የሊቢያ ድብደባ ዳራናዉና ምክንያቱ | ዓለም | DW | 21.03.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሊቢያ ድብደባ ዳራናዉና ምክንያቱ

ሕዝባዊዉ አመፅ ቤንጋዚ ላይ ጠንከር፣ ደመቅ፣ ትሪፖሊ ጭልጭል ከማለቱ ቅፅበት ወደ ነፍጥ ዉጊያ የቀየረዉ አዚም የአለም ሐያላንን ይትብሐልም ለዉጦ ፓሪስን አስቀደመ።ለንደኖችን ከፓሪሶች ጎን አሰለፈ።

default


እንደ ቱኒዚያ፣ እንደ ግብፅ ጎረቤቶቿ የሕዝቧን ሰላማዊ አብዮት፤ የአብዮተኛዉን ድፍረት፣ ፅናት በየአደባባዮችዋ ላፍታ አስመሰከረችና እንደ ዳርፉር ሶማሌ በገዢ-አማፂዎቿ ዉጊያ ትነድ ገባች።ሊቢያ።የሕዝባዊዉን አብዮት ሰላማዊ ይዘት ሒደት ባፍታ አስቀይራ የርስ በርሱን ጦርነት አለችዉ አላትና እንደ ኢራቅ-አፍቃኒሲታን በምዕራባዉያን ጦር ድብደባ ጥፋት-ዉድመቷ ፀና።

ታላቋ ሶሻሊስታዊ ሕዝባዊት ሊቢያ አረብ ጁምሕሪያ ሰሞናዊ እዉነት መነሻችን፥ ዳራዉ ማጣቀሻ፥ ድብደባዉ ፈረንሳይን አስቀድሞ፥ ብሪታንያን አሳድሞ፥ ዩናይትድ ስቴትስን ማስከተሉ ጥያቄያችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።
የዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪዎች መመታት፣ አለም አቀፉ ፀረ-ሽብር ዘመቻ መታወጅ፥ የኢራቅ መወረርም ለኮሎኔል ሙአመር ቃዛፊ «ሳይደግስ አይጣላም» አይነት ነበር።የቃዛፊዋን የታላቋ ሶሻሊስታዊ ሕዝባዊት ሊቢያ አረብ ጁምሕሪያን ነዳጅ ዘይት ለመሸመት ወይም በምትኩ ሸቀጥ-እዉቀታቸዉን ለመሸጥ ለሚፈልጉት ሐገራት በጣሙን ለምዕራባዉኑ ጥሩ አጋጣሚ ነበር።

አጋጣሚዉ የዘመናት ጠበኞችን ለወዳጅነት አፈላልጎ ቃዛፊ በከሰከሱት ገንዘብ፣ በዘረገፉት ሚስጥር፣ ባፈራረሱት የኑክሌር ተቋም የምዕራቦችን ልብ ሲገዙ የተጣለባቸዉ ማዕቀብ ተነሳ። በአሸባሪነት ወንጀል የጎደፈ ስም፣ ክብራቸዉን «ተለቃልቁት»።የፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬጋኑ «የመካከለኛዉ ምሥራቅ እብድ ዉሻ»፥ የጠቅላይ ሚንስትር ማርጋሬት ታቸሩ «ክልፍልፍ አሸባሪ» «ያ ቀርቶ ሌላ ዘፈን መጥቶ» አይነት ይነገር፥ ይመሰከርላቸዉ ያዘ።

«የሊቢያ መሪ ኮሎኔል ሙዓመር አል-ቃዳፊ በሐገራቸዉ ያለዉን የጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያ መርሐ ግብርን እንደሚያፈራርሱ በይፋ አረጋግጠዋል።የሊቢያ ባለሥልጣናት የሐገራቸዉን የኑክሌር፥ የኬሚካዊና ባዮሎጂያዊ የጦር መሳሪያ መርሐ ግብር እና እንቅስቃሴን የሚመለከቱ ሰነዶችን ለአሜሪካና ለብሪታንያ የስለላ ባለሙያዎች አስረክበዋል።ሊቢያ በሐገራት መካከል አስተማማኝና የተከበረ ሥፍራ ማግኘት ትችላለች።በጊዜ ሒደትም ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የተሻለ ግንኙነት ይኖራታል።»

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ጆርጅ ዳብሊዉ ቡሽ ታሕሳስ ሁለት ሺሕ ሰወስት (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ)

የያኔዉ የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌርም ከለንደን ቀጠሉ።«ይሕ የኮሎኔል ቃዳፊ ዉሳኔ ታሪካዊ፥ የደፋሮች ዉሳኔ ነዉ።እኔ አደንቀዋለሁ።አካባቢዉንና ዓለምን ይበልጥ ሰላማዊ ያደርገዋል።የጦር መሳሪያን በማሰወገዱ ሒደት የሚገጥሙ ችግሮችን በዉይይትና በመቀራረብ ማቃለል እንደሚቻልም እማኝ ነዉ።»

ቃዛፊ ሊያጠፏቸዉ ከደበደቧቸዉ፣ ከቀጧቸዉ፣ ከወንጀሏቸዉ

Flash-Galerie Libyen USA USS Stout

ሐይለኞች ጋር ታርቀዉ ኮንዳሊሳ ራይስን ከዋሽንግተን፣ ቶኒ ብሌርን ከለንደን፣ ጌርሐርድ ሽሩደርን ከበርሊን፣ ሲልቪዮ ቤርሎስኮኒን ከሮም ትሪፖሊ ድንኳናቸዉ ድረስ ማመላለሳቸዉ ለሳቸዉ ታላቅ ክብር ለጎብኚዎቻቸዉ የአዲስ ጥቅም ጅምር ነበር።

የያኔዋ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ወይዘሪት ኮንደሊሳ ራይስ በሁለት ሺሕ ስምንት ትሪፖሊን ሲጎበኙ ግን ያኔም፥ ከዚያ በፊትና በሕዋላም እዉነት የነበረ፥ የሆነና የሚሆን አንድ ቁም ነገር አሉ።

«ዩናይትድ ስቴትስ በተደጋጋሚ እንዳስታወቀችዉ ቋሚ ጠላት የላትም።ሊቢያ ጠቃሚ ሥልት መምረጧን አልጠራጠርም።ይሕን ግንኙነት ለማጠናከር መሥራታችንን እንቀጥላለን።ጥሩ ጊዜ ነዉ የተጀመረዉ።ምክንያቱም ብዙ የሚሠሩ ሥራዎች አሉና።እዚሕ መግሬብ ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ።አፍሪቃ ዉስጥ ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ።ሥለዚሕ በሊቢያና በዩናይትድ ስቴትስ መካካል ያለዉ ግንኙነት እንዳዲስ እንዲዳብር ጥሩ ጊዜ ነዉ።»

ዩናይትድ ስቴትስ፥ የምዕራብ ወዳጆችዋም ዘላቂ ጥቅም እንጂ ቋሚ ጠላት-ወዳጅም የላቸዉም። እንደሌላቸዉም ከራስስ በፊትም በሕዋላም ብዙዎች ሸሸገዉት አያዉቁም።ራይስ ምናልባት «የሚሠሩ ሥራዎች» ካላቸዉ በዚያዉ ሰሞን በሊቢያ ለተሾሙት አምባሳደራቸዉ የሰጧቸዉ የቤት ሥራ አንዱ ሊሆን-ሊሆን ላይሆንምም ይችላል።ብቻ በሊቢያ የተሾሙት የዩናይድ ስቴትሱ አምባሳደር ጄን ክሬትዝ የዲፕሎማሲዉ ወግ፥ የሐገራቸዉ መርሕ፥ የአለቆቻቸዉ ትዕዛዝ ግድ ብሏቸዉ ሳይሆን አይቀርም ከቃዛፊ ሹሞች መሐል ቃዛፊን ሊቃወሙ ይችላሉ ወይም አሜሪካን ይደግፋሉ የሚባሉትን ለማግኘት በዲፕሎማሲዉ ሸፋን ያድኑ ያዙ።

ከዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ያፈተለከ ሚስጥር እንዳመለከተዉ አምባሳደር ክሬትዝ ካነጋገሯቸዉ ምሁራን፥ዲፕሎማት ባለሥልጣናት ሁሉ እንደ ዶክተር መሐመድ ጅብሪል የአሜሪካዉን አምባሳደር ልብ የማረከ የለም።ሰዉዬዉ ፒተርስበርግ-ፔንስሎቬንያ ዩናይትድ ስቴትስ ነዉ የተማሩት።ብዙ መፅሐፍ ያሰተሙ፥ የሚሰማቸዉን ፊለፊት የሚናገሩም ናቸዉ።

እስከ 2009 ድረስ የሊቢያ ብሔራዊ ፕላን ድርጅት ሐላፊ ነበሩ። በ2009 የሐገሪቱ የምጣኔ ሐብት እና የልማት ቦርድ ሐላፊ ሆነዉ እንደተሾሙ የአሜሪካዉ አምባሳደር አነጋገሯቸዉ።እና ዘገቡ አምባሳደሩ ለአለቆቻቸዉ «ዩናይትድ ስቴትስን የሚደግፉ፥ ብልሕና አመራር የሚችሉ ናቸዉ።» አይነት ብለዉ።ዶክተር ጂብሪል ዛሬ ሰላሳ አንድ አባላትን የሚያስተናብረዉ የሊቢያ ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰኘዉ የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ተቃዋሚዎች ስብስብ የዉጪ ጉዳይ ሐላፊ ናቸዉ።

ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ከምዕራቦች ጋር አዲስ ለጀመሩት ወዳጅነት ክብር ትሪፖሊ ድረስ ሔደዉ ላረጋገጡላቸዉ ሐገራት ባለሥልጣናት በሁለት ሺ ሰባት አፀፋ ጉብኝት ሲያስቡ ያስቀደሙት ወይም በቅድሚያ ግብዣ ፍቃዱን ያገኙት ፈረንሳይንና ከፈረሳዩ መሪ ከኒካላይ ሳርኮዚ ነበር።ለታላቁ አብዮታዊ መሪ ታላቅ አቀባበል ያደረጉላቸዉ ፕሬዝዳት ሳርኮዚ ጉብኝቱን ያልፈቀዱ ወገኖቻቸዉን ጥያቄ፥ ተቃዉሞ ደፍልቀዉ የቃዛፊ ድንኳን ፓሪስ መሐል እንዲተከል ፈቅደዉም ነበር።

ቃዛፊ ከሃያ-አራት አመታት በሕዋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ምዕራባዊ ሐገር ባደረጉት በዚያ ጉብኝት ከሳርኮዚ ጋር ያፀደቁት የንግድ ሥምምነትም ቀላል የሚባል አልነበረም።ፈረንሳይ ሃያ አንድ ኤር ባስ አዉሮፕላን ለመሸጥና ለሊቢያ ሠላማዊ የሚባል የኑክሌር ተቋም ለመገንባት ተስማማች።አስር ቢሊዮን ዩሮ።

ዶክተር ጅብሪሊ በሁለት ሺሕ ዘጠኝ የመላ የአሜሪካ አስተዳደርን ባይሆን ባይሆን የአሜሪካዉን አምባሳደር ቀልብ መሳባቸዉ ርግጥ ነዉ። ምናልባትም የአሜሪካን ድጋፍ አግኝተዉም ይሆናል። የሊቢያ ሕዝባዊ አመፅ የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን የአርባ ሁለት ዘመን ሥልጣን መገዝገዝ ሲጀምር እንደ ቀድሞ መሪያቸዉ ቀድመዉ የሄዱት ግን ፓሪስ፥ የጋበዟቸዉ፥ ሕጋዊ እዉቅና ለሌለዉ ምክር ቤት እዉቅና የሰጧቸዉም ሳርኮዚ ናቸዉ።ከሁለት ሳምንት በፊት።

የሊቢያዉን ሕዝባዊ አመፅ ወደ እርስ በርስ ጦርነት፥ የርስ በርስ ጦርነቱን ወደ አለም አቀፍ ድብደባ ለመቀየርም ሳርኮዚን የቀደመ አለመኖሩ ነዉ ዚቁ።
«ከዚሕ ጊዜ ጀምሮ የጦር አዉሮፕላኖቻችን አማፂያኑ በሚቆጣጠሩት በቤንጋዚ አካባቢ ያለዉን (የጋዛፊ) ሐይል እየደበደቡ ነዉ።ሌሎች የፈረንሳይ አዉሮፕላኖች ሰላማዊን ሰዉ ለመከላከል በተጠንቀቅ ቆመዋል።»

አርብ።ከሁለተኛዉ የአለም ጦርነት በሕዋላ ወደ ምዕራብ ለሚያየዉ ዋሽንግተን ወደ ምሥራቅ ለሚመለከተዉ ደግሞ ሞስኮ ነበር የአለም መዘወሪያ ምሕዋር።ከኮሪያ ልሳነ ምድር፥ እስከ ቬትናም በተደረጉት ትላልቅ ጦርነቶችም ዋሽንግተን-ሞስኮዎች በተቃራኒ አቅጣጫ ሲቀድሙ፥ ለንደን፥ ፓሪስ፥ በርሊኖች ከምዕራብ፥ ቤጂንግ፥ ዎርሶ፥ ሐቫናዎች ሲከተሉ ነዉ-አለም የለመደች-የምታዉቀዉ።

ከቀዝቃዛዉ ጦርነት በሕዋላ ኢራቅ ሁለቴ፥ ይጎዝላቪና አፍቃኒስታን አንዳዴ በተደረገና በሚደረገዉ የሕብረ-ብሔራዊ ጦርነት ቀዳሚ አስተባባሪዋ ዩናይትድ ስቴትስ፥ ግንባር ቀደም ተከታይዋ ብሪታንያ፥ አሰላሾቹ ፈረንሳይና ብጤዎቻቸዉ ነበሩ።

የሊቢያ ሕዝብ የአርባ-ሁለት ዘመን ገዢዉን ከሥልጣን ለማስወገድ አደባባይ የወጣዉ ከሞሮኮ-እስከ ዮሮዳኖስ፣ ከባሕሬን እስከ የመን እንዳሉ ብጤዎቹ ሁሉ ከቱኒዚያ ግብፆች ብልሐት ድፍረት ተምሮ፣ በቱኒዚያ-ግብፆች ፅናት ተጃግኖ እንደ ቱኒዚያ ግብፅ ሕዝብ በሰላማዊ አመፅ የቱኒዝ ካይሮን ድል ትሪፖሊ ሊደግም አልሞ ነበር።ሕዝባዊዉ አመፅ ቤንጋዚ ላይ ጠንከር፣ ደመቅ፣ ትሪፖሊ ጭልጭል ከማለቱ ቅፅበት ወደ ነፍጥ ዉጊያ የቀየረዉ አዚም የአለም ሐያላንን ይትብሐልም ለዉጦ ፓሪስን አስቀደመ።ለንደኖችን ከፓሪሶች ጎን አሰለፈ።

«የብሪታንያ ሐይላት ሊቢያ ዘምተዋል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የሊቢያን ሕዝብ ለማዳን ያለዉን ፍላጎት ለማስከበር የተሰባሰበዉ አለም አቀፉ ሐይል አካል ናቸዉ።»

የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን።ቅዳሜ።ዋሽንግተኖችን አስከተለ።የዚያኑ እለት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የፓሪስ ለንደኖችን ጅምር ማፅደቃቸዉን አረጋገጡ።

«የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሐይል የሊቢያን ሰላማዊ ሕዝብ ለማዳን በሚደረገዉ አለም አቀፍ ጥረት በሊቢያ ላይ የተወሰነ እርምጃ እንዲወስድ አዝዣለሁ።እርምጃዉ አሁን ተጀምሯል።በዚሕ ጥረት ዩናትስ ስቴትስ የምትወስደዉ እርምጃ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የሊቢያን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል ያሰለፈዉን ዉሳኔ ቁጥር 1973ን ገቢራዊ ለማድረግ የተሰየመዉ ሰፊ ጥምረት አካል ነዉ።»

በፈረንሳይና በብሪታንያ ጉትጎታ የረቀቀ-የፀደቀዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዉሳኔ ቁጥር 1973 NO Flay ዞን ነዉ-ስያሜዉ።ከበረራ የታገደ፥ ወይም የታቀበ ቀጣና-እንደማለት።የአረብ ሊግ ሹማምንት እንዳሉት ዉሳኔዉን ሲደግፉ ዉሳኔዉ እገዳዉን የጣሱ የቃዛፊ በራሪዎች እንዲመቱ ወይም በራሪዎቹን የሚመቱ ሐይላትን የሚመቱ ፀረ-በራሪ መሳሪያዎችን እንዲያጠፉ ነዉ ብለዉ ነበር።

የመጀሪያዎቹ የፈረንሳይ አዉሮፕላኖች የደበደቡት ግን ሳርኮዚ እንደመሰከሩት ቤንቃዚ አካባቢ የመሸገዉን የሊቢያ መንግሥት ታንከኛ ጦርን ነዉ።አከታትለዉ የቃዛፊ ቅጥር ግቢን አጋዩት። በድብደባዉ የሊቢያ ጤና ጥበቃ እንዳለዉ እስከ ትናንት ድረስ ብቻ ስልሳ-አራት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።የአረብ ሊግ ዋና ፀሐፊ አምር ሙሳ አልገባቸዉም።ወይም አረብ እንዳይጠላቸዉ ያልገባቸዉ መስለዋል።
«የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ሰላማዊ ሰዎችን ከጥቃት ለመከላከል የበረራ እቅድ ቀጣና እንዲከልል ነዉ የጠየቅነዉ።ሰላማዊ ሰዎች ሳይጎዱ እገዳዉ እንዲከበር ነዉ የጠየቅ ነዉ።ዛሬ የተፈፀመዉ ወታደራዊ እርምጃ ግን በርግጥ ምንም አይነት ዘገባ የለኝም።»

Libyen Gaddafi Fernsehinterview 17.03.2011

ድብደባዉ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ዳግማዊ ሳዳም ሁሴይን ያደርግ ይሆናል። የሊቢያ ሕዝባዊ አመፅ ግን ከእንግዲሕ የቱኒዚያና የግብፅ ብጤዎቹን ታሪክ ክብርን መጋራቱ አጠራጣሪ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ