የሕዝብ ጥያቄ በምንጃር ሸንኮራ | ኢትዮጵያ | DW | 09.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የሕዝብ ጥያቄ በምንጃር ሸንኮራ

የተለያዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማንሳት አቤቱታዉን ለማሰማት አደባባይ የወጣዉ በሰሜን ሸዋ ዞን የምንጃር ሸንኮራ ሕዝብ ዛሬም የክልሉን ባለስልጣናት ማብራሪያ ለመስማት ተሰብስቦ መዋሉን ነዋሪዎች አመለከቱ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:41

ዛሬም ከባለስልጣናት ምላሽ ለማግኘት ሲጠብቁ ዉለዋል፤

 ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ከሁለት ሳምንታት በላይ የመብራት መጥፋት፣ ለኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ከገበሬዎች ለተወሰደ መሬት ተመጣጣኝ ካሣ አለመክፈል፤ ለወጣቶች የሥራ ዕድል የተመደበ በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ሥራ ላይ አለመዋል፤ እና ሌሎችም ችግሮች ሕዝቡን ወደ አደባባይ እንዲወጣ እንዳደረጉት አስረድተዋል።

የአካባቢዉ ሕዝብ በመልካም አስተዳደር እጦት ለችግር መዳረጉን ያነጋገርናቸዉ በሰሜን ሸዋ ዞን የምንጃር ሸንኮራ ነዋሪዎች ይናገራሉ። ከ15 ቀናት በላይ የመብራት አገልግሎት እንደሌላቸዉ፤ ለኢንዱስትሪ ፓርክ የተከለለ መሬት ለገበሬዎቹ ተመጣጣኝ ካሣ አልተሰጠበትም፤ የግብር መጠን ጥያቄ እና ለወጣቶች የተመደ እነሱ እንደሚሉት ከ20 ሚሊየን የሚበልጥ ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ አልዋለም የሚሉ ቅሬታዎችን ትናንት አደባባይ ወጥተዉ አሰምተዋል። በወቅቱ በተፈጠረዉ ግጭትም ንብረትነቱ የክልሉ መስተዳደር እና የአንድ ቻይና ባለሀብት የሆነ የቺፕዉድ ፋብሪካ መቃጠሉንም የአካባቢዉ ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። በዚህ ወቅትም በአቅራቢያዉ የሚገኝ የስንዴ ማሳም በእሳት መበላቱንም ገልጸዋል። ዛሬም በአካባቢዉ ምን ዓይነት ሥራ እንደሌለ እና ሕዝቡም ላቀረበዉ ጥያቄ ባለስልጣናት ማብራሪያ ይሰጣሉ በመባሉ በከተማዋ ኳስ ሜዳ ላይ ከጠዋት ጀምሮ ሲጠብቅ መዋሉን እኩለ ቀን አለፍ ብሎ በስልክ ያገኘኋቸዉ የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዉልኛል።

የመንግስት ባለስልጣናትን ማብራሪያ ለመስማት በስፍራዉ ከተሰበሰቡት የከተማዋ ነዋሪዎች አንዱ እንደሚሉትም ሕዝቡን ያነጋግራሉ የተባሉት ባለስልጣናት በጠባቂዎቻቸዉ ተከበዉ በስፍራዉ ቢገኙም ወደሕዝቡ አልቀረቡም።

ትናንት ከሰልፉ በኋላ በተፈጠረ ረብሻ ንብረት ከመቃጠሉ ሌላ ሁለት ሰዎች ቆስለዉ ሃኪም ቤት መግባታቸዉንም የአካባቢዉ ነዋሪዎች ይናገራሉ። የተጎዱትም በጥይት እንደሆነ ነዉ የሚያስረዱት።

የአማራ ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁንን በስልክ ለማግኘት ብንደዉልም ስብሰባ ላይ መሆናቸዉን ገልጸዉ፤ በፌስ ቡክ ገጻቸዉ ላይ ያሰፈሩትን መጠቀም እንደምንችል ገልጸዉልናል። ከትናንት ጀምሮ ጉዳዩን በመከታተል ዝርዝር መረጃ እንደሚያቀርቡ በፌስቡክ የገለጹት አቶ ንጉሡ ዛሬም ሀብት ማዉደም ትልቅ ስህተት፣ ትልቅ ጥፋት ሲሉ ረዘም ያለ ጽሑፍ አስፍረዋል። በቂ የሥራ ዕድል ለወጣቶች አልተፈጠረም የሚለዉ ጥያቄ መልካም ሆኖ ሳለ፤ ትናንት በቃጠሎ እና ንብረት ዉድመት የደረሰበት ፋብሪካ በ70 ሚሊየን ካፒታል ሥራ መጀመሩን አብራርተዋል። ፋብሪካዉ ለአካባቢዉ ወጣቶች ሥራ በመፍጠር 233 ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ያመቻቸ እንደነበርም ጠቅሰዋል። በትናንቱ አጋጣሚ ከዚህም ሌላ ወደ አዉሮፓ ሊላክ የተዘጋጀ 3 ኮንቴይነር ከሰል መቃጠሉን፤ የአረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርክም ጥቃት ደርሶበት አንድ ጀነሬተር መቃጠሉንም አመልክተዋል። እንዲያም ሆኖ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የምንጃር ሸንኮራ ነዋሪዎች ከባለስልጣናት ተገቢዉን ማብራሪያ ካላገኙ የባሰ ነገር ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች