የልጅነት ዘመን መዝሙሮች | ባህል | DW | 21.03.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የልጅነት ዘመን መዝሙሮች

የልጅነት ዘመን መዝሙሮች የሙዚቃ ዘርፍ በኢትዮጵያ ያልተስፋፋበት ምክንያት ምን ይሆን? ህፃናት ባህላቸውን በሚገባ አውቀው እንዲያድጉ ሙዚቃ የሚጫወተው ሚናስ ምን ያህል ነው ይላሉ?

«ህፃናት የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች» ከብዙ ህፃናት ልብ የማይጠፋ ሀረግ ነው። በእርግጥ ሀፃናት አበቦች ናቸውና የነገው ፍሬ ላይ እስኪደርሱ በሁሉም መስክ ከፍተኛ እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ ከጥበቦች ሁሉ እጅግ ረቂቅ የሆነው ሙዚቃ ህፃናት አበቦች ነገ ፍሬ ሆነው ለቁምነገር እንዲበቁ ለማስቻል አስተዋፅኦው እጅግ ላቅ ያለ እንደሆነ ጠቢባኑ በተደጋጋሚ ጊዜያት ሲገልፁ ይደመጣል። ወ/ሮ አምሳለ ሙሉጌታ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ፍሉትና ፒያኖን ጨምሮ የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ያስተምራሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነጥበባት ኮሌጅም ተባባሪ ዲን ናቸው፤ የፃናት መዝሙሮች ጠቀሜታን ያብራራሉ።
ሶስቱም ሙዚቀኞች ዋነኛ ትኩረታቸው ህፃናት ናቸው። ሙዚቀኛ ትዕግስት ጌታቸው የተለያዩ የህፃናት መዝሙሮችን በሙዚቃ ኖታ አሰናድታ ለመጪው ትውልድ እንዲቆይ ከመፅሀፍ ጋ አሳትማለች። ህፃናት በሙዚቃ እየተዝናኑ እግረመንገዳቸውን እውቀት እንዲገበዩ በሚል። ሌላኛዋ ሙዚቀኛ ሣምራዊት ታደሰም እንዲሁ ህፃናት ባህላቸውን እንዲማሩና እንዲጠብቁ ለማስቻል እስተዋፅኦ ይኖረዋል ያለችውን አጭር የልጆች መፅሐፍና ሲዲ አሳትማለች።ሙዚቀኛ ህይወት ማሞ አሁን በጣት በሚቆጠሩ ሙዚቀኞች ብቻ የሚከወነው የልጆች መዝሙር ስራ ወደፊት እንዲጎለብት ጥልቅ ምኞቷ እንደሆነ በመግለፅ በዘርፉ በስፋት ያልተሰራበትን ምክንያት ይህ ነው ትላለች።

የህፃናት መዝሙሮች ይበልጥ እንዳይስፋፉ መሰናክል ከሆኑ አበይት ምክንያቶች መካከል አንዱ አቅሙ ያላቸው ግለሰቦችና ተቋማት ለዘርፉ ትኩረት የመንፈጋቸው ነገር እንደሆነ ይጠቀሳል። ለአብነት ያህል ሙዚቀኛ ትዕግስት በግሏ ያሳተመችው የልጆች መፅሀፍና የመዝሙር ሲዲ የጠበቀችውን ያህል እንዳልተሸጠላት ገልፃለች። ለዚያ ደግሞ የሙዚቃ አሳታሚዎች ለጉዳዩ እምብዛም ትኩረት ያለመስጠታቸውና ስራዋን ለህትመት ለማብቃት ያወጣችውን ወጪ እንኳን የሚሸፍን ክፍያ ያለማቅረባቸው እንደሆነ ጠቅሳለች።


በእርግጥም የልጆች መዝሙሮች ላይ ብቻ ሳይሆን ለልጆች አካላዊ እድገትና ስብዕና መበልፀግ አጋዥ የሆኑ ጉዳዮች ላይ በአጠቃላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ ያሻል። ልጆች የእናት የአባቶቻቸውን ባህልና ቋንቋ እንዲያውቁ ማድረግና ያንንም እንዲጠብቁ ማስቻል የማንኛውም ኃላፊነት የሚሰማው ማኅበረሰብ ግዴታ ነው። ሙዚቃ ህፃናቱን እያዋዛ ባህላቸው ከውሳጣቸው እንዲሰርፅ የማድረግ አቅሙ እንዲህ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት መምህርና ተባባሪ ዲን ወ/ሮ አምሳለ ሙሉጌታ

Blume Brasilien Die kleinen Kunstwerke zeigt das Kinderhilfswerk Plan in der Ausstellung WeltSpielZeug (Ethnologisches Museum/Berlin 02.04.2004 - 29.08.2004)ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ለህፃናት መዝሙሮች እድገት ጥረት እንደሚያደርግ ጠቅሷል። የሀገሪቱ ወሳኝ የሙዚቃ ተቋም ከመሆኑ አንፃር ወደፊት በዘርፉ ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ በማድረግ የተለያዩ ጥናቶችን እንደሚያከናውን፣ የህፃናት መዝሙሮች የሚስፋፉበትን ስልት እንደሚቀይስም ተስፋ እናደርጋለን። ከያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ባሻገር በኢትዮጵያ የተወሰኑ የግል የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በውጭ ሀገራት የሚገኙ አንዳንድ ኢትዮጵያዊ ተቋማት ይብዛም ይነስም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ መጠቆም ያሻል።

ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች መካከል ደግሞ በባህልና ቱሪዝም አንዱ ነው። የቢሮው ምክትል ሃላፊ የሆኑት አቶ ሙሉ ገበየሁ በህፃናት መዝሙሮች ዙሪያ ያን ያህል ሰፊ ነው የተባለ ስራ እንዳልተሰራ ጠቁመዋል። ይሁንና ግን በመስሪያ ቤታቸው ስር የሚገኘው የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር የሚያቀርባቸው የሙዚቃ ትርኢቶችና ድራማዎች እንዲሁም አሳትመው ለገበያ ያቀረቡት የተለያዩ የህፃናት መዝሙሮችን ያካተተው አንድ የሙዚቃ ሲዲ ሳይጠቀስ አያልፍም ብለዋል።

ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንደመንግስት መስሪያ ቤትነቱ የሕፃናት መዝሙሮች ላይ ልዩ ትኩረት ሊያደርግና የበለጠ ሊንቀሳቀስ ያስፈልገዋል። የሚመለከታቸው አካላትና ማኅበረሰቡ በአጠቃላይ ለልጆች መዝሙሮች ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል። መዝሙር አለያም ሙዚቃ አንዱ የባህል መገለጫ ነውና።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic