1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕዝቡ ጥያቄ እና የልኂቃኑ መልስ

ዓርብ፣ መስከረም 9 2012

ምርጫ 97 በውዝግብ ከተጠናቀቀ በኋላ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተስፋ እንደገና ወደኋላ ተመልሷል። የተቃዋሚ ቡድኖች የትግል ስልትም እንደዚሁ ተቀይሮ ከፊሉ በስደት፣ከፊሉ ነፍጥ አንስቶ፣ ቀሪው ተበታትኖ ስርዓቱን በብዙ አቅጣጫ ሲታገሉት ከርመዋል። ገዢው ፓርቲም ይህንን የተቃዋሚዎቹን ጥረት ለማደናቀፍ በአዋጅ እና በአሠራር ጠብ እርግፍ ሲል ከርሟል።

https://p.dw.com/p/3Px8h
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

በፍቃዱ ኃይሉ

ከ2010 አጋማሽ ወዲህ የተከሰተው የለውጥ ባቡር እነሆ ዓመት ከመንፈቅ ሆነው። ኢሕአዴግ “ጥልቅ ተሐድሶ” ለማካሔድ የወሰነው በታኅሣሥ 2010 የ17 ቀን ስብሰባ ነበር። ነገር ግን እስካሁን መድረሻው አልለየለትም። ከመጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ “ለውጥ የለም” ከሚለው ‘ክህደት’ ጀምሮ “ለውጡ መሥመሩን ስቷል” እስከሚል ስጋት ድረስ እያነጋገረ ነው። “የለውጡ አጀንዳ ምንድን ነበር?” የሚለው ጥያቄ ላይ ግን ይህ ነው የሚባል መሥማሚያ የለም። ስለሆነም እያንዳንዱ ትችት ወቅታዊ ክስተቶችን እየተከተለ ነው እንጂ መነሻ እና መድረሻ የለውም። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ይህንን ክፍተት መሙላት ነው።

 

የሕዝብ ጥያቄዎች

 ለውጡ ስጋት የተሞላበት ነበር። እነሆ ይህ እየሆነ ዓመት ከመንፈቅ ከተጓዘ በኋላ ጥያቄዎቹ ምን መልስ አገኙ? መጀመሪያ ጥያቄዎቹን በአምስት ጨምቀን እንመልከታቸው።  

 

1ኛ፣ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች - 70 ከመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ከ35 ዓመት ዕድሜ በታች ናቸው። ወጣቶች ቢበዙም የወጣቶች ሥራ አጥነትም ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ነበር። በተጨማሪም የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና ፍትሓዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖር ደጋግመው ይሰሙ የነበሩ ብዙኀንን ያማረሩ ችግሮች ነበሩ።  

2ኛ፣ የሲቪክ ምኅዳሩ መጥበብ - የሲቪል ማኅበረሰቦች ሕግ፣ የፀረ ሽብርተኝነቱ አዋጅ እና ሌሎችም በነጻነት የመሰብሰብ፣ የመደራጀት እና የመጻፍ እና የመናገር ነጻነቶችን ሳይቀር በሕግ ሰበብ በማገድ የፖለቲካ እና ሲቪክ ምኅዳሩ እጅግ የጠበበ እንዲሆን በማድረግ ገዢው ፓርቲን ብቻ አውራ ማድረጉ ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሮ ነበር።

3ኛ፣ ክልላዊ ተመጣጣኝ ውክልና አለመኖር - በኢሕአዴግ ውስጥ ሕወሓት የነበረው የጎላ ተዋናይነት ሌሎች ድርጅቶች ክልላቸውን በሚመጥን ቁመና በፌዴራሉ ወካይ ሆነው አለመገኘታቸው ሌላኛው ቅሬታ ነበር። ሌላው ቀርቶ አራቱ የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ከወጡባቸው ክልሎች በቀር ሌሎቹ አገሪቱን መምራት የሚችሉበት የፓርቲ መዋቅር አልነበረም።

4ኛ፣ ክልላዊ ነጻነት - ክልሎች በፌዴራል መንግሥቱ ሙሉ የበላይነት ሥር በመሆናቸው ነጻነታቸው እጅግ የተገደበ ነበር የሚለው ሌላኛው ቅሬታ ነበር።

5ኛ፣ የአገራዊ አንድነት መሸርሸር - በፖለቲካዊ ውጥረቶች ሳቢያ ነውጦች እና አክራሪነት እየተንሰራፋ በመምጣቱ የአገሪቱ አንድነት አደጋ ላይ ወድቋል የሚል ከፍተኛ ስጋትም በብዙዎች ዘንድ አንዣንብቦ ነበር።

 

ሒሳቡ ሲወራረድ

አምስቱ ሕዝባዊ ጥያቄዎች በጣም ሰፊ እና የረዥም ጊዜ ጥያቄዎች እንደመሆናቸው በአጭር ጊዜ ምላሽ ያገኛሉ ብሎ መገመት የዋሕነት ይሆናል። ሆኖም፣ የለውጡ ጊዜ ለነዚህ ጥያቄዎች መሠረት ይጥላል፣ አልያም ማስታገሻ የሚሆን እርምጃ ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የገዢው ፓርቲ እና በለውጡ የመሳተፍ ዕድል የቀረበላቸው የተቃዋሚ ቡድኖች ልኂቃን የሠሩትን እና እየሠሩ ያሉትን በአምስቱ ነጥቦች እንደሚከተለው መገምገም ይቻላል።

1ኛ፣ እምብዛም ያልተለወጠ የኢኮኖሚ ሁኔታ - የሥራ አጥነቱ በነበረበት እየረገጠ ነው። የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ በአንፃሩ የተሻሻለ ቢሆንም፣ የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት ግን በሚያስደነግጥ ፍጥነት እየጨመሩ ነው። የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ዛሬም ብዙኀንን እያማረሩ ነው።

2ኛ፣ ምኅዳሩ ከነችግሩ በእጅጉ ሰፍቷል - ምናልባትም የተለየ የለውጡ ስኬት ሊባል የሚችለው የምኅዳሩ መስፋት ነው። ተቃዋሚዎች፣ ሚዲያዎች እና ሲቪል ማኅበራት ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ በነጻነት እየተንቀሳቀሱ ነው። የሲቪል ማኅበራት እና የምርጫ ሕግጋት ተሻሽለዋል። የሚዲያ ሕግጋት ክለሳ ላይ ናቸው። የፀረ ሽብር ሕጉ ቢከለስም እስካሁን ስላልፀደቀ አሮጌው ጥቅም ላይ ውሎ የምኅዳሩ መስፋት ላይ ጥላውን ጥሏል። ክልሎች የፌዴራሉን ያክል ክፍት አለመሆናቸው፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ኀይሎች ከሕግ በላይ መፈርጠማቸው አደገኛ ሁኔታዎች ሆነው ብቅ ብለዋል።

3ኛ፣ የክልሎች የኮታ ውክልና - በሚኒስትር እና በሚኒስትር ዲኤታ ማዕረግ የተሾሙ የፌዴራል ሠራተኞች የመጡበት ክልል እየተጠና ከሕዝብ ቁጥራቸው ጋር እንዲመጣጠን ተደርጓል። በዚህ ረገድ የኮታ ውክልና ተሟልቷል ማለት ይቻላል። ሆኖም በሕዝባዊ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ እውነተኛ ውክልና መጥቷል ማለት ይቸግራል። አብዛኛዎቹ ሹመኞች በብሔር ክልሎችን የሚወክሉ ልኂቃን እንጂ ከየአካባቢው የተውጣጡ ወኪሎች አይደሉም።

4ኛ፣ ፌዴራሉን ያገለለ ክልላዊ ነጻነት - ከሁሉም አሳሳቢ የሆነው የክልሎቹ የነጻነት ልክ ነው። የፌዴራሉ እና የክልሎቹ የጋራ እና የተናጠል ሥልጣን ልዩነቱ የት እንደሆነ እስከሚቸግር ድረስ ክልሎቹ ነጻነታቸውን አውጀዋል። ይህንንም ብዙዎች ከወዲሁ “ፌዴራሊዝም” ሳይሆን “ኮንፌዴራሊዝም” እያሉ እየጠሩት ነው። የበለጠ አሳሳቢው ደግሞ ክልሎቹ ፌዴራሉ ቃል የገባውን የለውጥ ሒደት ለማስፈፀም እንቅፋት መሆናቸው ነው። ክልሎቹ የገዢው ፓርቲ የውስጥ ለውስጥ ፉክቻ ማሳያ ሆነዋል። ይህ ችግር ኢሕአዴግ ራሱን አክስሞ ውሕድ ፓርቲ ለማምጣት በሚወስንበት ጊዜ ሊባባስ እንደሚችልም ይገመታል።

5ኛ፣ እንደአገር የመፈረስ አደጋ ተባብሷል - በአራተኛ ደረጃ እንዳየነው የክልሎቹ እንደኮንፌዴሬት አባላት ለመሆን መሞከራቸው እና የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ፍላጎታቸውን ለማስፈፀም አመፃን እንደ ስልት መጠቀማቸው እንዲሁም መንግሥት የተለያዩ ግጭቶችን አስቀድሞ መከላከል አለመቻሉ የኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ላይ ወድቋል የሚለውን ስጋት አባብሶታል።

 

ከሕዝባዊ ጥያቄዎቹ አንፃር የፖለቲካ ልኂቃኑ የሰጡትን ምላሽ ስንመለከተው ተስፋ ሰጪም፣ ተስፋ አስቆራጭም ሁኔታዎች ፊታችን ይደቀናሉ። ምናልባትም ከመቶ ሃምሳ ነጥብ የሚያስገኝ የለውጥ ሒደት ነበር ማለት ይቻላል። አሁንም ለውጡን ግብ የማድረሻ መንገዶች አሉ። ለአፋጣኝ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ቀዳሚው ነው። ኢሕአዴግ ከአባል ፓርቲዎቹ ጋር በመግባባት ክልሎች እና ፌዴራሉ በትብብር እና በመመጋገብ እንዲሠሩ ማድረግ ወሳኝ እርምጃ ነው። የተቃዋሚ ቡድኖች በማንኛውም ሁኔታ ጥያቄዎቻቸውን እና የፖለቲካ ንቅናቄያቸውን በሰላማዊ ማራመድ ይኖርባቸዋል። እነዚህ ከተስተካከሉ ለረዥም ጊዜ ጥያቄዎች የአጭር ጊዜ ምላሽ ሳይዘገይ ማግኘት ይቻላል።

 

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሐፊው እንጂ የዶይቸ ቬለን አቋም አያንጸባርቅም።

በፍቃዱ ኃይሉ