የላምፔዱዛው አደጋ እና የአውሮፓ ህብረት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 08.10.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የላምፔዱዛው አደጋ እና የአውሮፓ ህብረት

በቅርብ ጊዜ የአውሮፓ የጀልባ ስደተኞች ታሪክ እጅግ አስከፊው አደጋ ነው ። ባለፈው ሃሙስ በኢጣልያዋ የላምፔዱዛ ደሴት አቅራቢያ ወደ 500 የሚጠጉ ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ በእሳት ከተያያዘች በኋላ ሰጥማ የደረሰው አደጋ ። እንደ እድል ሆኖ 155ቱ ቢተርፉም የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 274 ከፍ ብሏል ።

ባለፈው ሃሙስ በኢጣልያዋ ደሴት ላምፔዱዛ አቅራቢያ በሰጠመችው ጀልባ ውስጥ ከነበሩት ስደተኞች አብዛኛዎቹ መሞታቸው ወይም ደብዛቸው መጥፋቱ ማነጋገሩ ቀጥሏል ። ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት በአደገኛው የባህር ላይ ጉዞ በአሳዛኝ ሁኔታ ሲጠፋ የሃሙሱ አደጋ የመጀመሪያ ባይሆንም ከ 5 ቀናት በፊት በአንዴ ያለቁት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑና የድረሱልን ጥሪ ያሰሙ የነበሩት በርካታ ስደተኞች ሰሚና ተመልካች አጥተው የውሃ ሲሳይ መሆናቸው ብዙ ጥያቄዎችን አስነስቷል ። በብዛት ከሶማሊያና ከኤርትራ ለመጡት ስደተኞቹ እልቂት ተጠያቂው ማነው ? አደጋውን ማስቀረት ይቻል ነበር ወይ ? አጠቃላዩ መፍትሄስ ምንድን ነው ? የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች እዚህ አውሮፓ ከዘግናኙ አደጋ በኋላ መላልሰው የሚነሱ ትችት አስተያየትና ተቃውሞ የሚሰነዘርባቸው ጉዳዮች ሆነዋል ። ከዚሁ ጋርም የአውሮፓ ህብረት የተገን ጠያቂዎች አቀባበል ደንብ ዋነኛው መነጋገሪያ ሆኗል ። በሆላንዱ ቲቡርግ ዩኒቨርስቲ የዓለም ዓቀፍ ማህበራዊ ሃላፊነቶች መምህርትና መቀመጫውን ብራሰል ቤልጂግ ያደረገው የአውሮፓ የውጭ ፖሊሲ አማካሪዎች ማዕከል ሃላፊ ዶክተር ሚርያም ቫን ራይሰን ጉዳዩ በቅርብ የሚከታተሉና በሲና በረሃ የስደተኞችን ፈተና የሚገልፅ መፀሃፍ ደራሲ ናቸው ። ተደጋግሞ ሲከሰት የቆየን ጉዳይ አሁን እንደ አዲስ ከማንሳት ይልቅ የስደተኞች ችግሩ በሚፈታበት መንገድ ላይ ቢተኮር ይበጃል ይላሉ ።

«ችግሩ ለረዥም ጊዜ የሚታወቅ ሆኖ ሳለ አሁን ከሌላው ጊዜ በተለየ ጉዳይን ማንሳታችን አሁን መጨነቅ መጀመራችን ያበሳጫል ። ለስደተኞች ማሰቡ ና በጉዳዩ ላይ መነጋገር መጀመሩ ግን ጥሩ ነው ። በእርግጥ አሁን መወያየት ያለብን ወደ አውሮፓ የሚመጡ ስደተኞች በመሉ የተገን ጥያቄአቸውን ወደ ሚመለከተው አካል ማቅረብ በሚችሉበት መንገድ ላይ ነው ። »በርካታ ስደተኖች የሚጎርፉባት የኢጣልያዋ ደሴት ላምፔዱዛ ከዋናው የኢጣልያ መሬት ይልቅ ለቱኒዝያ ትቀርባለች ። ስደተኞች ወደ ዚህች ደሴት በብዛት መግባት የጀመሩት በተለይ እጎአ ከ1999 ማለትም ከዛሪ 14 ዓመት ግድም አንስቶ ነው ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑ ከአፍሪቃና ከእስያ በርስ በርስ ጦርነቶች በረሃብና በልዩ ልዩ ችግሮች ምክንያት የተሰደዱ ሰዎች በአደገኛ የባህር ላይ ጉዞ ደሴቲቱ ገብተዋል ። እነዚህ እድል ቀንቷቸው በህይወት የደረሱት ሲሆኑ ወደ ላምፔዱዛ ሲያቀኑ የውሃ ሲሳይ የሆኑት ደግሞ ከ 10 እስከ 20 ሺህ ይገመታሉ ። ካለፈው ዓመት ጥር ወዲህ 33,100 ስደተኞች ላምፔዱዛ ገብተዋል ። አብዛኛዎቹም ከሶማሊያ ከኤርትራ እንዲሁም ከግብፅ ከሊቢያ እና ከቱኒዝያ ነው ። ባለፈው ሃሙስ በሰጠመችው ጀልባ ከተሳፈሩት አብዛኛዎቹ ኤርትራውያንና ሶማሊያውያን ናቸው ። ዶክተር ሚርያም ለሃሙስ አደጋ በዋነኛነት ተጠያቂ የሚያደርጉት ስደተኞቹ የመጡበትን ሃገር መንግሥት ነው ።

« ብዙዎቹ ኤርትራውያን በመሆናቸው ዋናው ተጠያቂ የኤርትራ መንግሥት ነው ። ብዙ ሰዎች ኤርትራን ጥለው እንደሚወጡ እናውቃለን ምክንያቱም እዚያ ተስፋም ሆነ ምንም ዓይነት እድል የላቸውም ። እንደሚመስለኝ በአሜሪካን ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት CIA ግምት በየወሩ 5 ሺህ ኤርትራውያን በየወሩ ሃገራቸውን ጥለው ይወጣሉ ። ይህ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው ። ከነዚህ መካከል ጥቂቶች ናቸው ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚሞክሩት ምክንያቱም መንገዱ በረሃውን ና ውሃውን አቋርጦ መምጣት በጣም አደገኛ ነውና »

ለስደተኞች እንግልትና ስቃይ ብሎም ሞት ዶክተር ሚርያም ተጠያቂ የሚሉት ስደተኖቹ የመጡበትን ሃገር ብቻ አይደለም ። ከለላ ፍለጋ አለያም እንደ መሸጋገሪያ የሚጠቀሙባቸውን ሃገራትም ጭምር እንጂ ።

« የሰሜን አፍሪቃ ሃገራትም ተጠያቂ ናቸው ። የስደተኞቹ ደህንነት አያስጠብቁም ። ስደተኞቹን የሚያስቀምጡት ማጎሪያ ጣቢያዎች ውስጥ ነው የተገን ጥያቄ ማመልከቻ የማስገባት መብትም የላቸውም ። በዚህ ረገድ በየመን በግብፅና በሊቢያ የሚፈፀመው እንዲሁም በሲና በረሃ ስደተኞች የሚደርስባቸው ቁም ስቅል አንዳንዴም የሚደርስባቸው ግድያ ይጠቀሳል ። »ከዚህ ሁሉ ችግር ማምለጥ የቻሉ ስደተኞቹ ከሰሜን አፍሪቃ ወደ አውሮፓና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሲያቀኑም የሚጠብቃቸው የተዘጋ በር ነው ።

« እስራኤልና የአውሮፓ ህብረት በሚችሉት መንገድ ሁሉ ስደተኞችን ለመግፋት ነው የሚሞክሩት ። እስራኤል ድንበሯን በግንብ አጥራለች ። ወደ እስራኤል የመሄጃው መንገድ የሚቻል አይደለም ። የአውሮፓ ህብረትም ስደተኖችን የጫኑ ጀልባዎች ወደ አውሮፓ ህብረት እንዳይደርሱ ነው የሚያደረገው ። »

የጀልባ ስደተኞች አደጋ ሲያጋጥማቸው ብዙውን ጊዜ ቀድመው የሚደርሱላቸው የአካባቢው አሣ አጥማጆች ናቸው ። ይሁንና ሃሙስ በሰጠመችው ጀልባ ውስጥ የተሳፈሩት ስደተኞች የድረሱልን ጥሪ ሲያሰሙ አሣ አጥማጆች አይቶ እንዳላየ ነበር ያለፏቸው ። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከዚህ ቀደም የነፍስ አድን እርዳታ በመስጠት ስደተኞችን ከመስጠም ያዳኑ አሣ አጥማጆች ከደላሎች ጋር በመተባበር እየተጠረጠሩ በመከሰሳቸው ነው ። የሚደርስላቸው ያጡት ስደተኞች ሰው ቢያየን ብለው ልብሶቻቸውንና ብርድ ልብሶቻቸውን በእሳት ከለኮሱ በኋላ እሳቱን የተመለከቱ ሃገር ጎብኚዎች ለኢጣልያ የባህር ጠባቂ ፖሊሶች በጠቆሙት መሰረት ነው 155 ቱ ስደተኞች በህይወት ሊተርፉ የቻሉት ። ከአደጋው የተረፉት እንደሚሉት ጀልባዋ ከሁለት ሳምንት በፊት ነው ከሊቢያ ነበር የተነሳችው ። ወደ ላምፔዱዛ በመጠጋት ላይ ሳለች ሞተሯ ተበላሽቶ ነው የሰጠመችው ። አውሮፓውያን ደጃፋቸው ለደረሰው አደጋ እርዳት መስጠት አለመቻላቸው ብዙ ቁጣን ቀስቋሷል ። ይፋዊው የአውሮፓ የተገን አሰጣጥ መርህ አባል ሃገራት ደንቡን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ነው ። ይሁንና ይህ በሁሉም አባል ሃገራት ተግባራዊ እንደማይሆን ዶክተር ሚርያም በምሳሌ ያስረዳሉ ።

«የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት በሙሉ አብዛኛዎቹ ኤርትራውያን ተገን የመጠየቅ አሳማኝ ምክንያት እንዳላቸው ይስማማሉ ። ተገን ከሚጠይቁ ኤርትራውያን 80 ከመቶው ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያገኛል ። ሆኖም የተለያዩ ሃገራትን መርሆች ስንመለከት አንዳንዶቹ ተገን ጠያቂዎችን ካስገቡ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ማጎሪያ ካምፖች ይልኩዋቸዋል ። ከዚያ ሆኖ ተገን መጠየቅ ደግሞ አስቸጋሪ ነው ። »

እስካሁን በሚሰራበት የአውሮፓ ህብረት የጋራ የስደተኞች አቀባበል ደንብ መሠረት ስደተኞች ተገን ለማግኘት ማመልከት የሚችሉት መጀመሪያ በገቡት የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገር ነው ። ይህ ደግሞ ስደተኞች በብዛት በሚጎርፉባቸው በህብረቱ ደቡባዊ ድንበር ሃገራት በኢጣልያ በግሪክና በስፓኝ ይተቻል ። እነዚህ ሃገራት የሚመጡት ስደተኞች ከአቅማችን በላይ ሆነዋልና ሌሎች አባል ሃገራትም ስደተኞቹን ይከፋፈሉ የሚል አቤቱታ በተደጋጋሚ ያሰማሉ ። ይሁንና በሰሜናዊ አውሮፓ የሚገኙት አባል ሃገራት በበኩላቸው በህብረቱ ተገን ላማግኘት ካመለከቱ ስደተኞች አብዛኛዎቹን የምናቀበለው እኛ ነን ሲሉ ይከራከራሉ ። እጎአ በ2012 ጀርመን ፈረንሳይ ብሪታንያ ስዊድን ና ቤልጂግ 102,700 ተገን ጠያቂዎችን መቀበላቸውን ነው በማስረጃነት የሚያቀርቡበት። ይሁንና ዶክተር ሚርያም ይህ መከራከሪያ ሆኖ ሊቀርብ አይገባም ከዚያይልቅ መፍትሄው ተባብሮ ችግሩን በጋራ እንዲሁም በህብረቱ ኮሚሽን ደረጃ መፍታት ነው ይላሉ ።

« ከሁሉ አስቀድሞ ወደ አውሮፓ በስደት የሚመጡ”genuine asylum seekers” እውነተኛ ተገን ጠያቂዎች እንደሆኑና ጉዳያቸው መታየት እንዳለበት ሊታወቅ ይገባል። አብዛኛዎቹ ተገን ጠያቂዎች ደቡባዊ አውሮፓ እንዳይከማቹ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ተገን ጠያቂዎችን የሚከፋፈሉበት እቅድ ያስፈልጋል ። በመጨረሻም የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የህብረቱን የጋራ የተገን አሰጣጥ መርህ ለማቀናጀትና አባል ሃገራትም ለመርሁ ተገዥ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚያስችለው ጠንከር ያለ ሥልጣን ሊሰጠው ይገባል »

ዛሬ ሉክስምቡርግ ውስጥ የተሰበሰቡት የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሃሙሱ እልቂት እንዳይደገም ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይ መክረዋል ። መሰል አደጋ ከአሁን በኋላ አለመድረሱን ግን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ያዳግታል ። ትናንት እንኳን 200 ስደተኞችን የጫነች መርከብ በኢጣልያ የባህር ክልል ውስጥ ከመስጠም የዳነችው ሁለት በአጠገቧ ያልፉ የነበሩ መርከቦች ታድገዋት ነው ። ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ የኢጣልያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች 350 ስደተኞች ን ያሳፈሩ ሁለት ጀልባዎችን ይዘዋል ።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic