የሐኖቨር ግዙፍ የኢንዱስትሪ አውደ-ርዕይ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 27.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የሐኖቨር ግዙፍ የኢንዱስትሪ አውደ-ርዕይ

ግዙፉ የሐኖቨር የኢንዱስትሪ አውደ-ርእይ በከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ በሰሜናዊ ጀርመን በሐኖቨር ከተማ ውስጥ እሁድ በይፋ ተከፍቶ ሰኞ ለሕዝብ መታየት የጀመረ ሲሆን፤ ከነገ በስትያ ዐርብ ይጠናቀቃል። አውደ ርእዩ በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ሲጎበኝ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:44
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
08:44 ደቂቃ

ግዙፍ የኢንዱስትሪ አውደ-ርእይ

በመክፈቻው ሥነስርዓት ላይም የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ተገኝተዋል። በዚህ በተንጣለሉ 27 ሰፋፊ አዳራሾች ውስጥ በተሰናዳነው ዐውደ-ርእይ የዓለማችን ድንቅ የሥነ-ቴክኒክ የፈጠራ ውጤቶች ለእይታ ቀርበዋል። ግዙፍ ኩባንያዎች በዐውደ-ርእዩ ታድመው ከስምምነት ላይም ደርሰዋል። የሥራ ማቆም አድማ የመጓጓዣ አገልግሎት ላይ ችግር ቢፈጥርም በርካታ ሰዎች ግዙፉን አውደ-ርእይ ጎብኝተዋል።

የሐኖቨር የኢንዱስትሪ አውደ-ርእይ እንደ ዘንድሮ ከፍተኛ ትኩረት ስቦ አያውቅም። 27 የተንጣለሉ አዳራሾችን ባካተተው ግዙፉ አውደ-ርእይ ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡ 450 ኩባንያዎችን ጨምሮ ከመላው ዓለም 5200 ምርት አስጎብኚዎች ተሳትፈውበታል። አውደ-ርእዩ እሁድ ሚያዝያ 16 ቀን፣ 2008 ዓ.ም. በይፋ ሲከፈትም ከጀርመን መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጋር የተገኙት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ባሰሙት ንግግር ሀገራቸው በአውደ-ርእዩ ያቀረበችውን ሥራዎች አስተዋውቀው ነበር።

«እዚህ በዩናይትድ ስቴትስ የማሳያ አዳራሽ ውስጥ አሜሪካ ለፈጠራ ውጤቶች የምታበረክተውን አስተዋጽኦ በኩራት እናሳያለን። እዚህ እንደምታዩት አኗኗራችንን፣ የሥራ እና የትምህርት ሁኔታችንን የሚቀይሩ ፈር ቀዳጅ ኩባንያዎች ቀርበዋል። ስለዚህ ለእኔ ይኼ፦ ሁላችሁም ቀረብ ቀረብ በሉና በአሜሪካ የተሠራ ግዙ ለማለት ተጨማሪ ዕድል ነው።»

በአውደ-ርእዩ የሰው ልጅ የወደፊት የአኗኗር ዘዬን ሊቀይሩ የሚችሉ በርካታ የምርምር ውጤቶች ታይተዋል። ለአብነት ያኽል ቺምፕ የተሰኘውን ሮቦት መጥቀስ ይቻላል። ቺምፕ የተፈጥሮ አደጋ በሚከሰትበት ወቅት ሰዎች በማይደርሱበት አደገኛ ቦታ ገብቶ ርዳታ መስጠት የሚችል ሮቦት ነው። ወደፊት ብዙም የሰዎች ርዳታ ሳያስፈልገው በራሱ ጊዜ ተግባሩን እንዲፈጽም የተሠራ ማገናዘብ የሚችል ምጡቅ (intelligence) ሮቦት ነው ተብሎለታል።

ሮቦቱ በዝግታ ይንቀሳቀሳል፤ ይተጣጠፋል፣ ይዘረጋጋል፣ በእጆቹ ማናቸውንም ነገር ጨብጦ ያነሳል፣ በአጠቃላይ በሰው ሠራሽ ዕውቀት የበለጸገ ሮቦት መኾኑን በአውደ ርእዩ ቀርቦ ለጎብኚዎች አስመስክሯል። በሰው ሠራሽ ዕውቀት የበለጸጉ ሮቦቶችን ማምረት ወደፊት አብዮት መሆኑ አይቀርም ተብሏል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፒትስበርግ ውስጥ የሚገኘው ካርኔጊ ሜሎን ዩኒቨርሲቲ በዚህ ዘርፍ ከፍተኛ እመርታ ማስመስከሩ ይነገርለታል። ሮቦቱን በአውደ-ርእዩ ያቀረበውም ይኸው የምርምር ተቋም ነው።

በስነ-ቴክኒኩ ዘርፍ የተለያዩ ምርቶችም ለእይታ ቀርበዋል። የፋብሪካ እና የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪ ውጤቶች በአንድ በኩል፤ የኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ ግብአቶች በሌላ በኩል ተደርድረው ታይተዋል። የኃይል ምንጭ፤ የኢንዱስትሪ አቅርቦት እንዲሁም ምርምር እና ስነ-ቴክኒክም በአውደ-ርእዩ በብዛት ለእይታ በቅተዋል። ይኽ ግዙፍ አውደ-ርእይ በይፋ በተከፈተበት ወቅት የጀርመን መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል አውደ ርእዩ ከምንጊዜውም ለየት ያለ መሆኑን ገልጠዋል።

«እዚህ ሁላችንም በወዳጅነት መንፈሥ ነው ሠላምታችንን የምናቀርብላችሁ። እንደ ጥብቅ ወዳጆች፤ የአሜሪካ ኩባንያዎች እርስ በእርስ መማማር የሚቻልባቸው ጠንካራ ኩባንያዎች መሆናቸውን እንደሚያውቁ ወዳጆች ነው አቀባበላችን። የጋራ ፈጠራዎችን ለማበልፀግ እና አዲስ ሀገር ለመገንባት ተቀራርበን መሥራቱን የበለጠ ማነቃቃት እንሻለን። የሐኖቨር አውደ-ርእይ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛው እመርታ ማሳያ ነው። የዘንድሮው ግን ከምን ጊዜውም ለየት የሚያደርገው የዓለም ምርጦች እንደተሰባሰቡ መጎብኘት መቻላችሁ ነው።»

በእርግጥም በዘንድሮው አውደ-ርእይ 5200 ምርት አቅራቢ ተሳታፊዎች ታድመውበታል። እርስ በእርስ በተገናኙ የተለያዩ የማምረቻ መሣሪያዎች ተሠርተው የሚቀርቡ ምርቶች በዓለማችን መስፋፋታቸውን ለማሳየትም ወደ 100 ግድም አብነቶች ታይተዋል። የሐኖቨር የኢንዱስትሪ አውደ-ርእይ የዘንድሮ ተባባሪ አቅራቢ የሆነችው ዩናይትድ ስቴትስ እና ጀርመን ጎልተው የሚታዩ የሥነ-ቴክኒክ ውጤቶች አቅርበዋል። ሁለቱ ሃገራት አንዱ ከአንዱ ለመብለጥ ከመፎካከር ይልቅ ግን በጋራ መሥራቱ ላይ ማተኮራቸውን የአውደ-ርእዩ ኃላፊ ዮኸን ኮይክለር ጠቅሰዋል።

«በመጀመሪያ ደረጃ አውደ-ርእዩ ሸሪኮች የተገናኙበት ነው። ዩናይትድ ቴትስ ለጀርመን የማሽን ኢንዱስትሪ ዋነኛ የገበያ መዳረሻ ናት። በመቀጠል ሥነ-ቴክኒኩ ላይ ትንሽ ፉክክር ታይቷል። ጥያቄው መፃኢ ፋብሪካዎች የት ነው የሚሆኑት የሚለው ነው። ጀርመን ውስጥ ከመሐንዲሶች ብቃት፣ ከኢንዱስትሪ ሶፍትዌሮች ማበልጸግ አንጻር የተስፋፋው ኢንዱስትሪ ነው። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ደግሞ አንዳችም የኢንዱስትሪ ማምረቻ መሣሪያዎችን ሳይጠቀሙ ሆኖም ኢንተርኔትን የንግድ ተምሳሌት ያደረጉ እንደ ጉግል፣ ፌስቡክ እና የመሳሰሉት የንግድ ስልቶች ናቸው ጎላ ብለው የሚታዩት። በእርግጥ የወደፊቱን ኢንዱስትሪ ሞተር ለመቆጣጠር ሩጫው አለ። እናስ አሜሪካኖች ናቸው ጀርመኖች ወደፊት ያን የሚቆጣጠሩት አለያስ መሆኑ አይቀርም ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የጋራ እድገት? ጥያቄው ያ ነው።»

በአውደ-ርእዩ የሥነ-ቴክኒክ ውጤቶችን ለእይታ ከማቅረብ ባሻገርም ግዙፍ ኩባንያዎች በጋራ ለመሥራት ተዋውለዋል። ለአብነት ያኽል፦ የጀርመኑ ግዙፍ የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች ማምረቻ ሲመንስ ኩባንያ እና የጃፓኑ ፓናሶኒክ አቻ ኩባንያ መካከል የተደረገው ውል ተጠቃሽ ነው። ሁለቱ ኩባንያዎች በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል። መቀመጫውን በርሊን እና ሙይንሽን ከተሞች ላይ ያደረገው የጀርመኑ ሲመንስ ኩባንያ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2015 ዓመት €75.6 ቢሊዮን ዩሮ አንቀሳቅሶ €7.4 ቢሊዮን ዩሮ የተጣራ ትርፍ ማግኘት ችሏል ድርጅቱ። 165 ዓመታትን ያስቆጠረው እና በዓለም ዙሪያ 348,000 ሠራተኞች ያሉት ሲመንስ ኩባንያ ከ200 በላይ ሃገራት ውስጥ ይንቀሳቀሳል።

ስምምነቱን ከሲመንስ ጋር የፈረመው ፓናሶኒክ ደግሞ በ98 ዓመት ታሪኩ በዓለም ዙሪያ 94 ተባባሪ ኩባንያዎች ሲኖሩት የ468 ኩባንያዎች ባለአክሲዮን ነው። ባለፈው የጎርጎሪዮስ ዓመት 7.715 ትሪሊዮን የጃፓን የን የተጣራ ትርፍ ማግኘት የቻለ ድርጅት ነው። ከጀርመኑ ኩባንያ ጋር በመሆን ወደፊት በሥነ-ቴክኒኩ ዘርፍ አዳዲስ ፈጠራዎችን ለማስመዝገብ ተስማምቷል።

አምና ከ220,000 ሰዎች በላይ የተጎበኘው አውደ-ርእይ ዘንድሮ በሚከናወንበት ወቅት ትናንት (ማክሰኞ)የሥራ ማቆም አድማ በተለይ በመጓጓዣ ዘርፉ በመታየቱ በርካታ ጎብኚዎች የመጓጓዣ ችግር አጋጥሟቸዋል። በጀርመን የሚገኙ የአውቶቡስ አሽከርካሪዎች፣ የአውሮፕላን አብራሪዎች እና የመዋዕለ-ሕጻናት ተንከባካቢዎች ለተሻለ የደሞዝ ክፍያ በሚል የሥራ ማቆም አድማ አድርገው ነበር። የአውደ-ርእዩ አስተናባሪዎች ማክሰኞ ከማለዳው አንድ ሰአት አንስቶ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰአት ድረስ ለመጓጓዣ አገልግሎት አውቶቡሶችን በማቅረብ ጎብኚዎች እንዳይስተጓጎሉ ለማድረግ ሞክረዋል።

ዛሬ ደግሞ የሉፍታንዛ አብራሪዎች የሥራ ማቆም አድማውን በመቀላቀላቸው ይኽ የመጓጓዣ ችግር አልተቃለለም። ከዛ ውጪ ግን አውደ-ርእዩ የሥነ-ቴክኒክ ውጤቶችን በማስተዋወቅ ስኬታማ ነበር ተብሎለታል። የሚቀጥለው ዓመት የሐኖቨር ግዙፍ የኢንዱስትሪ አውደ-ርእይ ተባባሪ ሀገር ፖላንድ እንደምትሆንም ተገልጧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic