በሊባኖስ በመልዕክት መቀበያ ስልኮች የደረሱ ፍዳታዎች ያደረሱት ጉዳት
ሐሙስ፣ መስከረም 9 2017ፍንዳታዎቹ በተለያዩ ቦታዎችና በተለያዩ ሰዎች ላይ ግን ደግሞ በአንድ ጊዜ የተፈጸሙ በመሆናቸው በመላ ሊባኖስ ፍርህት እንዲነግስና ውዥንብርም እንዲስፋፋም አድርገዋል። መገኛና ብዙሀን ከሆስፒታል የተገኙ ምንጮን ጠቅሰው እንደዘገቡት ከሆነ አብዛኛዎቹ ቁስለኞች ጉዳት የደረሰባቸው በዓይናቸውና እጆቻቸው ላይ ነው። በዚህም ዕይታቸውን ያጡና ጣቶቻቸው የተቆረጡባቸውም ጥቂቶች አይደሉም።
ድርጊቱን የፈጸመው አካል
ጥቃቱ የተፈጸመው በእስራኤል ሳይሆን አይቀርም ይባል እንጂ፤ እሳራኤል ግን እሳክሁን ሀላፊነቱን አልወሰደችም። ሆኖም ግን ይህ የግል የኤሊክትሮኒስ መሳሪያዎችን በመጠቀም ጉዳት የማድረስ ስልት ሰዎች በግል በሚገዙዋቸው የኤሌክትሮኒክስ መገናኛዎቻቸው ሊጠቁና ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል የሚያሳይ በመሆኑ አሳስቢነቱ የሁሉም የኅብረተስብክክፍል ሆኗል።
ፈንጂዎቹ ስልኮች መቼና እንዴት ወደ ሊባኖስ ገቡ?
እነዚህ ፈንጂ ያዘሉ የኢሌክትሮኒኪስ መገናኛ መሳሪያዎችና ሌሎችም ፈንጂ የተገጠመላቸው የእጅ ሬዲዮኖችና ኮምፕዩተሮች በማን እንደተሠሩና መቼና እንዴት ወደ ሊባኖስ እንደገቡ ብሎም ለሂዝቦላ አባላት እንዲደርሱ እንደተደረገ እስካሁን ግልጽ አይደለም። ቀደም ሲል የሂዝቦላ መሪዎች ስማርት ስልኮች ለጠላት ሊያጋልጡ እንደሚችሉ ማስታወቃቸውን ተከትሎ በተለይ የሂዝቦላ አባላት በገመድ አልባ የድምጽና የጽሑፍ መልክት ማስተላለፊያ ስልኮች እንዲጠቀሙ የተነገረ ሲሆን፤ ይህን ተክትሎም በርካታ የድምጽ መቀበያ ስልኮች ወይም ፔጀሮች ወደ ሊባኖስ እንደገቡና በአብዛኛው በሂዝቦላ ኣባላት እጅ እንደገቡ ነው የሚነገረው። ስልኮቹ በአንድ ሀንጋሪ በሚገኝ የታይዋን ኩባንያ የተሠሩ እንደሆነ ቢነገርም፤ ታይዋን ግን ፋብሪካው በሀንጋሪ ስለሚሠራውና የሚያሰራጫቸው ምርቶች ዕውቀቱ እንደሌላት ገልጻለች። የሀንጋሪ መንግሥትም ስለነዚህ ፈንጂ ተሸካሚ ስልኮች አመራረትና ስርጭት የሚያውቀው ነገር እንደሌለ በመግለጽ ምርመራ እንደሚደረግ አስታውቋል።
ስልኮቹ ፈንጂ ሊሽከሙ የሚችሉበት የቴክኖሎጂ ስልት
በስልኮቹ ሊፈነዱ የሚችሉ መሳሪያዎችን ማስቀመጥ መቻሉ ብቻ ሳይሆን በአንድ ጊዜ ሊፈነዱ የሚችሉበት ቴክኖሎጂ ዋናው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው። ሚስተር ኡጄኖ ሊሊ የተባሉ የቴክኖሎጂ ኤክስፐርት ለዶቼ ቬለ ሲገልጹ እንደተሰሙት፤ ምናልባት ሊፈነዱ የሚችሉት ንጥረ ነገሮች በምርት ወይም በስርጭት ወቅት በስልኮቹ እንዲገቡ ሳይደረግ አልቀረም፤ «ምናልባት ሊሆን የሚችለው በምርት ወይም በሥርጭት ጊዜ ነው። ስልኮቹ እንዲፈነዱና ጉዳት እንዲያደርሱ የሚያስችላቸውን የፈንጂ ቅመም ሊጫኑና ከዚያም ከርቀት እንዲፈነዱ ሊደረግ ይችላል።» በማለት ሙያዊ ግምታቸውን ተናግረውል።
የጥቃቱ አላማና በአሁኑ ወቅት የተፈጸመበት ምክንያት
ብዙዎቹ ስልኮች ከአምስት ወራት በፊት እንደገቡና ምናልባትም የእስራኤል መረጃ ክንውኑ ሳይደርሰበት አልቀረም ብሎ ሲገምት እንዲፈነዱ ሳያደርግ እንዳልቀረ ተንታኞች የሚናገሩ ሲሆን፤ አላማውም ሂዝቦላ የኢስራኤልን የቴክኖሎጂና የሰለላ አቅም ሊቋቋም እንደማይችል በማሳየት ፍርሀትና ውዥንብር ለመፍጠር እንደሆነ ይናገራሉ። ድርጊቱ ግን በአካባቢው ያለውን ውጥረት የሚጨምርና ምናልባትም ሌላ ጦርነት በሊባኖስ ግምባር ሊከፍት እንደሚያስችል ነው በብዙዎች ዘንድ የሚታመነው።
የአሜሪካና አውሮፓ አስተያየት
አሜሪካ በዚህ ምናልባትም የእስራኤል ድርጊት ሳይሆን አይቀርም በሚባለው ጥቃት፤ እንደሌለችበትና ይልቁንም በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍንና በጋዛም ተኩስ እንዲቆምጥረት እያደረገች መሆኑን አስታውቃለች። የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ሚስተር ጆሴፍ ቦርየል በኅብረቱ ስም ባወጡት መግለጫ ግን ድርጊቱን አውግዘው፤ ማንም ይፈጽመው ማን እንደዚህ ዓይነቱ ማንንም የማይለይ የጅምላ ጥቃት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስታውቀዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ በበኩላቸው ትናንት በኒውዮርክ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ድርጊቱን አደገኛ ብለውታል፤ «ይህ አደገኛ አካሄድ ነው። ሰላማዊ መገልገያ ቁሳቁሶች የጦር መስሪያ እንዳይሆኑና ለጦርነት እንዳይውሉ ከፍተኛ ቁጥጥር ማደረግ ያስፈልጋል» በማለት መንግሥታት ይህንን ተግባራዊ የሚያደርጉበት ሕግ ሊኖር ይገባልም ብለዋል።
ገበያው ንጉሤ
ሸዋዬ ለገሠ
ፀሐይ ጫኔ