የሊቢያ ዓመጽና የዘይት ዋጋ መናር | ኤኮኖሚ | DW | 28.02.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የሊቢያ ዓመጽና የዘይት ዋጋ መናር

ሰሜን አፍሪቃንና መካከለኛ ምሥራቅን ያናወጸው የሕዝብ እንቅስቃሴ በወቅቱ በተለይም በሊቢያ የአገዛዙን አስከፊ ገጽታ በሚገባ ሲያጋልጥ ማለቂያውን ለመገመት ደግሞ አዳጋች ሆኖ ቀጥሏል።

default

ዓመጹ በምሥራቅ በመንግሥት ተቃዋሚዎች ቁጥጥር ስር ከዋለችው ከቤንጋዚ ወደ ዋና ከተማይቱ ወደ ትሪፖሊ ሲዛመት አገሪቱን ለ 42  ዓመታት ሲገዙ የኖሩት ኮሎኔል ሞአመር ጋዳፊ ከወደቅኩ አይቀር አጥፍቼ ልጥፋ ያሉ ነው የሚመስለው። ለመሆኑ በነዳጅ ዘይት ሃብት የታደለችው አገር የፖለቲካ ቀውስ ሊያስከትል የሚችለው የኤኮኖሚ ችግር ምን ያህል ሊሆን ይችላል? ይህ በተለይ ከሊቢያ ነዳጅ ዘይት የሚገዙትንና በአገሪቱ የኤኮኖሚ ጥቅም ያላቸውን ምዕራባውያን መንግሥታትም ማሳሰቡ አልቀረም።

በሊቢያ ከለየለት ዓመጽ ውስጥ መውደቅ በዚህ በአውሮፓ ታላቅ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ቀውስ ስጋት ነው የተፈጠረው። ቤንጋዚ በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ስር ከዋለችና በዋና ከተማይቱ በትሪፖሊም የመንግሥት ሕንጻዎች መቀጣጠል ከያዙ ወዲህ ጀርመንና የአውሮፓ ሕብረት በአገሪቱ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሙያዎች ለቀው እንዲወጡ ሲያሳስቡ አውሮፕላኖችንም እያቀረቡ ነው። በኤኮኖሚው ረገድ እርግጥ ለጊዜው ገና እጥረት አልተፈጠረም። ይሁን አንጂ ስጋት መከተሉ ግን ከወዲሁ የነዳጅ ዘይት ዋጋ እንዲጨምር እያደረገ ነው።

ዌስት-ቴክሣስ-ኢንተርሚዲየት፤ በአሕጽሮት WTI በመባል የሚታወቀው የአሜሪካ የነዳጅ ዘይት ዓይነት ዋጋ ከትናንት በስቲያ በበርሚል አንድ ዶላር ከሃምሣ በመጨመር ወደ 93 ዶላር ከፍ ሲል የአውሮፓው የሰሜን ባሕር ዘይት ብሬንት ደግሞ በሶሥት ዶላር ወደ 105 ዶላር ተተኩሷል። በሁለቱ ዓይነቶች መካከል ያለው የ 12 ዶላር የዋጋ ልዩነት የኋለኛው ብሬንት ገና ብዙ ጭማሪ ስለሚደረግ እየሰፋ እንደሚሄድ ነው ከንግዱ ዘርፍ የሚነገረው። በወቅቱ አሜሪካ ውስጥ የነዳጅ ክምችቱ የተሟላ ሲሆን በአውሮፓ ብሬንት ለቀውሱ አካባቢ የቀረበው በመሆኑ ችግሩ ይበልጡን ሳይሰማው የቀረ አይመስልም። ለማንኛውም ሊቢያ የገበዮቹን ትኩረት እየሳበች መሆኗ በግልጽ የሚታይ ነገር ነው።

“የነዳጅ ዘይቱ ገበያ በሊቢያ ላይ አተኩሯል። ምክንያቱም ሊቢያ በዓለምአቀፍ ደረጃ ከሚመረተው ዘይት ሁለት በመቶውን የምታወጣው አገር ናት። ይህ ለምሳሌ ከግብጽ ሲነጻጸር እጥፍ መሆኑ ነው። አልጄሪያን ጨምረን ስለ ሰሜን አፍሪቃ ካወራን ደግሞ ምርቱ በጥቅሉ አምሥት በመቶ ይደርሳል። ይህ ታዲያ የማይናቅ ድርሻ ሲሆን ለዚህም ነው የአውሮፓው የዘይት ዓይነት ብሬንት ዋጋ እንዲያድግ የሚደረገው”

ይህን የሚሉት የዴካ ባንክ የዘይት ንግድ አዋቂ ዶራ ቦርቤሊይ ናቸው። ባለሙያዋ እንዳሉት በሊቢያው ዓመጽ ሳቢያ በአገሪቱ የዘይት ማውጣቱ ተግባር ከአሁኑ መሰናከሉም አልቀረም። ቢ.ፒ. ኩባንያ ለምሳሌ በምዕራባዊው ሊቢያ ነዳጅ ዘይትና ጋዝ ለማውጣት በሚያካሂደው የሙከራ ቁፋሮ እንደማይቀጥል አስታውቋል። የአውስትሪያው የነዳጅና የጋዝ ኩባንያ OMV-ም በሊቢያ የሚገኝ ውክልናውን ባልደረቦች በመቀነስ ላይ ነው።

የጀርመንንና የሊቢያን የንግድ ግንኙነት ከተመለከትን አገሪቱ ከትሪፖሊ የምትገዛው  ከሞላ-ጎደል ነዳጅ ዘይት ብቻ ነው ለማለት ይቻላል። በዕውነትም እ.ጎ.አ. በ 2009 ዓ.ም. ጀርመን ከሊቢያ ካስገባችው ምርት 99 በመቶውን ድርሻ የያዘው ዘይት ነበር። ሊቢያ ለገበያ የምታቀርባቸው የተቀሩት ምርቶች ስንዴ፣ የወይራ ፍሬ፣ ቲማቲም፣ ጨው ወዘተ. እዚህ ጨርሶ ተፈላጊነት የላቸውም። ለነገሩ ለሊቢያ በመጠናቸውም የዘይትን ያህል በሰፊው የሚመረቱ አይደሉም። ነዳጅ ዘይትን በተመለከተ ግን ሊቢያ ለጀርመን ሶሥተኛዋ ታላቅ አቅራቢ ናት።

በአንጻሩ ጀርመን ወደ ሊቢያ የምትልከው ምርት በመጠኑ ያን ያህል አይደለም። ሆኖም ግን በ 2008 እና 2009 በምርት መኪናዎች ረገድ የጀርመን የውጭ ንግድ ጠቃሚ ዕድገት ታይቶበታል። ለግንዛቤ ይህል አቅርቦቱ በእጥፍ ነበር የጨመረው። እርግጥ የጀርመን የምርት መኪና አምራች ኩባንያዎች ማሕበር የአፍሪቃ ዘርፍ ሃላፊ ፍሪድሪሽ ቫግነር እንደሚያስረዱት ይህን መሰሉ እመርታ በፕሮዤዎች ንግድ ረገድ ያልተለመደ ነገር አይደለም።

“እርግጥ ነው፤ የሊቢያ ንግዳችን ለኛ በጣሙን መንግሥት በሚሰጠው ኮንትራት ላይ የተመሠረተ ነው። የሊቢያ ኤኮኖሚ መንግሥታዊ ኤኮኖሚ ሲሆን በመንግሥት የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት ውሣኔዎች ላይም ጥገኛ ይሆናል። እና ፕሮዤዎቹም እንደዚሁ ታላላቅ ናቸው”

ፍሪድሪሽ ቫግነር አያይዘው እንደሚሉት የሊቢያ መንግሥት የኤኮኖሚ ፖሊሲ ዓላማም ሲበዛ ግልጽ ነው።

“የመንግሥቱን የመዋዕለ-ነዋይ ውሣኔዎች ለመረዳት ብዙም አያዳግትም። አገሪቱ ዘመናዊ ዕድገት ማድረግ አለባት። እናም የምታቅደው ነዳጅ ዘይቷን በራሷ ለማጣራትና ያለቀ ምርት ለገበያ ለማቅረብ ነው። አንዳንድ የመንግሥቱ ውሣኔዎች በአንጻሩ ሊረዷቸው ያዳግታሉ። ሚስጥራዊ ናቸው። ለምሳሌ አውሮፓውያን ለተወሰነ ጊዜ ቪዛ እንዳያገኙ መደረጋቸው!”

ይህ ከሁለት ዓመታት በፊት የጋዳፊ ልጅ ሃኒባል ጀኔቫ ላይ ለሁለት ቀናት ተይዞ ከቆየ በኋላ የታየ ነገር ነበር። የኢራቅ ልምድ እንደሚያሳየው ይህን መሰሉ ሁኔታ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴን በጣሙን የሚያዳክም ነገር ነው። እርግጥ አዲስ መንግሥት ሥልጣን ሲይዝ ንግዱ በአብዛኛው መልሶ ሊቀጥል ይችላል። ማለት አስተማማኝ ውሣኔን የሚያስተላልፍ አመራር ሲኖር! ይህ ካልሆነ ግን ሂደቱ በተለይም መለስተኛ ኩባንያዎችን ነው እስትንፋስ የሚያሳጣው። 

Flash-Galerie G20 Treffen Paris 2011

የቡድን-ሃያ ጉባዔ በፓሪስ

ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ፓሪስ ላይ የተካሄደ የቡድን-ሃያ መንግሥታት የገንዘብ ሚኒስትሮች ጉባዔ ወደፊት የኤኮኖሚ ቀውሶችን ቀድሞ ለመለየትና ለመቋቋም የሚረዳ መስፈርት ለማስቀመጥ ብዙ ከተከራከረ በኋላ ከአንድ ስምምነት ለመድረስ ችሏል። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉና የተፋጠረ ዕርምጃ ያደረጉ ሃያ ሃገራትን ያሰባሰበው ቡድን የተስማማቸው አምሥት አመልካች ነጥቦች በዓለም ኤኮኖሚ ላይ አደገኛ የሚዛን ዝቤት ሲከሰት በጊዜውና በትክክል ለመለየት የሚረዱ ይሆናሉ ተብሎ ታምኖባቸዋል።

በስምምነቱ መሠረት ወደፊት የምንዛሪ ልውውጥ መስፈርት፣ መንግሥታዊና የግል ዘርፍ ዕዳዎች፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችትና የየሃገራቱ የንግድ የገቢ-ወጪ ይዞታ የሚመረመሩ ይሆናሉ። በተለይ በመጨረሻው መስፈርት ላይ ቻይና ብዙ ተቃውሞ ማሰማቷ አልቀረም። ሆኖም የፊናንስ ሚኒስትሮቹ በጉዳዩ አስታራቂ መፍትሄ ለማግኘት ችለዋል። በዚህም የየሃገራቱ ገቢና ወጪ ሚዛን ወደፊት የሚለካ ቢሆንም መንግሥታቱ በምንዛሪ ክምችታቸው በወለድ የሚያስገቡት ገቢ ግን አይፈተሽም። በተለይ ቻይና በዚህ ጉዳይ የጠነከረችው በዓለም ላይ ታላቁን የውጭ ምንዛሪ ክምችት የያዘች በመሆኗ ነው። ይሄውም ሶሥት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይደርሳል።

እንደ ዕውነቱ ከሆነ ተገኘ በተባለው አስታራቂ ስምምነት አንዱ ተጠቃሚ ሌላው ደግሞ ተጎጂ መሆኑ አልቀረም። ጀርመን ለምሳሌ በዓለም ኤኮኖሚ ሚዛን ላይ በሚደረግ ፍተሻ ተጎጂ እንዳትሆን ልትፈራ ትችላለች። ቻይናና ጀርመን በውጭ ንግድ በዓለም ላይ ቀደምቱ ናቸው። ከዓለምአቀፉ የምርትና የአገልግሎት ንግድ በጣሙን ይጠቀማሉ ማለት ነው። እርግጥ ስኬታቸው ከሌሎች አገሮች ይዞታ ጋርም ትስስር አለው። ሁለቱ አገሮች በንግድና በአገልግሎት ረገድ አትራፊ ሲሆኑ ሌሎች በኪሣራ የተጠመዱም አልጠፉም። እናም ጀር,መን ለምሳሌ በውጭ ንግድ የምታገኘውን ትርፍ ቀንሺ ተብላ እንዳትጠየቅ ትሰጋለች።

የሆነው ሆኖ የቡድን-ሃያ ጉባዔ ውጤት የዓመቱን ርዕስነት ለያዘችው ለአስተናጋጇ አገር ለፈረንሣይ መለስተኛ ዕርምጃ ሆኖ ነው የሚታየው። ምክንያቱም በዓለም ኤኮኖሚ ላይ የተሳሳተ ሂደት መኖሩን መለየቱ አንድ ነገር ሲሆን ዋናው ነገር ግን ይህንኑ ለመታገል መቻሉ ላይ ነው። ፕሬዚደንት ኒኮላይ ሣርኮዚይ መንግሥታት ለብሄራዊ ጥቅም ቅድሚያ ከመስጠት እንዲቆጠቡ በጉባዔው ዋዜማ አስጠንቅቀው ነበር። ግን ይህ ጥሪ ሰሚ ጆሮ ማግኘቱ እስከፊታችን ሚያዚያ ወር የቡድኑ የፊናንስ ሚኒስትሮች ጉባዔ ድረስ በሚፈጸሙት ድርጊቶች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የሚለካ ነው የሚሆነው።

የቡድን-ሃያ ተጠሪዎች ከዓለም ኤኮኖሚ ሚዛናዊነት ጉዳይ ባሻገር የጥሬ ዕቃዎችንና የምግብ ምርቶችን ዋጋ ማስተካከል በሚቻልበት ሁኔታም ተነጋግረዋል። የወቅቱ የዋጋ ንረት ለባሰ የኑሮ ውድነትና ለአዲስ የረሃብ ቀውስ መንስዔ እንዳይሆን ማስጋቱን ነው የፈረንሣዩ ፕሬዚደንት ያስገነዘቡት። ሌላው የጉባዔው ተጨማሪ የውይይት ነጥብ የአካባቢ አየርን ለመጠበቅ የሚያስፈልገውን በጀት በማቅረቡ ላይ ያተኮረ ነበር።

ቡድን-ሃያ መንግሥታት ገና በኮፐንሃገኑ የአካባቢ አየር ጉባዔ ወቅት እሰከ 2020 ዓ.ም. ድረስ ለታዳጊ አገሮች አንድ መቶ ሚሊያርድ ዶላር ለማቅረብ ቃል መግባታቸው ይታወቃል። ዓላማውም የአየር ለውጥ ያስከተለውን ሁኔታ መቋቋም ነው። ነገር ግን በዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ የተነሣ የብዙዎቹ መንግሥታት ካዝና ባዶ በመሆኑ ጉዳዩ እስካሁን እንደታሰበው ወደፊት አልተራመደም። በዚሁ የተነሣም አንድ ተስማሚ ጽንሰ-ሃሣብ ተነድፎ ለፊታችን ሕዳር የቡድን-ሃያ መንግሥታት የመሪዎች ጉባዔ እንደሚቀርብ ነው የሚጠበቀው።

መሥፍን መኮንን    
                        ሂሩት መለሰ