የላይቤሪያ የምርጫ ክስ | አፍሪቃ | DW | 03.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የላይቤሪያ የምርጫ ክስ

ለመጪው ማክሰኞ ጥቅምት 28 ቀነ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የላይቤሪያ ሁለተኛ ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንቅፋት ገጥሞታል፡፡ በመጀመሪያው ዙር ከተፎካከሩት ዕጩ ፕሬዝዳንቶች ሶስተኛ ደረጃውን ያገኙት ቻርለስ ብሩምስካይን “ምርጫው ተጭበርብሯል” ሲሉ በፍርድ ቤት ከስሰዋል፡፡ የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክሱን ዛሬ ተመልክቷል፡፡ 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:03
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:03 ደቂቃ

የተቃዋሚ ዕጩ “ምርጫው ተጭበርብሯል” ሲሉ ከስሰዋል

ከጎርጎሮሳዊው 1989 ጀምሮ ላይቤሪያን ለ14 ዓመት ሲያምሳት በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት ለሀገሬው ዜጎች የተስፋ ቀንዲል የነበረ ክስተት ድንገት ከወደ አውሮጳ ብቅ አለ፡፡ የሀገራቸው ልጅ ጆርጅ ዊሀ የአውሮጳ ስመ ጥሮቹን የእግር ኳስ ክለቦች ፓሪስ ሴን ዠርማ እና ኤሲ ሚላንን ባለድል ሲያደርጋቸው በቴሌቪዥን ተመለከቱ፡፡ የአፍሪካ እና የአውሮጳ ኮኮብ ተብሎ ሲሸለም ደግሞ በብዙዎች ልብ ነገሰ፡፡ አድናቂዎቹ ለስያሜውም አልሰሰቱም፡፡ አሁንም ድረስ የሚጠሩት “ንጉስ ጆርጅ” እያሉ ነው፡፡

በእግር ኳስ ሜዳ ሀገሩን በበጎ ያስጠራው ዊሃ በፖለቲካው መንደርም ተመሳሳዩን ለመድገም ከአንድም ሁለት ጊዜ ሙከራ አድርጓል፡፡ በ1997 ዓ.ም አሁን በስልጣን ላይ ካሉት ኤለን ጆንሰን ሴርለፍ ጋር ተወዳድሮ ተሸንፏል፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት ደግሞ የፕሬዝዳንቷን ልጅ አሸንፎ የላይቤሪያ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሆኗል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ በተወዳደረበት እና መስከረም 30 በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ 38.4 በመቶ የመራጮችን ድምጽ በማግኘት ከተፎካካሪዎቹ ልቆ ተገኝቷል፡፡ ከዕጩ ፕሬዝዳንቶቹ መካከል ማናቸውም ከ50 በመቶ በላይ ማስመዘገብ ባለመቻላቸው ግን ሁለተኛ ዙር ምርጫ እንዲደረግ ግድ ብሏል፡፡ 

ዊሃ የዛሬ 12 ዓመት በተወዳደረበት ምርጫ በሁለተኛው ዙር መሸነፉን የሚያስታውሱ አሁንም ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይገጥመው ሰግተዋል፡፡ የቀድሞው የእግር ኳስ ኮከብ ለደጋፊዎቹ ባለፈው ሳምንት ባደረገው ንግግር ምርጫው የቱንም ያህል ዙር ቢካሄድ በደጋፊዎቹ እንደሚተማመን ለማሳየት ሞክሯል፡፡ “የመጀመሪያው ዙር ሆነ ሁለተኛ፣ ሶስተኛ፣ አራተኛ፣ አምስተኛ፣ ስድስተኛ፣ ማንኛውም ዙር ቢሆን መዘጋጀት ይኖርብናል” ብሏል ዊሃ በደጋፊዎች ጩኸት ታጅቦ፡፡

ዋነኛው ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ራሱን ለፉክክር እንዲህ ቢያዘጋጅም በመጀመሪያ ዙር ምርጫ ሶስተኛ ሆነው የጨረሱት ዕጩ ፕሬዝዳንት ቻርለስ ብሩምስካይን በፍርድ ቤት የከፈቱት ክስ ግን በምርጫው ላይ እንቅፋት ጋርጧል፡፡ ከአጠቃላይ መራጮች 9.6 በመቶ ድምጽ ብቻ ያገኙት ብሩምስካይን “ምርጫው ተጭበርብሯል” ሲሉ ለሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከስሰዋል፡፡ በምርጫው ወቅት የተስተዋሉ “ሕግን ያልተከተሉ አካሄዶች የድምጽ አሰጣጡን አጠልሽተውታል” ሲሉም ወንጅለዋል፡፡

ብሩምስካይን ልክ እንደ የኬንያው ተቃዋሚ ዕጩ ራይላ ኦዲንጋ ሁሉ የሀገሪቱ የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚሽን ኃላፊዎች ከስልጣናቸው እንዲነሱ እና በሌሎች እንዲተኩ ጠይቀዋል፡፡ ከሁለተኛ ዙር ምርጫ ይልቅ ድጋሚ ምርጫ መካሄድ አለበት ባይም ናቸው፡፡  ብሩምስካይንን ለውድድር ያቀረበው የነጻነት ፓርቲ ዋና ጸሀፊ ዲናያል ሲኖኢ ፓርቲያቸው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰበትን ምክንያት ያስረዳሉ፡፡ 

“የነጻነት ፓርቲ ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ የሚጎተጉተው መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም የተካሄደው የነጻ፣ ፍትሃዊ እና ግልጽ ምርጫን አነስተኛ መስፈርት እንኳ የሚያሟላ ባለመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው ውጤቱን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደረጃ የምንሟገተው፡፡ የምንጠይቀው ጉዳዩን ተመልክተው ድጋሚ ምርጫ እንዲኖረን እና ላይቤሪያውያን ይህን ሀገር በአግባቡ የሚያስተዳድር መሪ እንደሚመርጡ ነው” ይላሉ የፓርቲ ዋና ጸሀፊ፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲውን ክስ የተቀበለው የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ማክሰኞ ለሁለተኛው ዙር ምርጫ የሚደረገው ዝግጅት እንዲቋረጥ ወስኗል፡፡ ዛሬ ደግሞ ክሱን ተመልክቶ ሁለተኛው ዙር ምርጫ እንደታሰበው ማክሰኞ ጥቅምት 28 ይካሄድ አሊያም ለሌላ ጊዜ ይተላለፍ እንደው ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ የላይቤሪያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክሱን መመልከት ከመጀመሩ በፊት አስተያየታቸውን የተጠየቁ ቻርለስ ኮሮሞሃ የተባሉ የመዲናይቱ የሞኖሮቪያ ነዋሪ በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፈን ከተፈለገ ተቃዋሚዎች ያነሱት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል፡፡

“ይህ የህግ ጉዳይ ነው፡፡ ህግ ደግሞ ከለላ የሚሰጠው ለአብላጫዎቹ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ አብላጫዎቹ ሁሉ ለአናሳዎቹም ከለላ ይሰጣል፡፡ ስለዚህ አንድ ፓርቲ በሂደቱ የተለየ ሃሳብ ካለው እና ከጥርጣሬ ያለፈ ማረጋገጫ ማቅረብ የሚችል ከሆነ ጥያቄው ህጋዊነት ይኖረዋል፡፡ እኔ እንደማስበው ለሰላም ሲባል ጉዳዩን መመልከት ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ተጨማሪ ችግሮች ያመጣል” ሲሉ ነዋሪው ያስጠነቅቃሉ፡፡  

 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሰ    

Audios and videos on the topic