የሎሜ ውል ሠላሣኛ ዓመት | ኤኮኖሚ | DW | 28.02.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የሎሜ ውል ሠላሣኛ ዓመት

ቀድሞ የአውሮጳ የኤኮኖሚ ማሕበረ ሕዝብ በመባል ይታወቅ በነበረው እና በምሕፃሩ ኤሲፒ በመባል በሚጠሩት የአፍሪቃ፡ የካሪቢክ እንዲሁም የፓሲፊክ አካባቢ ሀገሮች መካከል የመጀመሪያው የሎሜ ውል ከተፈረመ ዛሬ ሠላሣ ዓመት ሆኖታል።

የዚሁ ውል ዓላማ ከሰባ የሚበልጡትን አዳጊ ሀገሮች የኤክስፖርት ይዞታን እና ከነዚሁ ሀገሮች ጋር የሚደረገውን ኢንዱስሪያዊ ትብብር በማጠናከር እንዲሁም፡ አንድ የልማት ርዳታ የሚቀርብበበት ድርጅት በማቋቋም በነዚህ ሀገሮች ውስጥ የሚታየውን ድህነት መቀነስ የተሰኘው ነበር።

በተለይ ፈረንሣይ፡ ቤልጅየምና ብሪታንያ በሰባኛዎቹ ዓመታት የአውሮጳ ኤኮኖሚ ማሕበረ ሕዝብ ከቀድሞው ቅኝ ግዛቶቻቸው ጋር አንድ ልዩ የኤኮኖሚ ግንኙነት እንዲያዘጋጅ በጠየቁት መሠረት ነበር የሎሜ ውል የተሰኘው ውል ተፈረመ። በውሉ መሠረት ስድስት መቶ አርባ ሚልዮን የኤሲፒ ሀገሮች ሕዝብ የገንዘብ ርዳታና በአውሮጳ ኤኮኖሚ ማሕበረ ሕዝብ አባል ሀገሮች ገበያም ውስጥ የተሻለ የንግድ ዕድል ተከፍቶለታል። ይሁንና፡ የአፍሪቃ፡ የካሪቢክ እና የፓሲፊክ አካባቢ ሀገሮች በሎሜ ውል በቀረበላቸው ቋሚ ርዳታ የኢንዱስትሪ ዘርፋቸውን ሳያሻሻሉ ነበር የቀሩት። የኤ ሲ ፒ ሀገሮች መንግሥታት ገንዘቡን አላግባብ ከማዋላቸው ሌላ፡ በከፊልም ለርስበርሱ ጦርነት እንደተጠቀሙበትና አንዳንዴም ሀንዘቡ የት እንደደረሰ ሳይታወቅ እንደጠፋ ነው የተገለፀው። ይህንኑ ሁኔታ ለመቀየርና የድሆቹን ሀገሮች የኤክስፖርት ይዞታ ለማሻሻል በማሰብ እአአ በ 2000 ዓም ከሎሜ ቀጥሎ የኮቶኑ ውል ተፈረመ። የጀርመናውያኑ የረሀብተኞች መርጃ ድርጅት የአውሮጳ ተጠሪ ወይዘሮ ብሪጊተ ዴዴሪኽ ባን የኮቶኑ ውል ከሎሜ ውል የተለየበትን ሁኔታ እንዳስረዱት፡ የኮቶኑ ውል ሲቭሉን ሕዝብ ያሳተፈ፡ ማለትም፡ የሴቶች ቡድኖችና መንግሥታዊ ያልእሆኑ ድርጅቶች ከአውሮጳ ኅብረት ጋር የሚኖረውን ትብብር የመሠረታዊ ልማቱንና ድጋፉን በተመለከተ በሚወጣው የዕቅድ አወቃቀር ላይ ሙሉ የመሳተፍ መብት ሰጥቶዋቸዋል።
የሎሜ ውል ከተፈረመ ዛሬ ሠላሣ ዓመት የሆነላበት ድርጊት የተመድ ያስቀመጠው የምዕተ ዓመቱ ግብ ማለትም በዓለም የሚታየውን ድህነት በግማሽ የመቀነሱ ለመቀነስ እና ለዚሁ ዓላማው መሳካትም የአውሮጳ ኅብረት አባል መንግሥታት ከጠቅላላ ብሔራዊ ገቢቸው 0,7 ከመቶ ለልማቱ ርዳታ እንዲሰጡ የጠየቀበት ጉዳይ ተግባራዊነት እንዲነሣ አድርጎዋል። ይሁን እንጂ፡ ለምሳሌ ጀርመን ከጠቅላላው ብሔራዊ ገቢዋ በያመቱ እስካሁን ስድስት ሚልያርድ ዩሮ ብቻ ነው ለልማቱ ርዳታ የሰጠችው። በፈረንሣይም ቢሆን ይኸው አሀዝ የተሻለ አይደለም፡ ከጠቅላላ ብሔራዊ ገቢዋ መካከል ለልማቱ ርዳታ የሰጠችው መጠን 0,3 ከመቶ ብቻ ነበርና። እርግጥ፡ በማዕከላይ አፍሪቃ ሀገሮች በኮንጎ፡ ርዋንዳና ቡሩንዲ ጋር ላይ ትኩረትዋን ያሳረፈችው ቤልጅየም በዚያ ለሚካሄዱ የሰላም ማስከበሪያ ሂደቶች በቀጣይነት በመርዳት ከዩኤስ አሜሪካ ቀጥላ ትልቅዋ ርዳታ አቅራቢ ሀገር ሆናለች።
የብሪታንያ ገንዘብ ሚንስትር ጎርደን ብራውንም በድሆችና በሀብታሞቹ ሀገሮች መካከል ልዩነቱን ለማጥበ፡ በአዳጊዎቹ ሀገሮች በተለይ፡በአሪቃ ድህነትን ለመታገሉ ጥረት ከሎሜና ከኮቶኑ ባሻገር ሌላ አዲስ ስምምነት እንዲወጣ፡ የበለፀጉት ምዕራባውያን መንግሥታትም የድሆቹን አዳጊ ሀገሮች የውጭ ዕዳም እንዲሰረዙ ፡ እንዲሁም፡ በዓለም ገበያ የተሻለ የንግድ ዕድል ሊያገኙ የሚችሉበት ሁኔታን የሚያቃልላቸው አዲስ የንግድ ውይይት እንዲጀመርና የልማት እና የርዳታ ፕሮዤ ወጪን የሚሸፍን አንድ አዲስ ዓለም አቀፍ የርዳታ አቅራቢ ተቋም እንዲከፈት ጠይቀዋል።