የሊቢያ አዳዲስ መሪዎችና ጉዞዋ | ዓለም | DW | 05.09.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሊቢያ አዳዲስ መሪዎችና ጉዞዋ

።«ሊቢያዎች የገንዘብ እጥረት ችግር የለባቸዉም።ይልቅዬ ሊቢያ በቂ የገንዘብ አቅም አላት።እንደሚመስለኝ በጣም ባጣዳፊ የሚያስፈልጋቸዉ ቴክኒካዊ ርዳታ ነዉ።»

default

አዲሱ መሪ ካዲሱ ባንዲራ ጋር

04 09 11

«ትሪፖሊ ለአርባ ሁለት አመታት በአምባገነን ጠንካራ መዳፍ ሥር ነበረች።ብዙ ተቋማት እንደ ሌሉን፣ በርካታ የሲቢል ማሕበረሰባት እንደሌሉን እናዉቃለን።ሥለዚሕ በዚሕ ረገድ ከዜሮ ነዉ የምንጀምረዉ።»

ማሕሙድ ሻማም-የሊቢያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት አፈ-ቀላጤ።የትናንት ሳምንት እሁድ።ሻማምም ሆኑ የበላይ የበታቾቻቸዉ ራሳቸዉ ከስድስት ወር በፊት በሊቢያም ሆነ በአለም የፖለቲካ፣ መድረክ ከዜሮ የማይሻሉ፣ኢምንት ነበሩ።ዛሬ ግን የሊቢያ መሪዎች፣ የሐያል-ሐብታሙ ዓለም ታማኝ ወዳጅ ናቸዉ።ከዜሮ-በመንፈቅ እድሜ ለመሪነት፣ ለሐያሉ ዓለም ወዳጅነት የበቁት ሐይላት ማንነት፣ ከዜሮ የሚያስጀምሯት ሐገራቸዉን የተትረፈረፈ ሐብት ለሕዝባቸዉ እኩል የማዳረስ፣ ፍትሕ ዲሞክራሲን የመገንባት አቅም፣ ብልሐታቸዉ ጥልቀት፣ የሃሉ ዓለም ድጋፍ እስከየትነት ግን በርግጥ ያጠያቃል።ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

ያቺ ቀን።እንደ አስካምናዉ ቢሆን ኖሮ፣ ሊቢያን ከአርባ-አንድ ዘመን በላይ ረግጠዉ የገዙት፣ በሻማም ቋንቋ «በዜሮ ላስቀሯት» ለኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ አመራር ታማኝ፣ ታዥነታቸዉን ለማረጋገጥ ሚሊዮኖች የሊቢያ አደባባዮችን ባጥለቀለቋቸዉ ነበር። በሺ የሚቆጠሩ ሹማምንት፣ አገልጋይ፣ ታማኞቻቸዉ እጃቸዉን ለመሳም-መሳለም በተራኮቱ ነበር።

በመቶ የሚቆጠሩ የዉጪ ሐገር ዲፕሎማት-አቻዎቻቸዉ የመልካም ምኞት መግለጫዉን ባዥጎደጎዱት ነበር።የሚሉ-የሚያደርጉትን ለመስማት ሚሊዮነ ሚሊዮናት በየራዲዮ-ቴሌቪዥኑ ላይ ጆሮ-አይናቸዉን በለገቱ ነበር።ዘንድሮ ግን በርግጥ አምናም፣ ሐቻምና ድሮም አይደለም።

የታላቁ ሶሻሊስታዊ ሕዝባዊት ሊቢያ አረብ ጅሙሕሪያ ታላቅ መሪ የዚያን ዕለት የሚሉ የሚያደርጉትን ቀርቶ ያሉበትንም የሚያዉቀዉ-እሱም እሳቸዉም ያሉበትን የማያሳዉቅ ሲበዛ ጥቂት ነዉ።መስከረም-1 ከ1969ጀምሮ ለአርባ ሁለኛ ጊዜ ዞሮ ሲገጥም፥ በቀደም ሐሙስ የሊቢያ ትልቆች-ትንሽነት፣ የብዙዎቹ ኢምንትነት፣ ደግሞ በተቃራኒዉ የትንሾቹ-ትልቅነት፣ የኢምንቶቹ ብዙ ነት በግልፅ ተረጋገጠ።

ከ1975 ጀምሮ መጀመሪያ እንደ አዉራጃ ረዳት አቃቤ-ሕግነት፣ ቀጥሎ እንደ ዳኛ የቃዛፊን የታላቅ መሪነት መርሕ ከሩቅ ግን ታላቁ መሪ በሚፈቅዱት መንገድ በማስፈፀማቸዉ በ1978 መጀመሪያ የአዉራጃ-በማከታተል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኝነትን ተሾሙ።

ሊቢያ ዩኒቨርቲ የተማሩትን የሽሪዓ ሕግ በልምድ እየገሩ፣እያዳበሩ፥ ከእድሜ ጋር በፖለቲካዉ ጥበብ እየበሰሉ፣ ለታላቁ መሪ ታማኝነታቸዉን ሲያስመስክሩ፥ የፍትሕ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ተረከቡ።2007።ሙስጠፋ አብዱል ጀሊል።


ቃዛፊ-በየአመቱ ትሪፖሊ አደባባይ የሚሉ፣ የሚያደርጉትን ለሰላሳ ሁለት አመት ከሩቅ፣አራት አመት ከቅርብ ይከታተሉ የነበሩት መስጠፋ አብዱል ጀሊል ዘንድሮ መስከረም አንድ-የቃዛፊን ሥልጣን መቆጣጠራቸዉን በዓለም ሐያላን ለማስመረቅ ፓሪስ ላይ ሲጠባበቁ፥ ማረጋገጪያዉን ከሚሰጡት አንዷ የጀርንዋ መራሒተ መንግሥት ወይዘሮ አንጌላ ሜርክል በርሊን ላይ ሁሉንም አሉት።«ሊቢያዎች የገንዘብ እጥረት ችግር የለባቸዉም።ይልቅዬ ሊቢያ በቂ የገንዘብ አቅም አላት።እንደሚመስለኝ በጣም ባጣዳፊ የሚያስፈልጋቸዉ ቴክኒካዊ ርዳታ ነዉ።»

በርግጥም ለሊቢያዎች ድሮም ዘንድሮም ገንዘብ በሽ ነዉ።የሊቢያ ሕዝብ አመፅም እንደ ቱኒዚያ፥ እንደ ግብፅ ወይም እንደየመን ብጤዎቹ የኑሮ ዉድነት ንረት፥ የሥራ አጥነት ችግር አልነበረም።ፍትሕ-ዲሞክራሲ እንጂ።

Nicolas Sarkozy und Mahmoud Jibril

ጅብሪል-ያዲሱ መንግሥት የዉጪ ገፅ ከሳርኮዚ ጋር

ሙስጠፋ አብዱ ጀሊል ለሚመሩት ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት የመንግሥትነት ይፋ እዉቅና የሰጠዉ የፓሪስ ጉባኤ ደግሞ አንጌላ ሜርክል ለሊቢያዎች ያስፈልጋል ያሉትን ርዳታ የቴክኒክ ለመስጠት ቃል ገብቷል።ከስልሳ የሚበልጡ ሐገራትን የወከሉት ጉባኤተኞች በጋራ እንዳሉት ለሊቢያ ጊዚያዊ መንግሥት ከዲፕሎማሲያዊ እዉቅና እስከ ፖሊስ ሥልጠና፥ ከባለሙያዎች ምክር እስከ መንግስት አወቃቀር ዙሪያ መለስ ድጋፍ ይሰጣሉ።

የጉባኤዉ አስተናጋጅ የፈረሳዩ ፕሬዝዳት ኒኮላ ሳርኮዚ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ የዘረፉት ያሉት ገንዘብ የአዉሮጳና የአሜሪካ ባንኮች እንዲለቁ ጉባኤተኞች ወስነዋል።«ቃዛፊ ያጭበረበሩት ገንዘብ ለሊቢያ ሕዝብ መመለስ አለበት።የትናንትናዋ ሊቢያ ገንዘብ ለዛሬይቱ ሊቢያ አገልግሎት ይዉል ዘንድ እንዲለቀቅ ሁላችንም ተስማምተናል።»

ሳርኮዚ «ቃዛፊ ያጭበረበሩት» ያሉት ገብዘብ አንድ መቶ ሰባ ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል።አብዛኛዉ ገንዘብ አዉሮጳና አሜሪካ በጣሙን ዩናይትድ ስቴትስ፥ ብሪታንያ፥ ፈረንሳይና ጀርመን ባንኮች ዉስጥ ነዉ ያለዉ።እንደየትኛዉም ሐገር ሕገ-ደንብ በየትኛዉም ወንጀል ከሚከሰስ ሰዉ ጋር «አባሪ እና ተባባሪ» የሚባሉ ግብረ-አበሮችም ተጠያቂዎች ናቸዉ።

ቃዛፊ ሲወነጀሉ የተጭበረበረ ገንዘብ ያስቀመጡት ወገኖች በአባሪ ተባባባሪነት የማይጠየቁበት፥ የቃዛፊ አጭበርባሪነትን ለማወቅ ዓለም አርባ ሁለት ዘመን የቆየበት ሰበብ-ምክንያት በርግጥ ግራ አጋቢ-አጠያያቂም ነዉ።

በቃዛፊ ዉድቀት ማግሥት ከፈራረሱት የሊቢያ መስሪያ ቤቶች የወጡት ሰነዶች ደግሞ ዛሬ የቃዛፊን አምገናዊነት፥ ገዳይ፥ አረመኔነት ዘራፊ-አጭበርባሪነት የሚነግሩን ሐያላን መንግሥታት በየሥለላ ተቋሞቻቸዉ አማይከይነት ከቃዛፊ መንግሥት ጋር የነበራቸዉን የቅርብ ትብብርና ወዳጅነት እያጋለጡ ነዉ።ነገሩ ብዙ ነዉ።ብቻ ቃዛፊን ከሥልጣን ለማስወገድ የዲፕሎማሲ-ፖለቲካ፥ የአየር ድብደባ፥ የጦር መሳሪያ ድጋፍ፥ ሥልጠናዉን ያስተባበሩት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ሳርኮዚ አዲሲቱ ያሏት ሊቢያ የከንግዲሕ ዋና ዘዋሪ ቢያንስ ላሁኑ፥ ቢያንስ ለይፋዉ እሳቸዉ ናቸዉ።ሙስጠፋ አብዱል ጀሊል።

ለኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ የትዉልድ ከተማ ለሲርት ሕዝብ በቅርቡ ያስተላለፉት መልዕክት፥ እንደ ፖለቲከኛ ድል አድራጊነታቸዉን፥ እንደ ዲፕሎማት በግድምድሞሽ ቋንቋ፥ እንደ ባሕላዊ መሪ በአግባቢ ቃላት መግልፅ መቻላቸዉን መስካሪ ነዉ።

«እዚያ ዉጊያ ይደረጋል ብዬ አልጠብቅም።የሲርት ልጆች ለወደፊቱ እኛን ይደግፋሉ።አሁንም ቢሆን የተወሰኑት የአማፂ ቡድን መስርተዋል።የሚያምኗቸዉን ሰዎች መርጠዋል።ሑከትና ጥፋትን ማስቀረት ይፈልጋሉ።»

ፖለቲከኛነታቸዉን ያሳዩት ግን የሊቢያ በተለይ የቤንጋዚ ሕዝብ የሙዓመር ቃዛፊ አገዛዝን መቃወም ከጀመረ በሕዋላ ነዉ።ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ የቤንጋዚ አመፀኞችን ለማግባባት ከአባቢዉ ከሚወለዱት ከፍትሕ ሚንስትራቸዉ የተሻለ ባለሥልጣን አላገኙም ነበር።አብዱል ጀሊል የካቲት አጋማሽ ቤንጋዚ እንደደረሱ ቃዛፊን ከድተዉ አማፂያኑን ተቀላቀሉ።

ወዲያዉ እንደሳቸዉ ሁሉ የቃዛፊ መንግሥትን የከዱ የቀድሞ ባልደረቦቻቸዉን፥ የጦር መኮንኖችን፥ የጎሳ መሪዎችንና ምሁራንን ሰብስበዉ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት የተሰኘዉን ተቋም መሠረቱ።እንደ ተማሪ፥ ያጠኑትን፥ እንደ አቃቤ ሕግ፥ እንደ ዳኛ፥ እንደ ሚንስትርም የሠረበትን የሕግ የበላይነት ለማስከበር ብዙ መጣር መሞከራቸዉ ግን ፖለቲከኛ ከመሆናቸዉ በፊትም ተመስክሮላቸዋል።

ከዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር መስሪያ ቤት አፈትልኮ የወጣ ሰነድ እንደሚያመለክተዉ በሊቢያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳዳር ጄን ክሬትስ በሁለት ሺሕ አስር ከአብድል ጀሊል ጋር ያደረጉትን ዉይይት አበረታች እና ገንቢ ይሉታል።አብዱ ጀሊል የሚመሩት የፍትትሕ ሚንስቴር መስሪያ ቤት ሠራተኞች ከዩናይትድ ስቴት ዲፕሎማቶች ጋር ተባብረዉ እንዲሰሩ መፍቀዳቸዉን አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

አብዱ ጀሊል ፍርድ ቤት እንዲለቀቁ የወሰነላቸዉ ሰወስት መቶ ያሕል እስረኞችን መንግሥት ባለመልቀቁ የሕግ የበላይነት መጣሱን በመጥቀስ በሁለት ሺሕ አስር ሥልጣን ለመልቀቅ በፍይፋ የጠየቁ፥ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ፊት ለፊት የተጋፈጡ የመጀመሪያዉ ሚንስትርም ናቸዉ።

ሑይማን ራይትስ የተሰኘዉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሐላፊ ሔባ ሞራዬፍ አብዱል ጀሊል ያሉትን ባሉ ሰሞን «አንድ የአረብ የፍትሕ ሚንስትር ሐገሩ ያለዉን እጅግ አስፈሪ የስለላ ድርጅት እንዲሕ በይፋ ሲተች አይቼ አላዉቅም»

ከእኒያ እስረኞች መሐከል ምናልባት በሲ፤ አይ፥ ኤ፥ ወይም በኤም አይ ስድስት ትብብር የተያዘ፥ የተገረፈ፥ የተሰቃየ ሊኖር ይችላል።ሰዉዬዉ እስረኞቹ ይለቀቁ ያሉት የዋሽንግተን-ለንደኖች እጅ እንዳለበት እያወቁ ከነበረ በርግጥ ከደፋርም-ደፋር የፍትሕ ሰዉ እንጂ ለፖለቲ-ሥለላዉ ጥልፍልፍ እንግዳ ነበሩ።በምዕራቡ ዓለም ዘንድ ያላቸዉ እዉቅና፥ የጦር አመራር ችሎታችዉም ብዙ የሚባልለት አይደለም።

ምዕራባዉያኑን በመያዙ ረገድ አብዱል ጀሊል የሚጎድላቸዉን ማሕሙድ ጅብሪን አሟልተዉታል። እንደ መንግሥት የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን የያዙት የሽግግር ምክር ቤቱ የሥራ-አስፈፃሚ ቦርድ ሊቀመንበርነ ማሕሙድ ጅብሪል አሜሪካ የተማሩ፥ አሜሪካና በተለያዩ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ዩኒቨርቲዎች ያስተማሩ ምሁር ናቸዉ።የቃዛፊን መንግሥት ከመክዳታቸዉ በፊት የሊቢያ ብሔራዊ የኢኮኖሚ ልማት ቦርድ የተሰኘዉ ተቋም ሊቀመንበር ነበሩ።

ፈረንሳይ ከመላዉ ዓለም ቀድማ መጋቢት አስር ለሽግግር ምክር ቤቱ የመንግሥትነቱን እዉቅና እንድትሰጥ ፕሬዝዳት ሳርኮዚን ያሳመኑት፥በሳርኮዚ በኩል የምዕራባዉያን ጦር የቃዛፊን ሐይል እንዲደድብ ከፍተኛዉን ሚና የተጫወቱት እሳቸዉ ናቸዉ።ዶክተር ማሕሙድ ጅብሪል።

ከእንግዲሕ የሊቢያ ሪፐብሊክ የምትባለዉን ሐገር አዲስ ጦር ይመራሉ ተብሎ በሰፊዉ ይነገርላቸዉ የነበሩት ጄኔራል አብዱል ፈታሕ ዩኒስ ነበሩ።በቅርቡ ተገደሉ።የከእንግዲሁ ተስፋ በኮሎኔል ዑመር አል-ሐሪሪ ላይ ነዉ።ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ለሥልጣን ባበቃዉ በ1969ኙ መፈንቅለ-መንግሥት የተሳተፉት ሐሪሪ በአማፂያኑ ዘንድ እንደ ጀግና የሚታዩ ናቸዉ።

የነዚሕና የባልደረቦቻቸዉ ጥረት፥ የምዕራቦች ሁለንተናዊ ድጋፍ፥ የሊቢያ ሕዝብ ፍላጎትም ታክሎበት የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ሊቢያ ከቃዛፊ ዉድቀት በሕዋላ እስካሁን ወደ መረጋጋት እያመራች ነዉ።

«አንዳዶች ልክ እንደ ቃዛፊ ሁሉ የሊቢያ ሕዝብ ለነፃነት አይታመንም፥ ከዛፊ ከተወገዱ ሐገሪቱ ትታወካለች እያሉ ያስጠነቅቁ ነበር።ሥርዓቱ ሲወገድ ግጭት ረብሻ ይቀሰቃል ብለዉ ያሰቡም ነበሩ።ለአመታት ከዘለቀዉ እመቃ በሕዋላ፥ በቅርብ ዕለታትና ወራት ከነበረዉ ጦርነት ጠባሳ በሕዋላ አሁን ሊቢያ የምናየዉ ግን በጣም ማራኪ ነዉ።እርግጥ ነዉ ወደ ፊት ብዙ ፈተናዎች ያጋጥማሉ። ይሁንና ሊቢያዉያን ቁርጠኝነታቸዉን፥ መንፈሳቸዉንና ፅናታቸዉን ለአለም እያሳዩ ነዉ።»

የኢራቁ የቀድሞ ፕሬዝዳት ሳዳም ሁሴን ከስልጣን የተወገዱ ሰሞን ከዋሽንግተን እና ለንደን ተመሳሳይ መልዕክት ተነግሮ ነበር።እርግጥ ነዉ ሊቢያ ዉስጥ የኢራቅ የአይነት የሺዓ-ሱኒ የሚባል የሐይማኖት ሐራጥቃ ልዩነት የለም።ከአንድ መቶ አርባ በሚበልጡ ጎሳዎች የተከፋፈለዉን፥ በቃዛፊ ዘመን በገንዘብ ይበሻበሽ የነበረዉን ሕዝብ አስተባብሮ ማስተዳደር፥ዲሞክራሲያዊ ነፃነትን የሚሻዉን ወጣት፥ ባሕላዊን አስተዳደር ከሚሹት የጎሳ መሪዎች ፍላጎት ጋር አቀራርቦ ማስተዳደር የአብዱል ጀሊልና የባልደረቦቻቸዉን ብልሐትን ይጠይቃል።

Libyen Rebellen in Bani Walid

የአዲሱ መንግስት ጦር-ለመጨረሻዉ ፍልሚያ፦ ባኒ ዋሊድ


የሊቢያ አዳዲስ መሪዎች ከዜሮ ተነስተዉ በመንፈቅ እድሜ ለመንግሥትነት መቃቱ በርግጥ ሰምሮላቸዋል።የሐያላኑን ድጋፍ ማግኘቱም አልገደዳቸዉም።እስካሁን በፀረ-ቃዛፊ አቋማቸዉ አንድ የመሰሉት ባንድነታቸዉ አብረዉ የሚጓዙት ርቀት-እስከየትነት አለመታወቁ ነዉ ቀቢፀ ተስፋዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic