የሊብያ እና የኢራን መሪዎች በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ | ዓለም | DW | 24.09.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሊብያ እና የኢራን መሪዎች በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ

የሊብያ መሪ ሞአመር ኧል ጋዳፊ እና የኢራን ፕሬዚደንት ማህሙት አህማዲኔዣድ ትናንት በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ያሰሙት ዲስኩር ትልቅ ቁጣ አስከተለ።

default

ሞአመር ኧል ጋዳፊ

ፕሬዚደንት አህማዲኔዣድ ካሁን ቀደም እንዳደረጉት ሁሉ የዘንድሮውም ዲስኩራቸው ጸረ ሴማዊ ነበር፤ የሊብያው አቻቸው ጋዳፊ የተንዛዛውንና አንድ ሰዓት ተኩል የፈጀውን ዲስኩራቸውን ባሰሙበት ወቅት የዓለሙን መንግስታት ድርጅት ቻርታ ቀዳደው እስከመጣል ርቀው ነበር የሄዱት። በዚህም የተነሳ አንዳንዶች ዲስኩሩን አቋርጠው የጉባዔውን አዳራሽ ለቀው ወጥተዋል። ይሁንና፡ የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ሌና ቦደቫይን እንደምትለው፡ የነዚህ ዓይነት መሪዎችን ዲስኩር ረግጦ መውጣት እና እነዚህን መሪዎች ከጉባዔው ማግለል መፍትሄ አይሆንም።

Demo der Iraner gegen Mahmood Ahmadinejad in Köln

በፕሬዚደንት ማህሙት አህማዲኔዣድ አንጻር በኒውዮርክ የተደረገ ተቃውሞ ሰልፍ

ነፍሰገዳዮችና አሸባሪዎች እንዴት በተመድ ጉባዔ ላይ ይጋበዛሉ በሚል በያመቱ የሚሰማው ጥያቄ ዘንድሮም ጎልቶዋል። የአከራካሪዎቹን መሪዎች ዲስኩር ረግጦ መውጣት መፍትሄ አይሆንም ባለችው ቦድቫይን አስተያየት መሰረት፡ ጋዳፊ በዲስኩራቸው ራሳቸውን መሳቂያ ከማድረግ አልፈው አዋርደዋል። ለዚህም ነው እርሳቸውን የመሰሉ መሪዎች በተመድ ውስጥ ንግግር ማሰማት ይገባቸዋል የሚባለው። ምክንያቱም ያኔ የጉባዔው ተሳታፊዎች ንግግሩን ላለማድመጥ እያሉ አምባገነኑን ባዶ ክፍል ውስጥ ጥለው ለመውጣት ይችላሉና። እነዚህ ዓይነቶቹ መሪዎች ባይጋበዙ ኖሮ ግን ይህን ዓይነት ውርደት ሊደርስባቸው አይችልም ነበር። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህን ዓይነቱን ሁኔታ ጠንክሮ መቋቋም ይኖርበታል።

ሊብያ፡ ሰሜን ኮርያ እና ኢራን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አባላት ናቸው። የተመድ ዋና ጸሀፊ ባን ጊ ሙን ደግሞ ሁሉንም አስማምተው ለመምራት የሚፈልጉ መሪ ናቸው። ዋና ጸሀፊው ልክ እንደ አንድ የክፍል አስተማሪ ለአስቸጋሪ ተማሪዎችም፡ የነዚህን ተማሪዎች ስህተት ለማስተናነስ ወይም እንዳላየ ለማየት ሳይሞክሩ ዕድል ይሰጣሉ። ሰላሳ ተማሪዎች ባሉበት ክፍል ውስጥ አስቸጋሪ ተማሪዎች እንዳሉ ሁሉ፡ አንድ መቶ ዘጠና ሁለት አባል ሀገሮች በያዘው የተመድም ሁኔታው ተመሳሳይ መሆኑንን ባን ጊ ሙን በመጠቆም፡ ቢገለሉ ይበልጡን አሳሳቢ ሊሆኑና መገለላቸውን እንደ ጀብደኝነት ሊጠቀሙበት ስለሚችሉ ሊገለሉ አይገባም ባይ ናቸው።

በኒው ዮርክ የሚታተም አንድ ዕለታዊ ጋዜጣ እንኳን ለእኩዮቹ መሪዎች ሰልፍ በደህና መጣችሁ በሚል ርዕስ ስር በመጀመሪያ ገጹ ባሰፈረው ዘገባው ላይ ጋዳፊ፡ አህማዲኔዣድና ሁጎ ሻቬዝን እንደተመድ የክብር እንግዶች የሚያሳይ ፎቶ አስቀምጦዋል። ይሁንና፡ ገዢዎች በተመድ ጉባዔ ላይ ዲስኩር ማሰማት የለባቸውም ሊባል ይቻል ይሆን ይሆናል፤ ግን አንድን መሪ እኩይ ነው ብሎ የሚፈርደው ማን ነው? መለኪያውስ ምንድን ነው? አንዱ ሌላውን እንደ እኩይ ይመለከታል። ዩኤስ አሜሪካ ለምሳሌ ለበርካታ ሙስሊም አክራሪዎች እጅግ የተበላሸች ሀገር ሆና ትታያለች። ሌሎች ደግሞ በርካታ አፍሪቃውያት ሀገሮች ወደጉባዔው መጋበዝ የለባቸውም ባዮች ናቸው። ቻይና እና ሩስያስ እንዴት ነው የሚታዩት? የትኞቹ መለኪያዎች ናቸው የአንድን መሪ ዲስኩር ረግጦ መውጣት የሚያስችሉት?

ለሰብዓዊ መብት መከበር እና ለዓለም ሰላም የቆመው የዓለሙ መንግስታት ድርጅት ይህ ዓይነቱ አሰራር አያስፈልገውም። የተመድ የአምባገነኖችን አነጋገር እና የሚያስተጋቡትን መልዕክት ራሱ ባስቀመጣቸው እሴቶቹ ትርጉም የማሳጣት አቅም አለው። ምንም እንኳን አቅም አልባ እየተባለ ወቀሳ ቢቀርብበትም፡ በሚያወጣቸው እና በሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች እና ማዕቀቦች ተገቢውን ርምጃ መውሰድ ይችላል። የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ጎርደን ብራውን እንዳጎሉት፡ ወደተመድ ጉባዔ የሄዱት የድርጅቱን ቻርታ ለማስከበር እንጂ ለመቀዳደድ አልነበረም።

ዴሞክራሲ በግዳጅ በሚያርፍ የማግለል ርምጃ ሳይሆን ከውስጥ በሚነቃቃ እምነት ይበልጥ ሊጠናከር ይችላል። በኢራን የታየው ሁኔታ ይህን አረጋግጦዋል። ዓለም በአጽናፋዊ ትስስር በተቀራረበችበት ባሁኑ ጊዜ የሚሰራበት መረጃ የማግኘቱንና የመለዋወጡን ሂደት የሚያራምደው እጅግ ፈጣኑ ዘመናይ የመገናኛ መረብ ዴሞክራሲን ያነቃቃል። ብዙ ሰዎች የተሻለ ትምህርት በሚያገኙበት፡ ዕውቀት በሚገበዩበት፡ የግል አስተያየት በሚያስተናግዱበትና በመረጃዎች አጠቃቀም ላይ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረጉ የተሻለ ይሆናል። በመሆኑም፡ የአንድን መሪ ዲስኩር ረግጦ በመውጣት ፈንታ ትምህርትን ማበረታታቱ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

ሌና ቦደቫይን/አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic