የልጅነት ልምሻን የማጥፋት ጥረት | ጤና እና አካባቢ | DW | 29.10.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የልጅነት ልምሻን የማጥፋት ጥረት

በየዓመቱ በጎርጎሪዮሳዊዉ የዘመን ቀመር ኦክቶበር 24 የልጅነት ልምሻ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚታሰብበት ዕለት ነዉ። በአንድ ወቅት ይህ በሽታ ድንገት የያዛቸዉን ህጻናት የእድሜ ልክ መፃጉዕ አድርጎ እንደሚያስቀር በመታየቱ እጅግ የሚፈራ ነበር። ክትባቱ የዛሬ 58ዓመት ገደማ ተገኘና ስጋቱ ቀነሰ። አሁን ደግሞ ፈፅሞ ለማጥፋት ጥረቱ ቀጥሏል።

በያዝነዉ የጥቅምት ወር የልጅነት ልምሻ ቀን ተመድቦለት የሚታወሰዉ ያለ ምክንያት አይደለም። በሽታዉን ለመከላከል የሚያስችለዉን የመጀመሪያዉን ክትባት ያገኘዉ ጆንስ ሳልክ የተወለደበት ወርም በመሆኑ እንጂ። በእርግጥ አሁን ለሕፃናቱ በአፍ የሚሰጠዉ የፖሊዮ ክትባት ከተገኘ 25ዓመቱ ብቻ ነዉ። ቀዳሚዉም ሆነ ይህ ክትባት ግን በትክክል በሽታዉን ለመቆጣጠር አስችለዋል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለዉ አልበርት ሳቢን በጎርጎሪዮሳዊዉ 1988ዓ,ም የቀመመዉ በአፍ የሚሰጠዉ የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት የበሽታዉን ስርጭት 99 በመቶ ቀንሶታል።

በዚሁ ወቅትም በዓለም ደረጃ የበሽታዉ አስወጋጅ ዘመቻ ተጠናክሮ ከተጀመረ ወዲህ ታላቅ ስኬት ማስመዝገብ እንደተቻለም WHO ያመለክታል። ከዛሬ 13ዓመት ወዲህም የልጅነት ልምሻ የሚከሰትባቸዉ ከአምስት አልበለጡም፤ በየዓመቱም ከ750 ሕጻናት በላይ በበሽታዉ አልተያዙም። የዓለም የጤና ድርጅት የልጅነት ልምሻ አሁን የሚገኘዉ በድሃ ሃገራት በተለይም በተገለሉ ማኅበረሰቦች ዘንድ መሆኑን ይገልጻል። ናይጀሪያና ፓኪስታን አሁን በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ሃገራት ናቸዉ።

ከዓመታት በፊት ፖሊዮ ከተለያዩ አምስት ሃገራት ፈጽሞ መጥፋት መቻሉ ተነግሮ ነበር። ከበሽታዉ ነፃ ከተባሉ ሃገራት መካከል ኢትዮጵያና ኬንያ ይጠቀሳሉ። ባለፈዉ ነሐሴ ወር ማለቂያ ገደማ ደግሞ የዓለም የጤና ድርጅት በጦርነት እና ግጭት በተተራመሰችዉ ሶማሊያ የልጅነት ልምሻ ወረርሽኝ ሳይቀሰቀስ እንዳልቀረ አመለከተ። ሶማሊያ ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከሰተዉ ወረርሽኝ ከ170 በላይ መያዛቸዉ ተገልጿል። ሶማሊያ ዉስጥ የፀጥታ ይዞታዉ በሚያሰጋበት አካባቢ ክትባቱን ማዳረስ ባለመቻሉ ችግሩ መከሰቱ ሲገለጽ፤ ከሕዝቡ ከቦታ ወደቦታ የመንቀሳቀስ ልማድ ጋ ተያይዞ ወደጎረቤት ሃገራትም እንዳይዛመት ተሰግቶ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ታዲያ ምልክቱ በኢትዮጵያም ሆነ ኬንያ መታየቱ ተነገረ። ሁኔታዉ አሁን በምንደረጃ ላይ እንደሚገኝ የጠየቅናቸዉ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የክትባት መርሃግብር አስተባባሪ አቶ ስንታየሁ አበበ፤ ከዛሬ አምስት ዓመት ጀምሮ ከልጅነት ልምሻ ነፃ ሆና በቆየችዉ ኢትዮጵያም በተለይ በሶማሌ ክልል የአጎራባቾቿ ሁኔታ ተፅዕኖዉ ታይቷል ይላሉ።

አቶ ስንታየዉ የሚገልፁት የቤተሙከራዉ ምርመራ ዉጤትም የሚያሳየዉ ሶማሊያ እና ኬንያ ዉስጥ ከተያየዉ የልጅነት ልምሻ ዓይነት ጋ ተመሳሳይ መሆኑን ነዉ። እናም በሽታዉ ከዉጭ የተዛመተ እንጂ እዚያዉ ከፅዳትና አያያዝ ጉድለት የመጣ አይደለም። እናም በሽታዉ ወደሌላ አካባቢ እንዳይስፋፋ ክትባት መሰጠቱንና በቀጣይም እንደሚሰጥ ይገልጻሉ።

Polio-Schutzimpfung in Afghanistan

በኅዳር የሚከናወነዉ የክትባት ዘመቻም ሀገር ዓቀፍ እንደሚሆን ነዉ ያመለከቱት። ዋናዉ ግን ይላሉ አቶ ስንታየሁ ኅብረተሰቡን ስለበሽታዉ ግንዛቤ እንዲኖረዉ ና የራሱንና የልጆቹን ንፅህና እንዲጠብቅ የማስተማሩ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ እንደሚሆንም ገልጸዋል።

ከአራት ዓመታት በፊት ጠፍቶ የነበረዉን የልጅነት ልምሻ በሽታ ዳግም እንዳይዛመት ለማድረግም በፌደራልና በክልሎች ደረጃ የዘመቻዉ እዝ መቋቋሙም ያም በየጊዜዉ በየአካባቢዉ ስላሉ ሁኔታዎች መረጃ በመለዋወጥ ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠሉም አቶ ስንታየሁ አስረድተዋል። ከሀገር ዉስጡ ጥረት በተጨማሪም የልጅነት ልምሻ በሽታ በቅርቡ ከታየባቸዉ አጎራባች ሃገራት ጋርም የተቀናጀ ዘመቻ ለማካሄድ የመረጃ ልዉዉጥ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። በኅዳር ወርም ተጎራባች ሃገሮቹ በዚሁ አሳሳቢ የጤና ጉዳይ ላይ የሚነጋገሩበትና መረጃም የሚለዋወጡበት ጉባኤ እንደሚኖር ገልጸዉልናል። በነገራችን ላይ የዓለም የጤና ድርጅት ሶርያ ዉስጥም የልጅነት ልምሻ በሽታ መከሰቱን ዛሬ አረጋግጧል። ከዓለም ፈጽሞ ሊጠፋ የሁለት ሃገሮች ጥረት ብቻ ይቀረዋል የተባለዉ ይህ በሽታ አሁንም አጋጣሚዎችን እየተከተለ መፈታተኑን የቀጠለ ይመስላል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic