የሊቢያ ውጊያ | አፍሪቃ | DW | 17.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሊቢያ ውጊያ

የሊቢያ ተቀናቃኝ ሚሊሽያዎች በሃገሪቱ የበላይነት ለመያዝ የሚያካሂዱት ትግል እንደቀጠለ ነው ። በተለይ በሊቢያው የትሪፖሊ አየር ማረፊያ የሚካሄደው ውጊያ ዛሬም አላበቃም። ከእሁድ አንስቶ የተዘጋው አውሮፕላን ማረፊያው ሥራ እስኪጀምር ድረስ ወራት ሊወስድ እንደሚችል ይገመታል በመገናና ብዙሃን ዘገባ መሰረት በውጊያው ሰዎች ተገድለዋል ፣ቆስለዋልም ።

የቀድሞው የሊቢያ መሪ ሞአመር ጋዳፊ ከ3 ዓመት በፊት ከሥልጣን ተወግደው በውጊያ ከተገደሉበት ጊዜ አንስቶ የሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ አየር ማረፊያ በሲንታን ከተማ ሚሊሽያዎች ቁጥጥር ስር ነው የቆየው ። ባለፈው እሁድ ከሚስራታ እና ከትሪፖሊ ከተሞች የተውጣጡ ሚሊሽያዎች አውሮፕላን ማረፊያውን በእጃቸው ለማስገባት በጠላቶቻቸው በሲንታን ሚሊሽያዎች ላይ በሰነዘሩት ጥቃት የተጀመረው ውጊያ አሁንም አልቆመም ። ‘ሊቢያ ሄራልድ‘የተባለው የኢንተርኔት ጋዜጣ እንደዘገበው በውጊያ ቢያንስ 35 ሰዎች ተገድለዋል ። ሌሎች 70 ደግሞ ቆስለዋል ። ከሞቱት መካከል ሰላማዊ ሰዎች ይኑሩበት አይኑሩበት ግልጽ አይደለም ። የሊቢያ መንግሥት ቃል አቀባይ አህመድ ላሚን እንደተናገሩት በሊቢያው አየር ማረፊያ መጠነ ሰፊ ጉዳት ነው የደረሰው ። በጥቃቱ ለደረሰው ጉዳት መልሶ ግንባታ እንዲሁም የሊቢያ ኤኮኖሚ እንዲያንሰራራ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የሃገሪቱ ገንዘብ ያስፈልጋል ።በትሪፖሊ አየር ማረፊያ ላይ ባለፉት ሶስት ቀናት በሮኬቶች በተፈጸመ ጥቃት ክፉኛ ከተጎዱት መካከል የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያው ማማ ይገኝበታል ።

«ከአውሮፕላን ማረፊያው 90 በመቶ ያህሉ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል ።ጥገናው ወራት ሊወስድ ይችላል ። በመቶ ሚሊዮኖች ዲናር የሚቆጠር ገንዘብም ሊያስፈልግ ይችላል ።የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያው ማማ የነዳጅ ዘይት ቦቴዎች እንዲሁም መኪናዎች የብሄራዊ ፀጥታ መሥሪያ ቤት ንብረት የሆኑ የመንገደኞች አውሮፕላኖች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ። የአየር ማረፊያው የጉምሩክ ህንፃና የአውሮፕላኖች መጠገኛ ህንፃም እንዳልነበሩ ሆነዋል ። »

የትሪፖሊ አየር ማረፊያ ከሊቢያ ዋነኛ የትራንስፖርት በሮች አንዱ ነው ። በትልቅነት ሁለተኛው የቤንጋዚው አየር ማረፊያ ከወራት በፊት በተካሄደ ከባድ ውጊያ እንደተዘጋ ነው ። የሚስራታው አውሮፕላን ማረፊያ ትናንት ቢከፈትም በትሪፖሊው አየር ማረፊያ መዘጋት ምክንያት ሥራewne መቀጠል አልቻለም ። የሊቢያው የፀጥታ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞቹን ከሃገሪቱ አስወጥቷል ። ሃገሪቱን የማረጋጋትና ዲሞክራሲያዊ አቅጣጫ የማስያዝ ተልዕኮ የተሰጠው በሊቢያ የተመድ የድጋፍ ተልዕኮ በምህፃሩ UNSMIL አሁን ባለው ሁኔታ ሊቢያ ውስጥ መሥራት አይቻልም ብሏል ።ሊቢያ ውስጥ አሁን በማዕከላዊ መንግሥትና በከተሞች በጎሳና በጎጥ በተከፋፈሉት ኃይሎች መካከል ሥልጣን ማደላደል የሚቻልበት መንገድ አይታይም ። በአብዮቱ የተመሰረቱት በሃገር

ውስጥ ሚሊሽያዎች የሚደገፉት ኃይሎች በሃገሪቱ ለፖለቲካና የኤኮኖሚ የበላይነት መፎካከራቸው ቀጥሏል ። አሁን በትሪፖሊ የአየር ማረፊያና በሌሎችም ከተሞች የሚካሄደው ውጊያ መንስኤ ይኽው ነው ።ሊቢያ ውስጥ ከሚዋጉት ኃይሎች ውስጥ በጋዳፊ ዘመን የጦር ኃይል አዛዥ የነበሩት ጀነራል ካሊፋ ሃፍታር አንዱ ናቸው ። ጀነራል ካሊፋ በሁለተኛዋ የሊቢያ ትልቅ ከተማ ቤንጋዚ ውጊያ እያካሄዱ ነው ። የደጋፊዎቻቸው ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑ የሚነገርላቸው ጀነራል ካሊፋ የአሁኑን ምክር ቤት ጨምሮ ተቀናቃኝ ሚሊሽያዎች እንዲሁም ደጋፊዎቻቸውን ከሊቢያ የማባረር ዓላማ ይዘው ነው የሚዋጉት ።የሊቢያ አዝማሚያ ያሰጋው ማዕከላዊ መንግሥት የዓለም ዓቀፉን ማህበረሰብ ድጋፍ ለመጠየቅ አስቧል ።የመንግሥት ቃል አቀባይ አህመድ ላሚን« አሁን ዓለም ዓቀፍ ኃይሎች እገዛ እንዲያደርጉ የሃገሪቱን አቅም ንብረትንን የዜጎቿን ህልውና እንዲጠብቁ ለመጠየቅ የሚያስችል በቂ ሁኔታ አለ ። አገሪቱ ተቋማትን በተለይም ደግሞ ጦር ኃይሉንና ፖሊሱን መልሶ መገንባት ይቻላት ዘንድ ምስቅልቅሉንና የተዛባውን ስርዓት ለማስተካከል እገዛ ሊያደርጉ ይችላሉ ።»የቀጠለው የሊቢያ ውጊያ በቅርቡ ድምፅ በተሰጠበት የምክር ቤት ምርጫ ለሚመሰረተው አዲሱ ፓርላማ ትልቅ ፈተና እንደሚሆን ይገመታል ።ሚሊሽያዎቹ ፣ወሳኞቹ እነርሱ እስከሆኑ ድረስ አዲሱ ፓርላማና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚመሰረተው መንግሥት አቅመ ቢስ ሆኖ ነው የሚቀረው ይላሉ ማይንዝ የሚገኘው የአረብ ሃገራት ጉዳዮች ጥናት ተቋም ባልደረባ ጉንተር ማየር ።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic