የሊቢያ ጦርነት ድልና ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች | ዓለም | DW | 03.10.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሊቢያ ጦርነት ድልና ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች

የሜድትራኒያን ደሴቲቱ ትንሽ ሐገር ሞልታ ደግሞ የአዉሮጳ ሕብረት አባል ናት።እዚያ የደረሱ ኢትዮጵያዉያን እንደሚሉት የሞልታ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን ባለሥልጣናትና የሐገሪቱ ፀጥታ አስከባሪዎች የሚያደርሱባቸዉ ግፍ ግን ለንፅፅር ይከብዳል።

default

ስደተኞች-ቱኒዚያ ጠርፍ

እዚሕ የተወከልን መንግሥታት በሙሉ የንፁሐን ሕይወትን በማዳናችን እና ሊቢያዉያን ሐገራቸዉን ዳግም እንዲቆጣጠሩ በማድረጋችን ልንኮራ ይገባል።ተገቢ እርምጃ ነበር።


የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ካደረጉት ንግግር።መስከረም ሃያ-2011 (ዘመኑ በመሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ)።እነሱም የዋሕ፥ ንፁሐን ነበሩ።ያዉም ሊቢያ ተጠልለዉ የነበሩ-ስደተኞች።የሊቢያዉ ጦርነት-ድልና ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች መከራ የዛሬ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

ለነሱ የሊቢያ ኑሮ አስቸጋሪ ነበር።ጦርነቱ ደግሞ ስቃይ።እና ዳግም ሥደት።ወይም የመሰደድ ሙከራ።ሙከራዉ-እሱ እንደሚለዉ ለእድለኞቹ መከራ ነዉ።ላልታደሉት ደግሞ በቃ-ከጦርነት ሲሸሹ የባሕር ሲሳይ ሆኖ መቅረት።ገሚሶቹ ከጥቂት ወራት በፊት ከዚያዉ ከሊቢያ በዶቸ ቬለ በኩል የድረሱን ጥሪ አሰምተዉ ነበር።ዛሬ ግን የሉም።ማን ይናገር የቀበረ ብሎ ነገርም የለም። አልተቀበሩም።ካለ ማንያርዳ የነበረ ነዉ።

የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን መንግሥት ጦር የወጋዉን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት አየር ሐይልን በግንባር ቀደምትነት ያዘመቱት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ኒኮላ ሳርኮዚና የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሚሩን በድል ማግስት ትሪፖሊ ነበሩ።ሁለቱ መሪዎች ለአዲሶቹ የሊቢያ መሪዎች እንደነገሩት ድል-በማድረጋቸዉ በርግጥ ኮርተዋል።

«መንገዶቻችሁ በተጓዦች ተሞልቷል።፥ዉሐችሁ እንደልብ ይፈሳል።ሆስፒታሎቻችሁ አገልግሎት እየሰጡ ነዉ።ይሕ በርግጥ ማራኪ ነዉ።እናንተ ይሕን ማድረግ እንድትችሉ ብሪታንያ በመርዳቷ እኮራለሁ። በማድረግ ላይ ያላችሁትን ማራኪ ለዉጥና ዛሬ ያየሁትን በማየቴ ደግሞ ይበልጥ እኮራለሁ።»

የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን መስከረም አስራ-አራት ሁለት ሺሕ አስራ አንድ።ትሪፖሊ።የኔቶ ድብደባ ካሜሩን እንዳሉት ለሊቢያዉያን ማራኪ ለዉጥ ሲያጎናፅፋት የኒያ በሕይወት የተረፉ ግፉዓን ስደተኞች ሕይወትንም በርግጥ ለዉጦቷል።የሜድትራንያን ባሕርን አሻግሮ ገሞሶቹን ኢጣሊያ፥ ሌሎቹን ሞልታ አድርሷል።ለዉጡ ግን በተለይ ሞልታ ለገቡት ሌላ ስቃይ ነበር።

የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት እንደዘገቡት ሊቢያ ዉስጥ ከጦርነቱ በፊት 1.5 ሚሊዮን ያሕል ጥቁር አፍሪቃዉያን ስደተኞች ወይም ሠራተኞች ነበሩ።አምንሲቲ ኢንተርናሽናል፥ ዩይማን ራይትስ ወችና የአፍሪቃ ሕብረት በየፊናቸዉ እንዳስታወቁት በየሐገራቸዉ ኑሮ መሯቸዉ፥ ወይም የየሐገራቸዉ ፖለቲካዊ ሥርዓት አስግቷቸዉ ከሸሹት መሐል የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ መንግሥት ደጋፊዎች ናችሁ ተብለዉ አሁን የሊቢያን የመንግሥትነት ሥልጣን በተቆጣጠሩት ሐይላት የተገደሉ አሉ።

Flash-Galerie Tunesien Libyen Grenze Afrikanische Flüchtlinge

የዳግም ስደተኛዉ ማረፊያ


የተደፈሩ፥ልጆቻቸዉን ተቀምተዉ የተባረሩ አሉ።ቁጥራቸዉን ግን እስካሁን በትክክል የሚያዉቅ የለም።

ከጦርነት-ግድያዉ፥ ከመደፈር-ቅሚያ ዘረፋዉ ሸሽተዉ ሲያመልጡ አድም በምግብ፥ ዉሐ እጦት፥ አለያም በማዕበል ግፊት፥ ወይም በጀልባ መሰናከል ምክንያት ያለቀዉን ስደተኛም በርግጥ ቤቱ ይቁጥረዉ-ቤት ከነበራቸዉ።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ቻድና ኒጄር ጠረፍ ላይ ሠፍረዋል።ቱኒዚያ ብቻ ከአምስት ሺሕ በላይ ስደተኞች ታስተናግዳለች።ይሕ በይፋ የሚታወቀዉ ነዉ።

ሳርኮዚ እንደ ፈረንሳይ ፕሬዝዳት፥ ካሜሩን እንደ ብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር የሚመሩት የአዉሮጳ ሕብረት ቱኒዚያ ከሠፈሩት አፍሪቃዉያን ስደተኞች መካካል አራት መቶዉን ለመቀበል ወስኗል።ሃያ-ሰባቱ የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት ሊቀበሉ የፈቀዱት ስደተኞች ቁጥር አራት መቶ ብቻ መሆኑን በአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት የሰብአዊ መብት ጉዳይ ተጠሪ ባርባራ ሎሽቢሕለር አሳፋሪ ይሉታል።

«ከየካቲት ጀምሮ ሲያመነቱ ነበር።ይሕ በርጥ በጣም የሚያሳዝን ነዉ።ምክንያቱም ባንድ በኩል ሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋል፥ የተቸገሩትን መርዳት፥ መቀበል አለብን ይባላል።በተግባር ግን ምንም የተደረገ ነገር የለም።ቱኒዚያ የሠፈሩት ስደተኞች እጅግ በርካታ መሆናቸዉን እናዉቃለን።አንዲት ደሐ ሐገር፥ በራስዋ ችግር የተያዘች ሐገር ያንያሕል ስደተኛ ልታስተናግድ አትችልም።ስደተኞቹ ያሉበት ሁኔታ በጣም አሰቃቂ በመሆኑ የሞቱ አሉ።እና የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት ይሕን ያሕል ጊዜም ዘግይተዉ አሁን-በአስቸጋሪ ሁኔታ ካሉት ስደተኞች መሐል አራት መቶዉን ብቻ እንቀበላለን ማለታቸዉ በርግጥ አሳፋሪ ነዉ።»

በፕሬዝዳት ኦባማ አገላለፅ የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን አምባገነናዊ ስርዓት ለማስወገድ ተገቢ እርምጃ የወሰደችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ሰብአዊ ርዳታ ከሚሹ ዳግም ስደተኞች አንዱንም ለመቀበል አልፈቀደችም።ከፈቀደችም የተቀበለችዉ ስደተኛ ማንነት አልተዘገበም።

የሜድትራኒያን ደሴቲቱ ትንሽ ሐገር ሞልታ ደግሞ የአዉሮጳ ሕብረት አባል ናት።እዚያ የደረሱ ኢትዮጵያዉያን እንደሚሉት የሞልታ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን ባለሥልጣናትና የሐገሪቱ ፀጥታ አስከባሪዎች የሚያደርሱባቸዉ ግፍ ግን ለንፅፅር ይከብዳል።

የሐገሪቱ የስደተኞች ኮሚሽን ሥለ ስደተኞቹ ይዞታ መልስ እንዲሰጠን ጠይቀን ነበር።የተሰጠን መልስ ለኮሚሽነሩ E-Mail ፅፈን፥ ቀጠሮ ይዘን፥ ያዉም ቀጠሮ ከተሰጠን እንድንጠብቅ ነዉ።በሞልታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) ተጠሪዎችም የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊዉ ከዉጪ እስኪመለሱ ጠብቁ አሉን።የሞልታ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ባልደረባ ግን ለጥያቄያችን መልስ ለመስጠት ፍቃደኛ ነበሩ።ሳራ ማሊያ ይባላሉ።በሞልታ ቀይ መስቀል የስደተኞች የሠብአዊ ጉዳይ ክፍል ባልደረባ ናቸዉ።ሥለ ሥደተኞቹ ይዞታ ጠየቅናቸዉ።
«ለዚሕ ጥያቄ መልስ የለኝም።ምክንያቱም እንደምታዉቀዉ የሞልታ ቀይ መስቀል ማሕበር ገለልተኛ ነዉ።እኔ ልነግር የምችለዉ እዚያ ሥለምንሰጠዉ አገልግሎት ነዉ።ሥለ ሥደተኞቹ ይዞታ ግን ልናገር አልችልም።»ቀይ መስቀል የሚሠራዉን ቀጠሉ፥-

Symbolbild Flüchtlingsstrom / Illegale Einwanderer Abschiebung vs Legalität Italien Gesetze

ስደተኛ-ኢጣሊያ

«የተለያዩ ወይም የተጠፋፉ ቤተሰቦችን ለማገናኘት እንሞክራለን።በተጨማሪም ማቆያ ማዕከሉ ላሉት ሥደተኞች የማሕበራዊና ሥነ-ልቡናዊ አገልግሎት እንሰጣለን።ይሕ ማለት ስደተኞቹ የሚሳተፉበት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን፥ ዉይይቶችን እናደራጃለን።ሥነ-ልቡናዊ አገልግሎት እንሰጣለን።ባሁኑ ሰዓት ቀይ መስቀል በስደተኞች ማቆያ ጣቢያ ሐኪም የለዉም።አንድ ዶክተር ግን አሉ።የሞልታ ቀይ መስቀል ባልደረቦች ስደተኞቹን ይጎበኛሉ።እኔም በሁለት ሳምንት አንዴ የተወሰኑ ጣቢያዎችን እጎበኛለሁ።»

ከስደተኞቹ አንዱ እንዳለዉ ግን የቀይመስቀሏ ተጠሪ የሚናገሩት የሞልታ መንግሥት የስደተኝነት እዉቅና ሰጥቷቸዉ የተሻለ በሚባል ማቆያ ጣቢያ ሥለሚገኙት ነዉ።በቀን ለአንድ ሰዓት ብቻ የፀሐይ ብርሐን እንዲያዉ ተፈቅዶላቸዉ ሥለሚገኙት እስረኞች አይደለም።ግፍ ስቃዩ እስከመቼ ይቀጥላል? እኛ መልስ የለንም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትንም ሆነ የሞልታ የስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣናትን መልስ ካገኘን ግን እናሰማችሗለን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ


Audios and videos on the topic