የሊቢያ ጦርነትና የስደተኞች ፈተና | አፍሪቃ | DW | 18.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሊቢያ ጦርነትና የስደተኞች ፈተና

ሊቢያ ዉስጥ ከሚደርስባቸዉ ግፍ-ስቃይ አምልጠዉ የሜድትራንያን ባሕር ለማቋረጥ ከሚመክሩ ከየ18ቱ ስደተኞች አንዱ ዉሐ ይበለዋል።የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት አፍሪቃዉያን ስደተኞች  ለሚደርስባቸዉ ግፍ-በደል፣ እንግልት ከየሐገሮቻቸዉ መንግስታት እኩል አዉሮጶችም ተጠያቂዎች ናቸዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:21

የሊቢያ ጦርነት፣ የስደተኛዉ አበሳ

               

የሊቢያ ብሔራዊ ስምምነት መንግሥት (GNA)ና የጄኔራል ኸሊፋ ሐፍጣር ታጣቂዎች የገጠሙት ጦርነት በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ስደተኞችን ላደጋ ማጋለጡን የርዳታ ድርጅቶች አስታወቁ።ድንበር የለሽ ሐኪሞች (MSF)ና ሌሎች ርዳታ አቀባይ ድርጅቶች እንደሚሉት ጦርነቱ፣ በየእስር ቤቶቹ የሚገኙ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ስደተኞችን ለበሽታ፣ለረሐብና አልፎ ተርፎ ለተፋላሚዎች ጥቃት አጋልጧል።ድርጅቶቹ እንደሚሉት አንዳድ አካባቢዎችን የሚቆጣጠሩ የተፋላሚ ኃይላት ሚሊሻዎች ደግሞ ስደተኞች እያሰቃዩ፣ እንደ መያዢያም እየተጠቀሙባቸዉ ነዉ።ቶም አሊሰን የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ እንደሚከተለዉ አጠናቅሮታል።
በአብዛኛዉ የአፍሪቃ ስደተኞች ሊቢያ ዉስጥ በየጦር አበጋዙ እስር ቤት መታጎር፣ በእሕል ዉኃ እጦት መጠበስ፣ መደፈር፣ ገንዘብ እንዲከፍሉ መገረፍ፣ በኤሌክትሪክ መቃጠል፣ በስለት መተልተል፣ እንደ ሸቀጥ መሸጥ-መለወጥ-----ብዙ ነዉ።ብዙ ጊዜ ተነግሯልም።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጎርጎሪያኑ አምና (2018) በ13ሺሕ ስደኞች ላይ ባደረገዉ ጥናት የግፍ-በደሉን ድካ ይፋ አድርጓል። መንግሥታት አዉግዘዉታል፣ የመብት ተሟጋቾች መፍትሔ እንዲፈለግ ተማፅነዋል።ዉግዘቱ አፍአዊ፣ ተማፅኖዉ አፍታዊ መሆኑ እንጂ ዚቁ።የስደተኞቹ ስቃይ፣ የአዛኞች ጩኸት፣ የመንግሥታት ከንቱ ዉግዘት ዑደት መቀጠሉ እንዳስተዛዘበ፣ ያቺ የሳርኮዚ፣ ካሜሩን፣ኦባማ፣ ቃዛፊ እብሪት ከትቢያ የቀየጣት ሐገር የሌላ ዕልቂት፣ስቃይ፣ ሰቆቃ መናኸሪያ መሆንዋ ነዉ-ጉዱን የዘለቀዉ ጉድ።በተለይ ለስደተኞች።
ድንበር የለሽ ሐኪሞች (MSF-በፈረንሳይኛ ምሕፃሩ) እንደሚለዉ «የብሔራዊ ስምምነት መንግስት» የሚባለዉ ስብስብና የጄኔራል ሐፍጣር ሚሊሺያዎች ግራ-ቀኝ በሚዋጉበት ትሪፖሊ አጠገብ ብቻ፤ በሚታወቁ ጣቢያዎች ብቻ፣ ከ3ሺሕ በላይ ስደተኞች ታጉረዋል።
የየጦር አበጋዙ በየመጋዘኑ ያጎረዉ ስደተኛን «በሺ የሚቆጠር» ከሚል ግምት ባለፍ ብዛቱን፣የሚደርስበትን ግፍና መከራ የሚያዉቀዉ

አሰቃዩና-ተሰቃዩ ብቻ ናቸዉ። ባለፉት ሳምንታት በተደረገዉ ጦርነት ስደተኞቹን ይረዱ የነበሩ 3 የሕክምና ባለሙያዎች ተገድለዋል።የጦርነቱ ዳፋ ለርዳታ ሠራተኞች በመትረፉ ምክንያት ለወትሮዉ አነሰም-በዛ ስደተኞቹን ይረዱ የነበሩ ሠራተኞች ወደየማጎሪያ ጣቢያዎቹ መድረስ አልቻሉም።
«ከምንሰራባቸዉ የማጎሪያ ጣቢያዎች አንዱ ቀስር ቢን ጋሺር አካባቢ ያለዉ፣ ዉጊያዉ እሚደረግበት አጠገብ ሥለሚገኝ እዚያ ወዳሉ ስደተኞች መቅረብ አልቻልንም።»
የድንበር የለሽ ሐኪሞች (MSF) አስተባባሪ ክራይዥ ኬንሲ ናቸዉ።

አንዳዶቹ እስር ቤቶች ሳንባ ነቀርሳና እከክ መሠራጨቱ ሲዘገብ፤ ወትሮም በቅጡ የማይመገቡት እስረኞች አሁን ደግሞ በእሕል ዉኃ እጦት እየተሰቃዩ ነዉ።ሊቢያ ዉስጥ ከሚደርስባቸዉ ግፍ-ስቃይ አምልጠዉ የሜድትራንያን ባሕር ለማቋረጥ ከሚመክሩ ከየ18ቱ ስደተኞች አንዱ ዉሐ ይበለዋል።የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት አፍሪቃዉያን ስደተኞች  ለሚደርስባቸዉ ግፍ-በደል፣ እንግልት ከየሐገሮቻቸዉ መንግስታት እኩል አዉሮጶችም ተጠያቂዎች ናቸዉ።
የአዉሮጳ መንግሥታት የቀኝ አክራሪዎችን መጠናከር ለማስወገድ ስደተኞችን እንደ ጦስ ዶሮ «ጭዳ» እያደረጓቸዉ ነዉ።የአዉሮጳ ሕብረት በቅርቡ ያፀደቀዉ መርሕ ስደተኞቹንና ስድተኞቹን ከአደጋ የሚያተርፉ ድርጅቶችን ሥለሚወነጅል ባሕሩን ሲያቋርጡ የተያዙ ስደተኞችን ግፍ መከራ ወደ ቆጠሩባት ሊቢያ ይመልሷቸዋል።የፖለቲካ «ጭዳ» ይሉታል የድበር የለሽ ሐኪሞች አስተባባሪ ኬንሲ 
«ባለፉት ሰባት ወራት ዉስጥ ብቻ ሶስት ትላልቅ ዉጊያዎች የተደረጉባት ሊቢያ ለስደተኞች አስተማማኝ መቆያ ልትሆን ጨርሶ አስትችልም።ተቀባይነት የለዉም።እነዚሕ ሰዎች ለአዉሮጳ መንግሥታት የፖለቲካ ጭዳ መሆን የለባቸዉም።»
ስደተኞቹ ለሊቢያ የጦር አበጋዞች የገንዘብ

ምንጭ ናቸዉ።ለየታጣቂዎቹ የወሲብ ማርኪያ፣ ላንዳዶቹ ደግሞ አገልጋይ ናቸዉ።አሁን ደግሞ የየጦር ቡድናቱ መሪዎች ብዙ ስደተኞች ወደ አዉሮጳ እንዳይጓዙ ከያዝን ከአዉሮጳ መንግስታት ድጋፍ እናገኛለን የሚል ስሜት አድሮባቸዋል።ሌላዉ ቀርቶ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመሠረተዉ ስብስብ መሪ ፈይዝ ሲራጅ ሳይቀሩ መንግስታቸዉ ከጄኔራል ሐፍጣር ጋር የገጠመዉ ጦርነት ከተባባሰ 800 ሺሕ የአፍሪቃ ስደተኞች አዉሮጳን ያጥለቀልቃሉ በማለት ዝተዋል።
ዛቻዉ፣ የአዉሮጶችን ድጋፍ ለማግኘት ዓለም አቀፍ እዉቅና ያለዉ መንግስት እንኳ ስደተኞችን መያዣ ማድረጉን ያረጋግጣል።የመካከለኛዉ ምሥራቅ የሠላምና የግጭት ጉዳይ አጥኚ ፕሮፌሰር ጄኮብ መንዲይ «የቀዉሶች መቃወስ» ይሉታል።
                                         
«በጣም ግራ የሚያጋባ የቀዉሶች መቃወስ ነዉ።አዉሮጳ ዉስጥ የፖለቲካ ቀዉስ አለ።ቀዉሱ በሊቢያ ላይ ተጫነ።የሊቢያዉ ቀዉስ በፋንታዉ ስደተኞቹ ላይ ወደቀ።»
አዉሮጶች በስደተኞች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለሊቢያ ተፋላሚ ኃይላት የሚሰጡት ድጋፍም ሊቢያን ለዉድመት፣ዜጎችዋን ለጥፋት፣ ስደተኞቹን ለሞት እየዳረገ ነዉ።ፈረንሳይ ጄኔራል ሐፍጣርን ትደግፋለች።ኢጣሊያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰየመዉን መንግስት ትደግፋለች።ጀርመን ያደፈጠች ትመስላለች።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች