የሒላሪ ክሊንተን ስብዕናና መርሕ | ዓለም | DW | 01.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የሒላሪ ክሊንተን ስብዕናና መርሕ

ሴትዮዋ እንደ ፕሬዝደት፤ የቀድሞዉ ፕሬዝደንት እንደ ቀዳማዊ ጌታ (የሚባል ነገር ካለ) ዳግም ዋይት ሐዉስ ለመግባት የከንግዲሁ ከባድ ፈተናቸዉ የሪፐብሊካን ተቀናቃኛቸዉ ዶናልድ ትራምፕን ማሸነፍ ነዉ።ትራምፕን ለማሸነፍ ደግሞ ጥሩ የፖለቲካ መርሕ፤ቅን አሳቢነት፤ ለሐገርና ለሕዝብ ጠቃሚ ሐሳብ ማመንጨት ብቻዉን በቂ አይደለም።በተለይ አሜሪካ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:01

የሒላሪ ክሊንተን ስብዕናና መርሕ

የዓለም አንደኛ ሐብታም፤ የጠንካራ ጦር፤ ምርጥ የሳይቲስቶቹ ሐገር የወደፊት መሪዋን ለመምረጥ ሁለት አማራጭ ቀርቦላታል።ሴት ወይስ ወንድ።ፖለቲከኛ፤ ዲፕሎማት፤ እናት ወይስ ቱጃር፤የቴሌቪዥን ዝግጅት አቅራቢ፤ ያሻዉን እንዳሻዉ ተናጋሪ አባት።ዶሆችን ደጋፊ፤ ስደተኞችን አስተናጋጅ የሐይማኖት እኩልነት ሰባኪ ወይስ ስደተኛ፤ ሙስሊሞችን አባራሪ።ክሊንተን ወይስ ትራምፕ የአሜሪካኖችን ዉሳኔ ለማወቅ እስከ ሕዳር መጠበቅ ግድ ነዉ።ፉክክሩ ግን ቀጥሏል።ቢሊየነሩ ፖለቲከኛ የወግ አጥባቂዉን የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩነት ባረጋገጡ በሳምቱ ባለፈዉ ሐሙስ ነባርዋ ፖለቲከኛ የለዘብተኛዉ የዲሞክራቲክ ፓርቲ እጩነታቸዉ በይፋ ፀድቋል።ባለፈዉ ሳምት የዶናልድ ትራምፕ መርሕና ሰብዕና ባጭሩ ቃኝተን ነበር።ዛሬ ተራዉ የሒላሪ ክሊንተን ነዉ።

በ1971 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር ነዉ) እንደሷ ሁሉ የል ዩኒቨርስቲ ሕግ ያጠና ከነበረዉ ወጣት ጋር ሲተዋወቁ፤ የግንኙነት-መፈላለጋቸዉ መሠረት እንደ ወጣት ፍቅር፤ እንደ ተማሪ ትምሕርት ነበር።የወጋቸዉ ርዕስ፤ የመፈላለጋቸዉ ፅናት፤ የመደጋገፋቸዉ ምክንያት ግን ፍቅር፤ ትምሕርት፤ ሥራ ዕድገት ብቻ አልነበረም።ፖለቲካም ጭምር እንጂ።«እና ቢል ከአርባ አምስት ዓመት በፊት ሕግ ቤተ-መፅሐፍት ዉስጥ የጀመርነዉ ዉይይት አሁንም እየጠነከረ ነዉ።»

ዛሬ እዉቀት፤ ሥልጣን፤ እድሜም አንቱታን ያጎናፀፋቸዉ ወይዘሮ ናቸዉ።ሒላሪ ዲያነ ሮድሐም ክሊንተን።ትምሕርቱ በዶክተርነት አሳርጎ፤ ፍቅሩ ትዳር፤ ትዳሩ እናት-አባትነትን አጎናፅፏቸዋል።የፖለቲካ ዉይይቱ ደግሞ ሰዉዬዉን ለትልቂቱ ሐገር ትልቅ ሥልጣን (ለፕሬዝደትነት) ባበቃ በ23ኛ ዓመቱ ዘንድሮ እሳቸዉን እንደ ቀዳማዊ እመቤት ከሚያቁት ቤተ-መንግሥት እንደመሪ ዳግም ለማስገባት ባለፈዉ ሳምንት ከወሳኙ

የመጨረሻዉ መጀመሪያ ፍልሚያ ላይ ደረሰ።ከዚሕ ለመድረስ የእስካሁኑ ፈተና በርግጥ ቀላል አይደለም።ዋይት ሐዉስ ለመግባት ከእንግዲሕ የሚቀረዉ ጉዞም ከባድ ነዉ።ግን ሒላሪ ክሊንተን በቀደም እንዳሉት ያ-የያኔ ፖለቲካ አስጠኚያቸዉ ፍቅር ለጋሻቸዉ አሁንም ከጎናቸዉ በመቆማቸዉ ደስተኛ ናቸዉ።ዊሊያም ጃፈርሰን (ቢል) ክሊንተን።

«ታዉቃለሕ፤ ያ ዉይይት እኛን በደስታ የተሞሉ ጥሩ ጊዜዎችን አሳልፏል።እኛን በፈተኑ አስቸጋሪ ጊዜዎችም አልፏል።በነዚሕ ጊዚያቶች ሁሉ ጥቂት ቃላት አግኝቻለሁ።ባለፈዉ ማክሰኞ ምሽት የእኔ ዋና አስረጂ (አስተማሪዬ) ሥራ ላይ ሆኖ ሳየዉ በጣም ደስ ብሎኛል።»

ሴትዮዋ እንደ ፕሬዝደት፤ የቀድሞዉ ፕሬዝደንት እንደ ቀዳማዊ ጌታ (የሚባል ነገር ካለ) ዳግም ዋይት ሐዉስ ለመግባት የከንግዲሁ ከባድ ፈተናቸዉ የሪፐብሊካን ተቀናቃኛቸዉ ዶናልድ ትራምፕን ማሸነፍ ነዉ።ትራምፕን ለማሸነፍ ደግሞ ጥሩ የፖለቲካ መርሕ፤ቅን አሳቢነት፤ ለሐገርና ለሕዝብ ጠቃሚ ሐሳብ ማመንጨት ብቻዉን በቂ አይደለም።በተለይ አሜሪካ።

የሚሉ-የሚያደርጉትን በጥሩ ቃላት፤ ድምፅ ሰጪዉ በሚገባዉ ቋንቋ መግለጥ፤አብዛኛዉ ድምፅ ሰጪ በዚሕ ወቅት የሚፈልገዉን አዉቆ የሚፈልገዉን ለማድረግ ቃል መግባት ተፎካካሪን ማሳጣት ግድ ነዉ።ለዚሕ ደግሞ የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ድጋፍ፤ የባለቤታቸዉ (የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን ሁለንተናዊ ትብብር አልተለያቸዉም።እሳቸዉም ዋዛ አይደሉም።

ዋና ነቃፊ፤ ተፎካካሪቸዉን ለማጣጣል፤ ከሁለቱ የቅርብ ደጋፊ፤ ተባባሪያ፤ አብነታቸዉ (ሞዴሎቻቸዉ) አልፈዉ የዲሞክራቶቹን ርዕሰ-ርዑሳንን አስተምሕሮ አነሱ።መፍራት ያለብን ፍራቻን ራሱን ብቻ ነዉ-እያሉ።«ዶናልድ ትራምፕ ባለፈዉ ሳምንት በተደረገዉ ጉባኤያቸዉ የተናገሩትን ሰምተናል።ከተቀረዉ ዓለም እና እርስ በራሳችንም ሊነጣጥሉን ይፈልጋሉ።ዛሬ ዓለምን ላጋጠመዉ አደጋ ያለገደብ እና በጭፍን እንዳናጎበድድ (ያስፈራሩናል።)መጪዉን ዘመን እንድንፈራ፤ እርስበርሳችን እንድንፈራራ ይፈልጋሉ።ታላቁ የዲሞክራቲክ ፕሬዝደንት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዘቬልት ከዘመናችን እጅግ የከፋ አደጋ በነበረበት ከዛሬ 80 ዓመት በፊት እንኳ የተናገሩት የትራምፕን ማስፈራሪያ በቀጥታ የሚቃረን ነበር።እንዲሕ ብለዉ። መፍራት ያለብን ፍርሐትን ራሱን ብቻ ነዉ።»

ሩዘቬልት ዩናይትድ ስቴትስን ከምጣኔ ሐብት ድቀት በማዳናቸዉ በአሜሪካኖች ዘንድ ይወደዳሉ።ሁለተኛዉን የዓለም ጦርነት ድል ያደረገዉን

የዓለም ሐይል በማስተባበራቸዉ ከዩናይትድ ስቴትስ አልፈዉ በአብዛኛዉ ዓለም ይደነቃሉ።የዩናይትድ ስቴትስን የዓለም ልዕለ ሐያል ሐገርነት በማረጋገጣቸዉ በአሜሪካና በአሜሪካ አፍቃሪዎች ዘንድ ይወደሳሉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲመሰረት በመጣራቸዉ በድፍን አለም ይደገፋሉ።

ሩዘቬልት የኬኔዲ፤ የቢል ክሊተን፤ የኦባማ የፖለቲካ አብነት እንደነበሩ እና እንደሆኑ ሁሉ የወይዘሮ ክሊንተንም ቢሆኑ በርግጥ አይደንቅም።የወይዘሮ ክሊንተን ቀዳሚ ምሳሌ ግን ከሩዘቬልት ይልቅ ኢሌኖር ሩዘቬልት ነበሩ።ከጥር 1993 እስከ ጥር 2001 እንደ ቀዳማዊት እመቤት ዋይት ሐዉስ በቆዩበት ወቅት ያከናወኑት ምግባርም ከኢሌኖይ ሩዘቬልት ጋር የሚያመሳላቸዉ ነዉ።

ብዙ የታሪካ ፀሐፊዎች እንደሚስማቡበትም ክሊንተን ከኢሌኖይ ሩዝቬልት ቀጥሎ ከፍተኛ ሥልጣን የያዙ ቀዳማዊ እመቤት ነበሩ።እንደ ፖለቲከኛ የተሳካላቸዉ ቀዳማዊ እመቤት፤ የኒዮርክ ሴናተር፤ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አሁን ደግሞ እጩ ፕሬዝደንት ደረጃ ለመድረስ ችለዋል። እንደ ሴት ወይዘሮም ጥሩ ሚስት፤ ሩሕሩሕ እናት አዛኝ አያት ናቸዉ።

ከዚሕ ለመድረስ ግን ከእዉቀት፤ጥረት፤ብልጠት በተጨማሪ ትዕግሥትም የባሕሪያቸዉ አካል መሆን ነበረበት።በርግጥም የሞኒካ ሉዊንስኪንና የባለቤታቸዉን ዉስልትና በሰሙ ማግስት ሰዉዬዉን በቃኸኝ በቃሁሕ ቢሏቸዉ ዛሬ የሆኑት መሆናቸዉ ወደፊት የሚመኙትን ማግኘታቸዉ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።

በዚሕ የምርጫ ዘመቻም እዉቀት፤ ብልሐት፤ ብልጠት ትዕግስቱ እስካሁን አልተለያቸዉም።ዋና ተቀናቃኛዉ የዶናልድ ትራምፕ አብይ የምርጫ መፈክር አሜሪካን መልሰን ታላቅ እናድርግ የሚል ነዉ።የሳቸዉ አፀፋ መቼ ትንሽ ሆነችና።«እጅግ በጣም ጠንካራ የጦር ሐይል አለን።አዳዲስ ነገሮችን በመፈጥር እጅግ የተካኑ ድርጅቶች አሉን።በጣም ሥር የሰደዱና ዘላቂ እሴቶች አሉን። ነፃነት፤እኩልነት፤ፍትሕ እና ዕድል።የእኒሕ ቃላት ሲነሳ ስማችን አብሮ በመነሳቱ እንኮራለን።»

ከሁለቱ የዩናይትድ ስቴትስ ትላልቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ ፓርቲ ሴት ፖለቲከኛን ለፕሬዝደትነት ሲያጭ ዴሞክራቲክ ፓርቲዉ፤ ሴት ፖለቲከኛ ለፕሬዝደትነት ስትታጭ ደግሞ ክሊተን የመጀመሪያዋ ናቸዉ።ግን ብልጥ ናቸዉ።እንደ ብዙዎቹ የሴት እኩልነት አቀንቃኞች ወንዶችን ወይም ለወንዶች የበላይነት የቆሙ ማሕበረ-ፖለቲካዊ ሥርአቶችን በማዉገዝ ጊዜ አላጠፉም።«የእናቴ ሴት ልጅ እና የሴት ልጄ እናት ነኝ» አሉ።ግን የቆሞኩት ለወንዶችም---

ጭምር ነዉ።

«እንደ እናቴ ሴት ልጅ እና እንደ ሴት ልጄ እናት እዚሕ (ከናንተ ፊት) ለመቆም በመብቃቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።ይቀን በመምጣቱ በጣም ደስተኛ ነኝ።ለአያቶች ለሕፃን ልጃገረዶችም፤ በዚሕ መሐል ላሉትም በሙሉ ደስተኛ ነኝ።ለወንድ ልጆችና ለትልቅ ወንዶችም ደስተኛ ነኝ።ምክንያቱም አሜሪካ ዉስጥ አንድ የሆነ እንቅፋት ሲወድቅ መንገዱ የሚለቀቀዉ ለሁሉም ነዉና።»

ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ እንዳሉት ቢመረጡ ስደተኛ አሜሪካን እንዳይረግጥ ሐገራቸዉን ከሜክሲኮ ጋር የሚያገናኘዉን ድንበር በግንብ ያሳጥራሉ።ለሙስሊሞች የመግቢያ ፍቃድ ይከለክላሉ።ክሊንተን ይሕን ይቃወማሉ።ለሐገራችን ከጠቀሙ ስደተኞች ይገባሉ ባይ ናቸዉ።

አሸባሪነትን ለማስወገድ አብነቱ፤ ክሊንተን እንደሚሉት ከሌሎች ሐገራት ጋር በመተባበር አሸባሪዎችን መዋጋት፤ የመረጃና የስለላ ልዉዉጦችን ማጠናከር፤ ዲፕሎማሲያዊን ጥረት ማሳደግ ነዉ።ከኢራን ጋር የተደረገዉ ስምምነት ለዶናልድ ትራምፕ አሜሪካንን ያንበረከከ ነዉ።ለክሊንተን ግን የዲፕሎማሲ ድል፤ የመልካም አመራር ዉጤት፤ የአሜሪካን ጠላት የመቀነስ ስልት ምሳሌ ነዉ።በሌላ በኩል በተለይ እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ የሚጠራዉን ቡድን ለማጥፋት እስካሁን የሚደረገዉ ድብደባ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

«ሐገራችንን አስተማማኝ ማድረግ እና ይሕን የሚያደርጉ ሰዎችን ማበረታት እና ማክበር ከፍተኛ ቅድሚያ የምሰጠዉ ጉዳይ ነዉ።የኢራንን የኑክሌር መርሐ-ግብር አንድም ጥይት ሳንተኩስ በመዝጋታችን ከፍተኛ ኩራት ይሰማኛል።ISISን ለማስወገድ የሚረዳ ስልት ነድፌያለሁ።መደደበቂያቸዉን ከአየር እንደበድባለን።ከምድር የሚዋጓቸዉን የአካባቢዉን ሐይላት እንረዳለን።»

ዶናልድ ትራምፕ

ሴቶችን አሳማ፤ ዳኛዉን የሜክሲኮ ዘር ስላለዉ ብቻ ትክክለኛ ፍርድ የማይሰጥ ሲሉ የሚቀልዱ መስሎን ነበር አሉ-ክሊንተን በስተንግግራቸዉ ማብቂያ ግን ሰዉዬዉ እዉነታቸዉን ነዉ።ምክንያቱም ሌላ ዶናልድ ትራምፕ አላየንም እና።እራሳቸዉስ ቢመረጡ ያሉትን ሁሉ ያደርጉት ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic