የሐጃጆች ሞት | ዓለም | DW | 25.09.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሐጃጆች ሞት

በዱዓ፤ሐዘን፤የመፅናናት ምኞቱ መሐል ብቅ፤ ጥልቅ፤ የሚለዉ ጥያቄ ግን እስካሁን ትክክለኛ መልስ አላገኘም።በዚሕ ዘመን፤ ባንዴ፤ ያን ያሕል ሕዝብ እንዴት አለቀ? የአይን ምሥክሩም አልገባቸዉም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:50
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:50 ደቂቃ

የሐጃጆች ሞት

ለሐጅ ጉብኝት የተጓዙ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ምዕመናን ትናንት ሚና-ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ ድንገት በመሞታቸዉ የሐገራት መሪዎችና የድርጅት ተጠሪዎች የሚያስተላልፉት የሐዘን መግለጫ፤ የሐይማኖት መሪዎች ፀሎት ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።በአደጋዉ 717 ሰዎች ሞተዋል፤ ከ800 በላይ ቆስለዋል።የሳዑዲ አረቢያ ገዢዎች የአደጋዉ ትክክለኛ መንሥኤ እንዲጣራ አዘዋል።ኢራን ግን ለአደጋዉ የሪያድ ነገሥታት ሐላፊነቱን እንዲወስዱ አሳስባለች።በሐጂ ጉብኝት ወቅት ተደጋጋሚ አደጋዎች ቢደርሱም በርካታ ሠዉ የሞተበት አደጋ ሲደርስ በሃያ-አምስት ዓመት ዉስጥ የትናንቱ የመጀመሪያዉ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ የዜና መልዕክቶችን አሰባስቧል።

ከመካዉ ዓል-ሐራም እስከ ሞስኮዉ ካቴድራል፤ ከምሥራቅ ለንደኑ እስከ ካይሮዉ አል-አዝሐር፤ ከካምፓላዉ ቃዛፊ፤ እስከ እየሩሳሌሙ ዓል-አቅሳ፤ ከዓለም መሳጂዶች የሚንቆረቆረዉ ዱዓ፤ምልጃ ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።ከዋይት ሐዉስ እስከ ክሬምሊን ያሉ አብያተ-መንግሥታትም የሐዘን መግለጫዉን እያጎረፉት ነዉ።የሐገራት፤የድርጅቶችና የሐይማኖት መሪዎችም እንዲሁ።

በዱዓ፤ሐዘን፤የመፅናናት ምኞቱ መሐል ብቅ፤ ጥልቅ፤ የሚለዉ ጥያቄ ግን እስካሁን ትክክለኛ መልስ አላገኘም።በዚሕ ዘመን፤ ባንዴ፤ ያን ያሕል ሕዝብ እንዴት አለቀ? የአይን ምሥክሩም አልገባቸዉም።

«ምንም ሊገባኝ አይችልም።እንዲሕ አይነት አደጋ የሚደርስበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይገባም።ባካባቢዉ ሰዉ የሚያድሩባቸዉ ድንኳኖች ናቸዉ ያሉት።(ጀመራት) ድልድይንም መጓዝ ያለባቸዉ ባንድ አቅጣጫ ነዉ።ባንድ አቅጣጫ ነዉ የሚዞሩት፤ ወደ ኋላ መመለስ፤ መቆምም አይችሉም።»

ሌሎች እንዲሕ ይተርካሉ ድንኳች የተተከሉባቸዉ ጎዳና ቁጥር 204 እና ጎዳና ቁጥር 223-ጀምራት ድልድይ አጠገብ ይገናኛሉ።እንደ ትናንቱ ባይሆን ኖሮ፤ ምዕመናን ድልድዩ ላይ ሆነዉ ሰይጣንን ለመደብደብ ተምሳሌት ጠጠር ይጥሉበታል።ትናንት ግን ከቁጥር 204 ጎዳና የተነሳዉ የሕዝብ ማዕበል እና ከቁጥር 223 የሚተመዉ ሌላ ማዕበል ሁለቱ ጎዳኖች እሚገጥሙበት ሥፍራ-ሲደርሱ ይላታማሉ።ከዚያ--ትርምስ፤ግጭት፤ጩኸት---

እና እልቂት።በሕዝብ መጨናነቅ፤መገፋፋት፤መረጋጋጥ፤ በቃጠሎ፤ ሌላ ቀርቶ በግንባታ ክሬን መዉደቅ -በዚያ ቅዱስ ሥፍራ፤ ሰዉ ሲሞት ሲቆስል ያሁኑ በርግጥ የመጀመሪያዉ አይደለም።ሰኔ 1982 በደረሰ አደጋ 1426 ሐጃጆች ካለቁ ወዲሕ በርካታ ሰዉ ሲሞት ግን የትናንቱ የመጀመሪያዉ ነዉ።717 ሰዉ----ለዚያራ በተከናነባት ጨርቅ እንደ ምሳሌዉ ተከፈነባት።8 መቶ ቆሠለ።

የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ግድም 364 ሰዉ በተመሳሳይ አደጋ ከሞተ ወዲሕ የሁለቱ ቅዱስ ሥፍራዎች የበላይ ጠባቂ የሚባሉት የሳዑዲ አረቢያ ነገስታት በተለይ መጨናነቁን ለማስተንፈስ፤ተጨማሪ ድልድዮች፤ መንገዶችና መሿለኪያዎች ማስራታቸዉን፤የኮሚፒዉተር መቆጣጠሪዎች ማስተከላቸዉን፤ በርካታ የአደጋ ተከላካይ ሠራተኞች ማስማራታቸዉን በየዓመቱ ይናገራሉ።ትናት የሆነዉ-ለምን ሆነ ታዲያ?

ንጉስ ሳልማን ይጣራል ነዉ መልሳቸዉ።«አሳዛኝ አደጋ ነው። የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን በተቻለ ፍጥነት አጣርተዉ ውጤቱን እንዲያሳውቁን አዘናል። የምዕመናን ደህነነት ለማስጠበቅ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን ።»

የንጉሱ የጤና ሚንስትር ግን «የጉዞዉን ደንብና ሥርዓት ያላከበሩ ምዕመናን የፈጠሩት ትርምስ» የሚል መልስ ሰጥተዋል። በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ የሚያስተናግድ መንግሥት ጥንቃቄ፤ ምክር፤ ዝግጅቱ እልቂት አለማስቀረቱ ብዙዎችን ማሳዘኑ አልበቃ ያለ ይመስል፤ ባለሥልጣናቱ በምዕመኑ ማሳበባቸዉ ማስተዛዘቡ አልቀረም።የኢራን መሪዎች ከመታዘብም አልፈዉ የሪያድ ነገስታት የመካና መዲና «የበላይ ጠባቂ ነን» እንደሚሉት ሁሉ ለአደጋዉም በበላይ ሐላፊነት መጠየቅ አለባቸዉ ባዮች ናቸዉ።

ታዛቢዉ ደግሞ፤ «በቂ ፀጥታ አስከባሪ ወይም ሥርዓት አሲያዥ ቢኖር ኖሮ፤ ሕይወት አድን ሠራተኞች ፈጥነዉ ቢደርሱ፤ ከሁሉም በላይ ተጨማሪ ማስፋፋት ቢደረግ ኖሮ-ያ ሁሉ ሕዝብ ባላለቀ ነበር» ይላሉ።

«ሚና ተጨማሪ የማስፋፊያ ግንባታ ያስፈልገዋል።መንገዶቹ መስፋፋት፤ ድንኳኖቹም ተራርቀዉ የሚተከሉበት ሥልት ሊኖር ይገባ ነበር።(ከእንግዲሕም) የሆነ የምሕንድስና ሥራ-መሠራት አለበት።»

የሟቾቹ ዜግነትና ብዛት ቀስበቀስ ይፋ እየሆነ ነዉ።እስካሁን የመጀመሪያዉን ሥፍራ የያዙት ኢራኖች ናቸዉ።131።ሞሮኮ 87።ሕንድ 14።ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ እንዳለዉ ኢትዮጵያዉይንም ሞተዋል።ቁጥራቸዉ ግን ገና በይፋ አልተነገረም።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

 

 

Audios and videos on the topic