሄደዉ። መጨረሻ ላይ የነበረዉ ነገር ራሱ በድምጹ እንዴት እንደገለጸዉ ሁሉ ሰዉ አይቶታል። በጣም ድንቅ ነበር። በአርቲስት ማሕሙድ አህመድ ገጽታ ላይ ሁለቱንም ነገር ነበር ያነበብነዉ።»

ለአንጋፋዉ ድምጻዊ ለክብር ዶክተር ማሕሙድ አህመድ ወደ ጀርመን መምጣት የመጀመርያ እንዳልሆነ ተናግሮአል።

«ጀርመንን የማዉቀዉ ከ 1992 ዓ.ም ጀምሮ ነዉ። ከዝያም በኋላ ለብዙ ጊዜ መጥቻለሁ። አሁን ደግሞ ለሽልማቱ መጥቼ ነዉ። ዝግጅቱን ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ የለፉትን በሙሉ ላመሰግን እወዳለሁ። »

ከሙዚቃዉ ዓለም አልወጣህም ? አሁንም ታዜማለህ?

« እንግዲህ ትንሽ ወደመዳከሙ ደረጃ ብንደርስም ሙዚቃ አያስረጅም። ሙዚቃ ጡረታ አይፈልግም፤ ልጦር ብዬ ብወጣም ሙዚቃ አይለቅም። ስለዚህ ከሙዚቃ ጋር አብረን እንኖራለን፤ አብረንም ኖረናል።»    

 የኢትዮጵያ አርቲስቶች ማዕከል ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ የክብር ሽልማትን የሰጠ ሲሆን ከዚህ ቀደም፤ ደራሲን ገጣሚ አርቲስት አያልነኽ ሙላትን፤ አርቲስት ዶ/ር ዳዊት ይፍሩን፤ ሁለገቧ የጥበብ ንግስት ዓለምፀሃይ ወዳጆን፤ አርቲስት አሰለለፈች አሽኔን፤ አርቲስት ተረፈ ለማን፤ ቀራፂ ብዙነህ ተስፋን፤ አርቲስት ሃረገወይን አሰፍን፤ አርቲስት እመቤት ነጋሲን፤ አርቲስት አብራር አብዶን፤ አርቲስት ወንዲ ማክን፤ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየዉ አርቲስት አብርሃም አስመላሽን፤ አርቲስት ማኅሌት ደመረን፤ እስከዛሬ በማኅበሩ ወደ ፍራንክፈርት ከተጋበዙ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች መሆናቸዉን አቶ ተፈሪ ፈቃደ ተናግረዋል። ለድምጻዊ ማሕሙድ አህመድ የክብር ሽልማት የተሰጠ እለት በሙዚቃ ተሸላሚዉ የማሕሙድ አህመድ እና ፀሃዬ ዮሐንስ ታዳሚዉን በሙዚቃቸዉ ሲያስደስቱ ማምሸታቸዉንም ገልፀዋል።

አርቲስት አብርሃም ወልዴ፤ ፍራንክፈርት ጀርመን

አርቲስት አብርሃም ወልዴ፤ ፍራንክፈርት ጀርመን

« በጣም የሚገርም ነገር ነዉ። ጋሽ ማሕሙድ እንደገና አዲስ ሙዚቃ ማዉጣት የሚችል ነዉ። የሚደንቅ ዓይነት ድምጽ ነዉ የታየዉ እዝያ ቦታ ላይ። አንድ 76 ዓመት እድሜ ካለዉ ሰዉ አዲስ ሙዚቃ አልብም ሲሰራ እንደነበረዉ ዓይነት ጊዜ ዘፈኖቹን እንዳለ ነዉ ያወረዳቸዉ። ያ ሕዝቡን እጅግ ነዉ ያስደነቀዉ ። እሱ ሲዘፍን በነበረበት ወቅት አዳራሽ ዉስጥ የነበረዉ ስሜት ማየት ይቻላል። አርቲስት ፀሃዬ ዮሐንስን የወሰድንም እንደሆነ የታየዉ ይሄዉ ነዉ። የበሰሉ የአርቲስት ዉጤቶች የታየበት መድረክ ነበር።»          

በዝግጅቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኘዉ አርቲስት አብርሐም ወልዴ ማሕሙድ አሕመድ በሕይወት ዘመኑ ስላበረከታቸዉ ሥራዎች በፅሑፍ ለታዳሚ አቅርቦአል። ቡዙ ስራ ላበረከቱ ባለሞያዎች ክብር መሰጠቱ እጅግ የሚያስደስት ነዉ ሲልም አርቲስት አብረሃም ገልፆአል።

« በጣም ነዉ ደስ ያለኝ። ከምንም ነገር በላይ መጀመርያ ይህን ሞያ ለዚህ ዘመን ለዚህ ጊዜ ያቆዩልንን ሰዎች ማክበር ሲጀመር እኔ በጣም የምመኘዉ እና የምፈልገዉ ነገር ስለሆነ ከምንም ነገር በላይ አስደስቶኛል። ሁለተኛ ደግሞ የጋሽ ማሕሙድን ልደት ማክበርም ሆነ የዓመቱ ታላቅ ሰዉ በሚል መሸለሙ በጣም አስደስቶኛል። አዘገጃጀቱ ትኩረት የሰጡበት መሆኑን ሳስበዉ ከምንም ነገር በላይ በጣም ስሜት የሚነኩ ነገሮች፤ በጣም ደስ የሚሉ ነገሮች ብዙ ጊዜ ብዙ ዝግጅቶች ላይ የማላያቸዉ ነገሮች አይቻለሁ። በዚህ በኩል በጀርመን የኢትዮጵያ አርቲስቶች ማኅበር ማዕከል ሊቀመንበር አቶ ተፈሪን ትልቅ ስራዉን ልፋቱን ድካሙን ያየበት ከምንም በላይ አስደስቶኛል።» 

ለዝግጅቱ መሳካትና የሚሰበሰበዉ ገንዘብ በአገር ቤት ድጋፍ ላጡ አንጋፋ አርቲስቶች መደጎምያ እንዲዉል በተለይ በፍራንክፈርትና አካባቢዋ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸዉን የማዕከሉ ሊቀመንበር አቶ ተፈሪ ተናግረዋል። በተለይ ፎቶግራፍና ፊልሞችን መመቅረፅ ለማኅበሩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉት ባዝ ፎቶ በመባል የሚታወቀዉ ድርጅት ተጠሪ አቶ ብሩክ አንዳርጌ ሰይፈ ስላሴ ምስጋና ተበርክቶላቸዋል። በኮመዲ ስራዎቹ የሚታወቀዉ የባላገሩ አይዶል አዘጋጅና አቅራቢ አርቲስት አብርሃም ወልዴ በፍራንክፈርት ከአንጋፋው ድምጻዊ ከክቡር ዶክተር ማሕሙድ አህመድ፤ እና ፀሃዬ ዮሃንስ የነበረዉን ቆይታ ይናገራል።

«በዚህ አጋጣሚ እኔ ጋሽ ማሕሙድ እና ፀሃዬ ዮሃንስ አብረን አንድ ሆቴል ነበርን። የነበረ ፍቅር የነበረዉ ነገር ኪነ-ጥበብ ዉስጥ ያለ ሕይወት በራሱ በአኗኗራችን ራሱ ብዙ ነገር መገለጽ ያለበት ይመስለኛል። እና ለፀሃዬ ዮሃንስም ያለኝን ትልቅ አክብሮት እና ፍቅር በዚህ አጋጣሚ ልገልጽ እፈልጋለሁ። ምክንያቱም በአየሁት ጊዜ ዉስጥ ለጋሽ ማሕሙድ ያለዉ አክብሮት ለኔ ደግሞ እንደ ታላቅ ወንድም የነበረዉ ነገር የምመኘዉ ነገር ነዉ ያየሁት እና እግዚአብሔር  ወደፊት የሁላችንንም ልብ አንድ ያድርግልን፤ ሃገራችንንም አንድ ያድርግልን ልባችንም አንድ ያድርግልንና የፍቅር ሰዎች ያድርገን እላለሁ።»   

በዝግጅቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኘዉና አጠር ያለ ቃለ-ምልልስ የሰጠን አንጋፋዉ ሙዚቀኛ ፀሃዬ ዮሃንስ፤ ክብር ለሚገባዉ ክብር እንስጥ ላለዉ ማኅበር ምስጋና ይገባዋል ሲል አመስግኖአል።

Deutschland Auszeichnung für Mohamud Ahmed

ድምጻዊ ማሕሙድ አህመድ እና በፍራንክፈርት ጀርመን የኢትዮጵያዉያን የኪነጥባበባት ማዕከል ሊቀመንበር አቶ ተፈሪ ፈቃደ

«የምሽቱ ዝግጅት በጣም ደስ የሚል ነበር። የማሕሙድን የ 76 ኛ የልደት በዓልና የኢትዮጵያን ሕዝብ ያገለገለበትን የአገልግሎት ዘመን አክብሮት ነዉ የሰጠነዉ፤ ሕዝቡም አክብሮታል። በጣም ደስ የሚል ዝግጅት ነበር። የሰዉ ልጅ በሕይወቱ ቆሞ እንዲህ አክብሮትን ሲያይ በጣም ደስ ይላል። ያልተለመደ ነገር ነዉ እየተለመደ የመጣዉ። ፍራንክፈርት ዉስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያኖች ይሄን ነገር ጀምረዉታል። ሰዉ ቆሞ ለሰራዉ እንዲህ ክብር ሲሰጠዉ፤ ቆሞ ሲጨበጨብለት እና አገር ላይ የተለመደ ስላልሆነ ይሄ ነገር፤ እየተለመደ በመምጣቱ በመጀመሩ ደስ የሚል ነገር ነዉ። ማሕሙድ ከ50 ዓመት በላይ ነዉ ያገለገለዉ፤ እንደዚህ ሲከፈል ማየት ደስ ይላል፤ በዚህም ዝግጅት በመሳተፊ በጣም ደስ ብሎኛል። ይሄንንም በጎ ነገር ለሰሩ ኮሚቴዎች በጣም በጣም ምስጋና ይገባቸዋል። ኢትዮጵያ ዉስጥ ከ 20 እና ከ 30 ዓመት በላይ ያገለገሉ፤ አርቲስቶች መጠግያ የሌላቸዉ አርቲስቶች ቤት ክራይ መክፈል የማይችሉ አርቲስቶችን ለመደጎም ተፈልጎ ነዉ ይህ ዝግጅትም የተዘጋጀዉ። እና እዚህ አክብረሽ እዛ ደግሞ መርዳት በሁለቱም በኩል ትልቅ ጥቅም ያስገኘ ነዉ። ትልቅ ነገር ነዉ እየተደረገ ያለዉ። በዚህ ዝግጅት ላይ በመሳተፊ በጣም ደስ ይላል ደስ ብሎኛል።»

ማሕሙድ አህመድ  “መቼ ነው? ዛሬ ነው? ሀገሬን  ኢትዮጵያን የማየው?” እያለ አዚሞአል። አብሮ አልቅሷል ዳር ድንበርን ከሚስጠብቁት ጋር በጋራ በብሔራዊ ስሜትን ቀስቅሶአል፤ ከፊት ሆኖ መርቶአልም። ድምጻዊ ማሕሙድ አህመድ በሙዚቃዉ ዓለም 56 ዓመት እንደኖረ አጫዉቶናል።

«በሙዚቃ ዓለም 56 ዓመት ሆነኝ።»  እና የሙዚቃ ሕይወትህን እንዴት ትገልፀዋለህ? እኔ አሁን እኔነቴን የሚገልፅ ስለኔ ሕዝብ ሊናገር ይገባል፤ እንጂ እኔ እኔነቴን የምገልጽበት መንገድ ያለ አይመስለኝም። ሕዝብ ያለዉን ፍቅርና ያለዉን አክብሮት ገልፆልኛል፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጠቅላላዉ ከአንተነት ወደ አንቱነት ስላደረሰን አመሰግናለሁ። እኔ በዶይቼ ቬለም በኩል እንዲደርስልኝ የምፈልገዉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአንተነት ወደ አንቱነት ላደረሰኝ በጠቅላላ አክብሮቱን ስለገለፀልኝ ትልቅ ባለ ዉለታዬ ሕዝብ ነዉ። አሁንም ዋሴም ጠበቃዬም የኢትዮጵያ ሕዝብ ነዉ።»

    

ጋሽ ማሕሙድ አህመድ በመጨረሻ ልጠይቅህ አልነዉ፤ ለኛ ለተኪዉ ትዉልድ በሁሉ ዘርፍ ምን ምክርህን ትሰጠናለህ? «ምክር ከባድ ጥያቄ ነዉ። ለማንኛዉም መከባበርን የመሰለ ነገር እንደሌለ ነዉ እኔ የማዉቀዉ። ትንሹንም ትልቁንም በማክበር ነዉ ወደ ትልቅ ደረጃ የሚደረሰዉና ይህንን እንዲከተሉ ነዉ የምጠይቀዉ»  

አክብሮትን ለሰጡ ክብር ይገባቸዋል ብለዋል፤ ሲሉ ተጋባዥ አርቲስቶቹ በሙሉ ተናግረዋል። ጤና እድሜ ቃለ-ምልልስ ለሰጡን ለአንጋፋዉ ድምጻዊ ለክብር ዶክተር ማሕሙድ አህመድ፤ ለድምጻዊ ፀኃዬ ዩሐንስና ለአርቲስት አብርሃም ወልዴ እንመኛለን።  

 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic