የሊቢያ ምክር ቤት ተማፅኖ | አፍሪቃ | DW | 16.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የሊቢያ ምክር ቤት ተማፅኖ

በሊቢያ ከጥቂት ቀናት በፊት ስራውን የጀመረው አዲሱ ምክር ቤት የተመድ በተለያዩት ተቀናቃኝ ሚሊሺያ ቡድኖች መካከል ከብዙ ሳምንታት ወዲህ በቀጠለው ውጊያ ሰበብ ትልቅ ችግር ውስጥ የምትገኘዋን ሀገራቸውን እንዲረዳ

ጠየቀ። የተመድ የሊቢያን ሕዝብ ደህንነት፣ የሀገሪቱን ፀጥታ ጥበቃ እና የተቋማትን ኅልውና ለመከላከል እና ለማረጋገጥ የሚያስችል ርምጃ እንዲወስድ ነው የምክር ቤቱ እንደራሴዎች ባለፈው ረቡዕ የተማፀኑት።

ይኸው ጥሪ የቀረበው በወቅቱ የሊቢያ ምክር ቤት ከሚገኝበት ከመዲናይቱ ትሪፖሊ ወደ 1,000 ኪሎ ሜትር ርቆ ከምትገኘው የባህር ጠረፍ ከተማ ፣ ቶብሩክ ነው። ምክር ቤቱ መቀመጫውን ከትሪፖሊ ወደ ቶብሩክ ያዛወረውም በመዲናይቱ በሚካሄደው ውጊያ ለመራቅ በማሰብ ነው። የዓለም አቀፉ ድርጅት እንዴት ሊረዳ እንደሚችል ግን እንደራሴዎቹ በግልጽ አላስቀመጡም።

ይህ በዚህ እንዳለ፣ በትሪፖሊ እና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች አሁንም ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው። እንደሚታወቀው ፣ በትሪፖሊ የሚገኙት ብዙዎቹ የውጭ ሀገራት ኤምባሲዎች እና ለሊቢያ የተቋቋመው የተመድ ተልዕኮ ሰራተኞቻቸውን ከተመሰቃቀለችው ከተማ ካስወጡ ሰንበት ብሏል።

በሊቢያ የቀድሞው የኦስትርያ ኤምባሲ የመከላከያ ጉዳዮች ተጠሪ ቮልፍጋንግ ፑዝታይ እንዳመለከቱት፣ የምክር ቤቱ ጥሪ በምክር ቤቱ የተወከሉት የተለያዩት ቡድኖች እንደራሴዎችን ክሽፈት ያሳየ ነው።

« ይኸው ተማፅኖ በሊቢያ ዴሞክራሲያዊውን ሥርዓት ለመፍጠር የሚፈልገው ኃይል ፖለቲካዊ ውሳኔ መውስድ የማይችል፣ ፍፁም አቅም አልባ ቡድን መሆኑን አረጋግጦዋል። »

ይሁንና፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተመረጠው አዲሱ ምክር ቤት ጠቅላላ የሊቢያን ሕዝብ የማይወክል መሆኑን ፑዝታይ አስረድተዋል።

« ለምክር ቤታዊው ምርጫ የተሳተፈው መራጭ ሕዝብ ቁጥር በጣም ንኡስ ነበር። እአአ በ2012 ዓም ድምፁን ከሰጠው መካከል አንድ ሦስተኛው ብቻ ነው የመረጠው። በዚህም የተነሳ የምክር ቤቱ ሕጋዊነት አጠያያቂ ሆኖዋል። ለምርጫ የወጣው ጥቂቱ ሕዝብ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያምን ነው። በመሆኑም፣ የሙሥሊም ወንድማማችነት ማኅበር ደጋፊዎች ከምርጫው ርቀዋል። »

የአውሮጳ የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት ባልደረባ ማቲያ ቶአልዶ የሊቢያ ምክር ቤት የሰሞኑን ተማፅኖ ያቀረበው በሁለት ምክንያቶች የተነሳ ነው ይላሉ።

« አሁንም በስራ ላይ የዋለ የተመድ ውሳኔ አንቀጽ 1973 መኖሩን መዘንጋት የለብንም። እንደሚታወሰው ይኸው የውሳኔ አንቀጽ ነበር በሊቢያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንዲኖር መንገዱን ክፍት ያደረገው። ውሳኔው ከዚህ በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሊቢያን ሕዝብ ደህንነት የመከላከል ኃላፊነት እንዳላበት አሳስቦዋል። የሰሞኑ የሊቢያ ምክር ቤትም ጥሪ በዚሁ ውሳኔ የተጠቀሰውን ያዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የሲቭሉን ሕዝብ ደህንነት የመከላከል ኃላፊነት ለማጉላት የታሰበ ነው። የሊቢያን ከለል መጠበቅን በተመለከተ የዓለሙ መንግሥታት ድርጅት ውሳኔ ማሳለፉን ያስታውሳሉ። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ የውጭ ኃይላትን በሌሎች ሀገራት በሚካሄዱ ውዝግቦች የተነሳ ችላ በተባለችው ሊቢያ ውስጥ አንድ ርምጃ እንዲወስዱ ለማሳሰብ ነው። »

በዩክሬይን፣ በሶርያ፣ በጋዛ ሠርጥ እና ካለፉት ጥቂት ቀናት ወዲህ ደግሞ በኢራቅ የሚካሄዱት ውዝግቦች በሊቢያ በተቀናቃኝ ሚሊሺያዎች መካከል የቀጠለው ውጊያ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት እንዳያገኝ አድርጓል። በወቅቱ እንደሚታየው በተለያዩ የሊቢያ አካባቢ ያሉት የተለያየ አካባቢያዊ፣ ሀይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ አመለካከት የሚወክሉት ቡድኖች እርስ በርስ መፋለማቸውን ቀጥለዋል። በሊቢያ በመጨረሻ በተካሄደው ውጊያ ብቻ ከሁለት መቶ የሚበልጥ ሰው ተገድሎዋል። ባለፈው ረቡዕም አምስት ሲቭሎች በምዕራባዊ ትሪፖሊ በተካሄደው ውጊያ ወቅት በተተኮሰ ሮኬት ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በሊቢያ እየተካሄደ ያለው ውጊያ በፅንፈኛ ሙሥሊምሞች እና ሀይማኖትን መሠረት ባላደረገት ቡድኖች መካከል የሚካሄድ ነው ብሎ ለማስተናነስ እንደማይቻል የቀድሞው የኦስትርያ ኤምባሲ የመከላከያ ጉዳዮች ተጠሪ ቮልፍጋንግ ፑዝታይ አስረድተዋል። ይሁንና፣ ይላሉ ፑዝታይ፣ የፅንፈኛ ሙሥሊም ኃይላት በሚስራታ አካባቢ ጠንካራ ሠፈር ሲኖራቸው፣ ተቀናቃኞቻቸው ደግሞ በሲንታን አካባቢ እየተንቀሳቀሱ ነው።

አዲሱ የሊቢያ ምክር ቤት በሀገሩ የሚንቀሳቀሱትን የበርካታዎቹን ተዋጊ ቡድኖችን ሚሊሺያዎች የጦር መሳሪያ ትጥቅ ማስፈታት ይፈልጋል። ይህ ግን አዳጋች ሊሆን እንደሚችል የአውሮጳ የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት ባልደረባ ማቲያ ቶአልዶ አስረድተዋል።

« ከሚሊሺያዎቹ መካከል ብዙዎቹ በአሁኑ ጊዜ በመደበኛው የሊቢያ ፀጥታ ኃይላት ውስጥ በይፋ ተዋኅደዋል። እንዲያውም፣ እነዚሁ እርስበርስ የሚዋጉት የተለያዩት ቡድኖች ሚሊሺያዎች ከመንግሥት ደሞዝ ይከፈላቸዋል። ይህ በወቅቱ የሊቢያ ውዝግብ ውስጥ የሚታይ ምጸት ነው። እና ምክር ቤቱ አሁን እየሞከረ ያለው ቢያንስ ላንዳንዶቹ የሚሰጠውን ክፍያ ለማስቆም ነው። »

ሊቢያውያኑ እንደራሴዎች ይህን ማድረግ ያሳካላቸው መሆን አለመሆኑ አጠያያቂ ነው። ክፍያውን የማስቆሙ ርምጃ፣ የአውሮጳ የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት ባልደረባ ማቲያ ቶአልዶ እንደሚገምቱት፣ አንዳንዶቹን ሚሊሺያዎች የሚያካሂዱትን ውጊያ እና የኃይል ተግባር እንዲጠናክሩት ያደርጋቸዋል።

ሁኔታዎች ይህን በመሰሉበት ባሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሊቢያ ውዝግብ እንዳይባባስ ሊያደርጋቸው የሚችሉ አራት አማራጮች እንዳሉት በሊቢያ የቀድሞው የኦስትርያ ኤምባሲ የመከላከያ ጉዳዮች ተጠሪ ቮልፍጋንግ ፑዝታይ ይናገራሉ። የመጀመሪያው እስካሁን እንደሚያደርጉት ውዝግቡ እንዲያበቃ ይረዳሉ የሚላቸውን ድርድሮች መደገፉን መቀጠል ይሆናል። በዚሁ ድጋፉ ላይ ፣ ምንም እንኳን ያለፉ ተሞክሮዎች አበረታቺ ባይሆኑም፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረ ሰብ ቃታር እና ቱርክን የመሳሰሉ ሀገራትን በይበልጥ ማሳተፍ እንደሚገባው ፑዝታይ ገልጸዋል።

« ይህ ዓይነቱ አሰራር ትልቅ የተሳካ ውጤት ያስገኛል ብየ አላስብም። ምክንያቱም ካሁን ቀደም የተደረጉ በርካታ ድርድሮች አንዳችም የረባ ውጤት አላስገኙም። አሁንማ ውጤታማ ይሆናሉ ተብሎ አይጠበቅም፣ ያም ቢሆን ግን መሞከሩ ተገቢ ነው። »

ሁለተኛው አማራጭ ውዝግቡ እንዳይባባስ ለማድረግ በተቻለ መጠን መሞከር ነው። ለዚህም ድንበሮችን በመዝጋት የሰብዓዊ ርዳታ ለማቅረብ ጥረት ሊደረግ ይችል ይሆናል። በዚሁ ጊዜ ግን የውጭው ዓለም ጣልቃ መግባት አይኖርበትም። ይህ ግን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሊቢያ ያደረገው ጣልቃ ገብነት መክሸፉን ማመን ስለሚሆን ተግባራዊነቱን ፑዝታይ ተጠራጥረውታል።

ሶስተኛው ትሪፖሊ ደረጃ በደረጃ የመንግሥት መዋቅር ግንባታን የምትጀምርበት አሰራር ነው። ይሁን እንጂ፣ ይህን በስራ በተግባር ለመተርጎም በወቅቱ በመዲናይቱ የሚታየው ሁኔታ በፍፁም አስተማማኝ አይደለም። አራተኛው እና የመጨረሻው አማራጭ በሊቢያ የተወሰነ ዓለም አቀፍ የሰላም ተልዕኮ መጀመር ይሆናል። ይህ የሊቢያ ምክር ቤት ካቀረበው ጥሪ ጋር ይመሳሰላል። በሊቢያ የተወሰነ ዓለም አቀፍ የሰላም ተልዕኮ የሚሠማራበት ፍላጎት በመዲናይቱ ትሪፖሊ አንድ መንግሥት የመመሥረት እና ካለውጭ የጦር ጣልቃ ገብነት ሥልጣኑን በመላ ሀገር የማስፋፋት ዓላማ ይዞ ነው የተነሳው። ይሁን እንጂ፣ በነዳጅ ዘይት በታደለችው ሰሜን አፍሪቃዊቷ ሊቢያ ውስጥ ይህን ዓይነት የሰላም ማስከበሪያ ተልዕኮ ሥምሪት እውን የማድረጉን እድል የአውሮጳ የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት ባልደረባ ማቲያ ቶአልዶ የመነመነ ሆኖ ያዩታል።

« በትልቆቹ ኃያላት ሀገራት ዘንድ ይህን ዓይነት ተልዕኮ የመጀመሩ ፍላጎት አይታየኝም። ጣልቃ ለመግባት ፍላጎት ያሳዩት ሁለቱ ሀገራት ግብፅ እና ኢጣልያ ብቻ ሲሆኑ፣ ይኸው ጣልቃ ገብነት የሰብዓዊ ርዳታ በማቅረቡ ወይም ፖለቲካ ወይም ወታደራዊ ርምጃ በመውሰዱ ይሁን አይሁን በግልጽ ከማሳወቅ ተቆጥበዋል። የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ይሠማራ እንኳን ቢባል የት የሚለው ቴክኒካዊ ጥያቄን መመለሱ አዳጋች ነው፣ ምክንያቱም፣ በአሁኑ ጊዜ ሊቢያ ውስጥ አንድ ሳይሆን 20 ግንባሮች ናቸው ያሉት፣ ይህ ሁኔታውን ውስብስብ አድርጎታል። እና ሰላም አሰከባሪዎቹን የት ነው የምታሠማራው? »

የተወሰነ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበሪያ ተልዕኮ በማሠማራት ጥያቄ ላይ በመጀመሪያ በሊቢያውያን መካከል ስምምነት መደረስ ይኖርበታል። የአውሮጳ የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት ባልደረባ ማቲያ ቶአልዶ እንደታዘቡት ግን፣ በወቅቱ ውጊያ በማካሄድ ላይ የሚገኙት የሊቢያ ሚሊሺያ ቡድኖች የተኩስ አቁም ስምምነት የመድረስ ፍላጎት ያላቸው አይመስልም።

አንድሪያስ ጎርሴቭስኪ/አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic