የሌጎስ ታክሲዎችና ነፃ ኢንተርኔት | አፍሪቃ | DW | 26.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሌጎስ ታክሲዎችና ነፃ ኢንተርኔት

የሌጎስ-ናጄሪያ ትልቅ ከተማ ነዋሪዎች ታክሲ ውስጥ በነፃ ኢንተርኔት የመጠቀም እድል አግኝተዋል። «ሜትሮ-ታክሲ» የተባለው የመጓጓዣ አገልግሎት ድርጅት ከናይጄሪያ ዋና የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ጋር በትብብር ይሰራል። ይህ የታክሲ አገልግሎት ለሌጎስ ነዋሪዎች ምን ማለት እንደሆነ ሳም ኦልኮያ አጠያይቋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:00

ናይጄሪያ

አንድ የሜትሮ ታክሲ ሹፌር ተሳፋሪዎቹን ሰብስቦ የመኪናውን ሞተር አስነሳ። የተሽከርካሪው በር ላይ በደማቁ የነፃ የኢንተርኔት አገልግሎትን የሚጠቁም" Free Wifi in taxi "የሚል መልዕክት ተለጥፏል።የሜትሮ ታክሲ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ፕሪሲላ ኢቤ ድርጅታቸው ነፃ የኢንተርኔት አገልግሎት ታክሲ ውስጥ መስጠት የጀመረበት ምክንያት ፤ተሳፋሪዎች በተሽከርካሪዎች በተጨናነቀ የሌጎስ ከተማ ታክሲ ውስጥ ሲቆዩ ጊዜውን ሳይሰለቹ እንዲያሳልፉ ታስቦ ነው ይላሉ።« ለሰዓታት ትራፊክ የያዛቸው ደንበኞችን መቼም ታውቃለህ። ማቅረብ ያለብህ ዘገባዎች ይኖራሉ፣ ኢሜልህን መመልከት ትፈልጋለህ፤ እዛ ስራ ፈተህ ከመቀመጥ ኢንተርኔት በመጠቀም ህይወትህን ማቅለል ትችላለህ። ተማሪዎች ምን አዲስ ነገር እንዳለ ከማህበራዊ መገናኛ ያገኛሉ፣ መንገድ ላይ ሆነህ ስለ ትራፊክ ሁኔታ መረጃ ማግኘት ትችላለህ። መንገድ ላይ ሆነህ ዜና የመከታተል እድል አለህ።»

በናይጄሪያ የንግድ መዲና ሌጎስ ጎዳናዎች ላይ ሰዎች ለሰዓታት የተጨናነቀው ትራፊክ ይዧቸው መቆማቸው የተለመደ ነው። የሜትሮ ታክሲ ተጠቃሚዎች ነፃ የኢንተርኔት አገልግሎቱ ብዙ ነገር አቃሎልናል ይላሉ። ከነዚህ ተጠቃሚዎች አንዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያው ቻርለስ ኦፊአ ነው። ቻርለስ የታክሲው ላይ የኢንተርኔት አገልግሎት የመረጃ ልውውጥ ልማዱን እንዴት እንደቀየረው ይናገራል። « ኢንተርኔት ስራ እንዳልፈታ ያደርገኛል። ደንበኞቼን አገኛለሁ፤ ሁል ጊዜ ስብሰባ ስላለኝ እንደተንቀሳቀስኩ ነው። ይህ ለመገናኘት ጥሩ እድል ይፈጥርልኃል፤ ማለቴ በመንገድ ላይ ሆነህ፣ትራፊክ ይዞህ ያሉህን ቀጠሮዎች በሙሉ መጨረስ መቻል በጣም ጥሩ ነገር ነው። ኢንተርኔት፤ ደንበኞችን ከመሳቢያ ዘዴዎች አንዱ ነው።»

Verkehrsstau in Lagos Nigieria

ደንበኞችን መሳብ መቻል ማለት ደግሞ እንደ ሴጉን ባምግቦሴ ላሉ የሜትሮ ታክሲ ሹፌሮች ጥሩ ገበያ ማለት ነው። ሴጉን፤ ትራፊክ ሲይዛቸው ትዕግስታቸው የሚያልቅ ደንበኞች፤ ኢንተርኔት ከተጀመረ በኋላ ቁጥራቸው ቀንሷል ይላል። እሱ እንደሚለው ደንበኞቹ በኢንተርኔት ስለሚጠመዱ ብዙም ውጪ ስለሚሆነው ነገር አይጨነቁም።« እንዲህ ያለው ነገር ቀንሷል። የሚያስቸኩል ነገር የለም። አንዳንዴ ደንበኞች ሲቸኩሉ አብረህ የምትፈጥንበት አጋጣሚ ነበር። ያም ሲሆን አንዳንዴ ሹፌሮች ትኩረታቸው ይሰረቃል። ግን አሁን ተመችቷቸዋል። መስሪያ ቤት በስራ ቢወጠሩም በተሽከርካሪ መጨናነቅ መንገድ ላይ ቢጎተቱም ታክሲ ውስጥ ዋይፋይ ካገኙ ዘና ይላሉ። እና መጣደፍ፣ መቻኮል የመሳሰሉት ነገሮች ከንግዲህ የሉም።»

ነፃ ኢንተርኔት ያለው የሌጎስ የታክሲ አገልግሎት በትራፊክ መጨናነቅ የተጠመዱ ሰዎችን አለመረጋጋት ያቃለለ ይመስላል። አጋጣሚውን ተጠቅመውም ዘግይተን በደረስን የሚሉም አንዳንዶች አይጠፉም።

ሳም ኦልኮያ

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic