የሕንድ የኤኮኖሚ ዕርምጃና ችግሩ | ኤኮኖሚ | DW | 03.11.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የሕንድ የኤኮኖሚ ዕርምጃና ችግሩ

ሕንድ እንደ ቻይና ሁሉ የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት በማድረግ ላይ ከሚገኙት ቀደምት አገሮች አንዷ ናት። ሆኖም ደቡብ እሢያይቱ አገር ባለፈው አንድ አሠርተ-ዓመት በምጣኔ-ሐብት ልዕልና አቅጣጫ ታላቅ ዕርምጃ ታድርግ እንጂ ዜጎቿ በሙሉ የዕድገቱ ተጠቃሚ ሆነው አይገኙም።

default

አንድ ሚሊያርድ ሕዝብ የሚኖርባት ሕንድ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በአማካይ 8 በመቶ ዕድገት የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕርምጃ ስታደርግ ቆይታለች። በዓለም ላይ ታላቋ የዴሞክራሲ አገር በዚሁ ዕድገቷ ከቻይና ጋር በመጣመር ቀደምቷ ናት። የዘርፉ ጠበብት ከተኛችበት በመነሣት ላይ ያለች ግዙፍ አገር የሚሏት የሕንድ የኤኮኖሚ ዕድገት ማበቡ ታዲያ ያለ ምክንያት አይደለም። አገሪቱ ገና ከዛሬው በኮምፒዩተር ቴክኖሊጂ፣ በጠፈር ሣይንስና በባዮ-ቴክኖሎጂ ምርምር በዓለምአቀፍ ደረጃ ቀደምት ስፍራን ለመያዝ የበቃች ናት።

በዓለም ላይ ከሶሥት አንዱ የኮምፒዩተር ጠቢብ ዛሬ ሕንዳዊ ነው። ግን በዚያው መጠን ከሶሥት አንዱ ማንበብና መጻፍ አይችልም። መሃይም ነው። ቦምቤይንና ዴልሂን በመሳሰሉት በዘመናዊ ሕንጻዎች ባሸበረቁት ታላላቅ ከተሞች ጥቂቶች በተትረፈረፈ ሃብት በቅንጦት ይኖራሉ። 250 ሺህ የአገሪቱ ዜጎች ግን ኑሯቸውን የሚገፉት ከድህነት መስፈርት በታች ነው። ይህ ሁሉ የካሽሚር ውዝግብና የሌሎች የተሰንጣሪ ንቅናቄዎች የፖለቲካ ችግር ታክሎበት የወደፊቱን ሂደት ቀላል አላደረገውም። ይሁንና የአገሪቱ ባለሥልጣናት ሕንድ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዓለም ላይ ድሆች ከሚባሉት አገሮች ሰፈር ወጥታ ከቻይና ጎን የእሢያ የዕድገት መንኮራኩር ለመሆን መብቃቷን ብዙ ነው የሚኮሩበት።

ሕንድ የኑክሌያር ሃይል ባለቤትም ስትሆን ይህም ብዙ በራስ መተማመን እንዲያድርባት ያደረገ ጉዳይ ነው። ሁኔታው የጸጥታው ም/ቤት ቋሚ ዓባልነት የይገባኛል ጥያቄ እንድታነሣ አብቅቷታል። የመንግሥቱ ኮንግሬስ ፓርቲ ፖለቲከኛ ራሺድ አልቪ በቅርቡ አገሪቱ 60ኛ የነጻነት በዓሏን ባከበረችበት ወቅት ስለዚሁ እንዲህ ነበር ያሉት። “በአኔ ዕምነት ያለፉት 60 ዓመታት ታላቅ ስኬት፤ ዓለምም አውቆ ሊቀበለው ይገባል የዴሞክራሲ ስርዓት እንቆናጠጥ ማድረግ መቻላችን ነው። ዴሞክራሲያችን በነዚህ ስድሥት አሠርተ-ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ ከየትኛውም ጋር መፎካከር በምንችልበት ሁኔታ ተጠናክሯል ለማለት እደፍራለሁ”

እርግጥ በወቅቱ የሚታየው አስደናቂ ዕድገት ዋነኛ ተጠቃሚዎች ከተሞችና በዚያው የሚኖሩት የመካከለኛው ሕብረተሰብ መደብ ዓባላት ብቻ ናቸው። የኤኮኖሚው ዕድገት ተዓምር በአንጻሩ የገጠሩን አካባቢ ብዙም አላዳረሰም። ለነገሩ ግን አንዴ ታላቁ የአገሪቱ የነጻነት አባት ማሃትማ ጋንዲ እንዳሉት የሕንድ ሕልውና የሚከሰተው በመንደሮቿ ገጽታ ነው። በዕውነትም ከ 550 ሺህ የሚበልጡ መንደሮችን የጠቀለለው ግዙፍ የገጠር አካባቢ ሳይለማ ለዕድገቱ ዘለቄታ ዋስትና ሊኖር አይችልም። በርካታ የኤኮኖሚ ጥበብት ዛሬ ደግመው ደጋግመው የሚያስጠነቅቁትም ይህንኑ ነው።

በዓለም ላይ ዝነኛ እየሆኑ የሄዱት የሕንድ የዘመናዊ ኤሌክትሮኒክ ጥበብና አገልግሎት ሰጭ ዘርፎች በሙሉ ሰፍረው የሚገኙት በከተሞች ነው። በነዚህ ዘርፎች በሙያ ለመሰማራትም ትምሕርት ያስፈልጋል። ለገጠሩ ነዋሪ የሚደረስባቸው አይደሉም። ስለዚህም የእርሻ ልማትን ዘመናዊ ለማድረግ የሚረዳ አጠቃላይ የዕድገት ጽንሰ-ሃሣብ መፍጠሩ የሚመረጠው መንገድ ሆኗል። ዛሬ ሕንድ ውስጥ 120 ሚሊዮን ገበሬዎች ይኖራሉ። ከጠቅላላው የአገሪቱ 1.1 ሚሊያርድ ሕዝብ ሁለት-ሶሥተኛው ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በእርሻው ኤኮኖሚ ላይ ጥገኛ ነው። ይሁን እንጂ የእርሻው ዘርፍ ከአገሪቱ የኤኮኖሚ ሃይል አንጻር ያለው ድርሻ ከሃያ በመቶ አይበልጥም። የብዙዎች ገበሬዎች ኑሮ ብርቱ የሕልውና ትግል የተጫነው ሆኖ ነው የሚገኘው።

የሕንድ የእርሻ ልማት ሲበዛ በአየር ሁኔታ ላይ ጥገኛ ነው። የዝናቡ ወራት ከዘገየ ወይም ከመጠን በላይ ብዙ ዶፍ ከወረደ ገበሬው አብዛኛውን አዝመራውን ያጣል። ከዚሁ በተጨማሪ ዝግ ሆኖ ከቆየ በኋላ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ለውጭው ዓለም የተከፈተው የሕንድ ገበያ በመንግሥታት በሚደጎመው የምዕራቡ ዓለም ምርት መጥለቅለቁም ለአገሬው ገበሬ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው የሆነው። በሕንድ የሚታረስ መሬት ትልቅም ሆነ ትንሽ በዘልማድ ከአባት ወደ ልጆች የሚተላለፍና የሚከፋፈል በመሆኑ የገበሬው መሬት ሲበዛ ትንሽ ነው። በመሆኑም ፉክክሩን መቋቋም አይቻልም።

በዚሁ የተነሣ ብዙ ገበሬዎች ሰፊ ወለድ ከሚጠይቁ በዝባዦች ብድር በመውሰድ ከችግራችው ለማምለጥ ይሞክራሉ። ሆኖም የተበደሩትን ገንዘብ ያህል የሚሆነውን ወለድ መክፈል ስለማይችሉ በመጨረሻ የሚቀራቸው ራሳቸውን እስከመግደል መድረስ ነው። ይህ በገጠር አካባቢዎች ያልተለመደ ነገር አይደለም። የሕንድ ባለሥልጣናትም በተለያዩ ዘርፎች የሚታየው የኤኮኖሚ ዕድገት የገጠሩ ልማት ሳይታከልበት ለአገሪቱ ዘላቂ ዕርምጃ መቅሰፍት መሆኑን ውሎ-አድሮ ተረድተውታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ማንሞሃን ሢንግ ባለፈው ነሐሴ ወር የነጻነት በዓል ንግግራቸው ማዕከላዊ ጉዳይ ያደረጉት ይህንኑ የገጠሩን ልማት ነበር።

የኒው ዴልሂ መንግሥት እንደሚለው የእርሻ ዘርፉን ምርታማነትና ጥራት ወደፊት ማራመዱ የመጪዎቹ ዓመታት ዓቢይ ተግባር ነው። በራስ ሕልውና ከተወሰነ ለተፎካካሪነት ወደሚያበቃ ምርታማ የእርሻ ልማት ዘይቤ መተላለፉ ቢቀር በሃሣብ አዲሱ አቅጣጫ ሆኗል። የሕንድ የእርሻ ልማት ዕድገት በወቅቱ በዓመት ከአንዲት በመቶ ጥቂት ቢበልጥ ነው። ይህ ደግሞ የኒው ዴልሂ የንግድና ኢንዱስትሪ ም/ቤት የምጣኔ-ሐብት ጠቢብ አንጃን ሮይ እንደሚሉት ተገቢውን ስልታዊ ዕቅድ በተግባር በማዋል ዘርፉ እንደተቀረው መስክ የዕድገት አስተዋጽኦ እንዲኖረው ማራመዱን ግድ ያደርገዋል።

“የሚመረጠው ስልታዊ ዘዴ በመላ አገሪቱ የእርሻ ውጤቶችን ወደ ምርት የሚለውጡ ፋብሪካዎችን ማቋቋሙ በሆነ ነበር። ለምሳሌ በማቀዝቀዣ ማከማቻዎች ጉድለት የተነሣ አርባ በመቶው የእትክልትና የፍራፍሬ ምርት ከንቱ ይሆናል። ፋብሪካዎቹ በአገሪቱ ዙሪያ በአነስተኛ ደረጃ ሊቋቋሙ ይችላሉ። ይህ ደግሞ በገጠር አካባቢዎች የሥራ መስኮችን የሚከፍትና ብልጽግናንም የሚያስከትል ነገር ነው። በአጠቃላይ ለበለጠ የኤኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ ሊሆን ይችላል”

እርግጥ ከዚህ ግብ ለመድረስ በገጠር አስፈላጊው መዋቅር እንዲስፋፋ መደረጉ ቅድመ ግዴታ ነው። ጥቂት ከተሜዎች ሲካብቱ የገበሬው በድህነት መቀጠልና የጨቅላ ሕጻናት ያላግባብ በሥራ መበዝበዝ፤ በአጠቃላይ የገጠርና የከተማ ያልተጣጣመ ዕድገት ለብልጽግና ሊያበቃ የሚችል አይሆንም። እንዲያውም ለማሕበራዊ ቁጣ መባባስ ምክንያት ነው የሚሆነው።