1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Hirut Melesseረቡዕ፣ ሐምሌ 3 2016

የሐምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. አርዕስተ ዜና ሱዳን የሚገኙ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ስደተኞች የከፋ አደጋ ላይ ናቸው ሲል ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂዩመን ራይትስ ዋች አሳሰበ። ከመካከላቸው ገዳሪፍ ያሉ ከ40 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ስደተኞች ይገኙበታል ። ከግንቦት አንስቶ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ በደቡብ ሱዳን መንግስትና በተቃዋሚዎች ተወካዮች መካከል በኬንያ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ንግግር ሊጠናቀቅ ሲል ተሰናከለ። የኔቶ አባል ሀገራት መሪዎች ጉባኤ ላይ ዩናይትድ ስቴትስና ሌሎች የኔቶ አባል ሀገራት ለዩክሬን የአየር መከላከያ ስርዓት ለመለገስ ቃል ገቡ።

https://p.dw.com/p/4i7bz

ኒውዮርክ    የኢትዮጵያና የኤርትራ ስደተኞች በሱዳን አደጋ ላይ ናቸው

ጦርነት በበረታባት በሱዳን የሚገኙ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ስደተኞች የከፋ አደጋ ላይ ናቸው ሲል ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂዩመን ራይትስ ዋች አሳሰበ።የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መግፋት ከቀጠለም ኢትዮጵያን በሚያዋስነው በገዳሪፍ  ግዛት የሚገኙ ከ40 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ስደተኞች ለአደጋ እንደሚጋለጡ ድርጅቱ አስጠንቅቋል።  
በድርጅቱ ዘገባ መሠረት በኤርትራ ይደርስብናል ከሚሉት ጭቆና ሸሽተው ከለላ ለማግኘት ወደ ሱዳን የሚሰደዱ ኤርትራውያንም በተለይ ወደ ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍል መግባታቸውን ቀጥለዋል። አብዛኛዎቹ ስደተኞች ግን ጦርነት ከመነሳቱ በፊትም ሱዳን የነበሩ ናቸው። በጀርመን ዜና አገልግሎት ዘገባ መሠረት ሁኔታው የተባባሰው ፈጥኖ ደራሹ ኃይል በቅርብ ሳምንታት በሱዳን ጦር ቁጥጥር ስር ወደነበረው ሴናር ወደ ተባለው ግዛት እየገፋ ከመጣ በኋላ ነው።
የእጅ አዙር መሪ የሚባሉት የሱዳን ጦር አዛዥ አብደል ፈታህ አልቡርሀን እና የቀድሞ ምክትላቸው የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ ሞሐመድ ሀምዳን ፋግሎ ካለፈው ዓመት ሚያዚያ አንስቶ ውጊያ ላይ ናቸው። የተመድ እንደተናገረው ጦርነቱ ቁጥሩ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ እንዲሰደድ አድርጓል። በሰሜን ዳርፉር ግዛት ያለው ሁኔታ ደግሞ  አስፈሪ ነው። በተለይም የመጨረሻዋ ትልቅ ከተማ አል ፋሺር በዳግሎ ኃይሎች እጅግ ውስጥ መውደቅ የመቻሏ ስጋት አለ። ፈጥኖ ደራሹ ኃይል በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በወሲብ ጥቃት እና ሰላማዊ ሰዎችን በዘፈቀደ በመግደል ይወነጀላል። 

ጁባ     የደቡብ ሱዳን የሰላም ንግግር እየተንገዳገደ ነው

ሊጠናቀቅ የነበረው የደቡብ ሱዳን የሰላም ንግግር ተሰናከለ። ስምምነቱ ሊያበቃ ሲቃረብ በንግግሩ ተካፋይ የሆኑት ተቃዋሚ ቡድኖች ስምምነቱን ለመፈረም ሰዎች የለእስር ማዘዣ እንዲያዙ የሚፈቅደው በቅርቡ የፀደቀው አዲስ ሕግ እንዲሰረዝ ጠይቀዋል። ከግንቦት አንስቶ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ በደቡብ ሱዳን መንግስት ተወካዮችና ለአምስት ዓመታት የዘለቀውን የሱዳን የርስ-በርስ ጦርነት ባስቆመው የጎርጎሮሳዊው 2018 ዓመተ ምኅረቱ ስምምነት ያልተካተቱት ተቃዋሚዎች  መካከል ሲካሄድ የነበረውን የዚህ የሰላም ንግግር አስተናጋጅ ኬንያ ናት።የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚዎች ንቅናቄ ኅብረትን በንግግሩ የወከሉት ፔጋን አሙን ኦክዬሽ  ፈላጭ ቆራጩ ብሔራዊ የጸጥታ ሕግ በፕሬዝዳንቱ ከተፈረመ ስምምነቱን መፈረሙ ትርጉም አይኖረውም ሲሉ ትናንት ምሽት ለአሶስየትድ ፕሬስ ተናግረዋል። ባለፈው ሳምንት የደቡብ ሱዳን ፓርላማ ያጸደቀው ረቂቅ ሕግ፣ ሕግ ሆኖ ከመውጣቱ በፊት የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር በ30 ቀናት ውስጥ ማጽደቅ ይኖርባቸዋል። አሙም እንዳሉት ሕጉ የደቡብ ሱዳን ዜጎችን መሠረታዊ መብቶችና ነጻነቶችን ይጥሳል። በዚህ ሕግም ሰላም ወይም ዴሞክራሲ ሊኖር አይችልም። በንግግሩ ተሳታፊ የሆነ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ለአዳዲስ የዩኒቨርስቲ ምሩቃንን ለመደገፍ የሚሰራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ተወካይም የፀጥታ ሕጉ በድርድሩ ላይ አሉታዊ መንፈስ ፈጥሯል ሲል ተናግሯል። ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂዩመን ራይትስ ዋችም ኪር አወዛጋቢውን ሕግ እንዳይቀበሉ ጥሪ አቅርቧል።

ዋሽንግተን ዲሲ  የዋሽንግተኑ የኔቶ አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ቀጥሏል

በዩክሬኑ ጦርነት ላይ ያተኮረው የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት የኔቶ አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ እየተካሄደ ነው። በትናንቱ የመጀመሪያ ቀን ስብሰባ የአስተናጋጇ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሀገራቸው ድርጅቱን የመርዳት  የተቀደሰ ግዴታ እንዳለባት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ለዩክሬንም የአየር መከላከያ ስርዓት ለመስጠት ቃል ገብተዋል። የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በበኩላቸው እየጨመረ በሄደው የሩስያ የሚሳይልና የድሮን ጥቃት ምክንያት በተደጋጋሚ ሲጠይቁት የነበረውን የአየር መከላከያ ስርዓት ለሀገራቸው ለመስጠት ቃል ስተገባላቸው አመስግነዋል።የኔቶ አባል ሀገራት መሪዎች በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ በሚያወጡት መግለጫ ዩክሬን የኔቶ አባልነትን ጨምሮ በአውሮጳና አትላንቲክ ውኅደት የጀመረችውን «የማይቀለበስ »ያሉትን «መንገድ»ማገዛቸውን እንደሚቀጥሉ ቃል መግባታቸውን አንድ ምንጭ ለሮይተርስ ገልጸዋል። በጋራ መግለጫው መሠረት የኔቶ አባል ሀገራት ከተስማሙ እና ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ ዩክሬን የኔቶ አባል እንድትሆን ግብዣ ይቀርብላታል። ተሰናባቹ የኔቶ ዋና ሃላፊ የንስ ሽቶልትንበርግ እንደተናገሩት ዩክሬን የኔቶ አባል ለመሆን መንገድ ላይ ናት።ይሁንና ሀገሪቱ መቼ የኔቶ አባል እንደምትሆን  አሁን ለመናገር ያዳግታል።
"አዲስ አጋር ለመጋበዝ መግባባት ያስፈልጋል። እናም ሁሉም አጋሮች ዩክሬን የኔቶ አባል እንድትሆን ይስማማሉ።ሆኖም ይህ መቼ ሊሆን እንደሚችል ለመናገር አሁን ጊዜው ገና ነው። ማለት የምችለው ከዩክሬን ጋር እየተንቀሳቀስን ወደ ኔቶ አባልነት እየተጠጋን እና እየተጠጋን ነው። »
በሚቀጥሉት ወራት ዩክሬን በርካታ ስልታዊ የአየር መከላከያ ስርዓቶችን ታገኛለች። ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን ለመስጠት ቃል ከገባችው የአየር መከላከያ  ውስጥ ዩክሬን የጠየቀችው ቢያንስ አራት የፓትርየት ስርዓቶችን ያካትታል። ዩናይትድ ስቴትስ ጀርመንና ሮማንያ ተጨማሪ የፓትርየት ባትሪዎችን እንደሚልኩ በጋራ ስምምነቱ ላይ ተገልጿል። ሌሎች አጋሮች ደግሞ የአየር መከላከያ ስርዓት ለዩክሬን ይልካሉ ።የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ መሪዎቹ ለዩክሬን ተጨማሪ F-16 የጦር ጀቶችን ለመስጠትም በቅርቡ ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
«ዛሬ ዋሽንግተን ውስጥ ስራችንን ቀጥለናል። በተለይ F-16 ጀቶችን በሚመለከት በቅርቡ ይወሰናል።ለዩክሬን የሚሰጡ የጦር አውሮፕላኖችን ቁጥር እንጨምራለን። ትናንት 5 ተጨማሪ ፓትርየቶችን እና 10 ሌሎች የአየር መከላከያ ስርዓቶች አግኝተናል። ዛሬ ደግሞ በጀቶቹ ላይ የሚሰጥ ውሳኔ ይኖራል።» ።
 የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ዛሬ ቀደም ሲል ዩናይትድ ስቴትስ ሰራሽ F-16 ጀቶች ከዴንማርክና ከኔዘርላንድስ ወደ ዩክሬን እየተላለፉ መሆኑን ገልጸው ጀቶቹ በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ በጋ በዩክሬን ሰማይ ላይ ይበራሉ ብለው ነበር። ኔቶ ከተመሰረተ ዘንድሮ 75 ዓመት ደፍኗል።

ቦን    የአውሮጳ እግር ኳስ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ውድድር


በ17ኛው የአውሮጳ  ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ሁለተኛ ጨዋታ በእንግሊዝ  እና በኔዘርላንድ ቡድኖች መካከል  ዛሬ ምሽት 4:00 ሰዓት በዶርትሙንድ ሲግናል ኢንዱና ፓርክ ስታድዮም ይደረጋል ። እንደፈረንሳይ ሁሉ ግማሽ ፍጻሜ የደረሰው የሳውዝ ጌቱ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ለዋንጫው ብዙም ግምት ያልተሰጣትን ኔዘርላንድን ይገጥማል። 
በየጫወታው መሻሻልን እያሳየች ከግማሽ ፍጻሜው ከደረሰችው ኔዘርላንድ ጋር የሚደረገው ጨዋታ በበርካቶች ዘንድ እየተጠበቀ ነው። ሁለቱ ቡድኖች በሩብ ፍጻሜው እንግሊዝ ስዊዘርላንድን በመለያ ምት 5 ለ 3 አሸንፋ ነበር ግማሽ ፍጻሜውን የተቀላቀለችው ። 
ኔዘርላንድ በሩብ ፍጻሜው እጅግ በጣም ጥሩ አቋም ላይ የነበረችውን ቱርክ በጫወታ 2 ለ 1 አሸንፋ ነው ግማሽ ፍጻሜውን የደረሰችው ።  እንግሊዝ እና ኔዘርላንድስ በአውሮጳ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገናኙበት የጎርጎርሳውያኑ 1935 ወዲህ በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ የውድድር መድረኮች 22 ጊዜ ተገናኝተዋል። በውድድሮቹ ኔዘርላንድ 7 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ስትይዝ እንግሊዝ ስድስት ግዜ አሸንፋለች። 9 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።   
የምሽቱ ጨዋታ አሸናፊ የፊታችን ረቡዕ በርሊን ኦሎምፒያ ሽታዲዮን በወጣት እና አንጋፋ ተጫዋቾች የበረታውን ስፔንን ለዋንጫ ይገጥማል። ለፍጻሜ ለማለፍ ትናንት ማክሰኞ ምሽት 4:00 ሰዓት በተደረገው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ስፔን ፈረንሳይን 2 ለ 1 አሸንፋ ለፍጻሜ ማለፏ ይታወሳል።

ዱስልዶርፍ       የጀርመን የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች 20 ሺህ ዩሮ ቃል ተገባላቸው

 የጀርመን የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች በፓሪሱ የኦሎምፒክ ውድድር የወርቅ ሜዳልያ ካሸነፉ ለእያንዳዳቸው 20 ሺህ ዩሮ ወይም 21 ,400 ዶላር እንደሚሰጣቸው የጀርመን የእግር ኳስ ፌደሬሽን በጀርመንኛው ምህጻር DFB አረጋገጠ። ለሴቶች የእግር ኳስ ቡድን ይሰጣል የተባለው የዚህ ገንዘብ መጠን  በቶክዮው የኦሎምፒክ ውድድር የወንዶቹ የእግር ኳስ ቡድን ቢያሸንፍ ሊሰጠው ቃል ከተገባለት ገንዘብ ጋር ተመሳሳይ ነው። ለዛሬ ሶስት ዓመቱ የቶክዮው ኦሎምፒክ የጀርመን የሴቶች እግር ኳስ ቡድን አላለፈም ነበር። የጀርመን ቡድን ደግሞ ለዘንድሮው የፓሪስ ኦሎምፒክ አላለፈም።የሴቶቹ ቡድን ከ15 ቀን በኋላ ከአውስትራሊያ ከዚያም ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር   ከ18 ቀናት በኋላ እንዲሁም ከ21 ቀናት በኋላ ከዛምቢያ ጋር ይጋጠማል። የሴቶቹ ቡድን በ2025 ስዊዘርላንድ ለሚካሄደው የአውሮጳ እግር ኳስ ሻምፕዮና ማለፉንም አረጋግጧል።  
 

ኂሩት መለሰ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።