የሊቢያዉ ጦርነት፥ ዲፕሎማሲዉና ምዕራቡ አለም | ዓለም | DW | 10.03.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሊቢያዉ ጦርነት፥ ዲፕሎማሲዉና ምዕራቡ አለም

ዩሮ-ዶላር የሚዛቅበት ነዳጅ ዘይት እዚያዉ እየከሰለ ነዉ።ከሁለት ሳምንት በፊት በየአዉራ ጎዳናዉ የሚሰማዉ የመኪና ጥሩምባ፥ የከበሮ ድምድምታ በቦምብ ግምግምታ ተለዉጧል።የሰዎቹ-ዉካታ በጣር ጩኸት።እና ጥፋት።

default

የአማፂያኑ ምሽግ

የሊቢያዉ መሪ የኮሎኔል ሙዓመር አል-ቃዳፊ ታማኝ ጦርና የሐገሪቱ አማፂያን ሰሜናዊ ሊቢያ ዉስጥ የጀመሩት ዉጊያ ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።ተፋላሚ ሐይላት በዲፕሎማሲዉም መስክ ድጋፍ ለማግኘት ተቀናቃኝ ዘመቻ ጀምረዋል።የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የሊቢያን የአየር ክልል መቃኘት መጀመሩን አስታዉቋል።የኔቶ አባል ሐገራት የመከላከያ ሚንስትሮች እና የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት መሪዎች በሊቢያ ላይ ሥለሚወስዱት እርምጃ ብራስልስ ዉስጥ በየፊናቸዉ ተሰብስበዉ እየተወያዩ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ የሊቢያን ወቅታዊ ሁኔታ ባጭሩ ይቃኛል።

የሜድትራንያን ባሕር የተንተራሱት የቤንጋዚ፥ የአዛ-ዛዊያሕ፥ የቤርጋ፥ የራስ ላንፉ ከተሞች ዉሎ-አዳር ባጭር ጊዜ ተለዋወጠ።ከሁለት ሳምንት በፊት የሠልፈኛ ዉካታ-ጭፈራ-መፈክር ያስተጋባባቸዉ የነበሩት እንያ የነዳጅ ቋቶች ዛሬ ታንክ፣ መድፍ፥-ያጓራባቸዋል።ጥይት፥ ሮኬት፥ ያፋጩባቸዋል።ጄት፥ ሔሊኮብተር ያስገመግባቸዋል።

ዩሮ-ዶላር የሚዛቅበት ነዳጅ ዘይት እዚያዉ እየከሰለ ነዉ።ከሁለት ሳምንት በፊት በየአዉራ ጎዳናዉ የሚሰማዉ የመኪና ጥሩምባ፥ የከበሮ ድምድምታ በቦምብ ግምግምታ ተለዉጧል።የሰዎቹ-ዉካታ በጣር ጩኸት።እና ጥፋት።

የአለም ቀይመስቀል ኮሚቴ እንደሚለዉ ያቺ ሠፊ፥ የነዳጅ ዘይት ባለጠጋ ሐገር ከእርስ በርስ ጦርነት እየተዘፈቀች ነዉ።የኮሚቴዉ ሊቀመንበር ያኮብ ኬለንበርገር ዛሬ እንዳስታወቁት በጦርነቱ እየቆሰለ ወደየ ሆስፒታሉ የሚሔደዉ ሰዉ ቁጥር እለት በእለት እጨመረ ነዉ።አለም አቀፉ ድርጅት በጦርነቱ የተጎዱትን ይረዳ ዘንድ የሊቢያ ባለሥልጣናት እንዲፈቅዱለት ሊቀመንበር ኬለንበርገር ተማፅናዋል።

Libyen Aufständische Kämpfer bei Brega

አማፂያኑ

ኬለንበርገር ፍቃድ የጠየቁት የትኞቹን ባለሥልጣናት እንደሆነ ግን ግልፅ አይደለም።ሊቢያ ሁለት ሐይላት አቃርጠዉ የሚቆጣጠሯት፥ የሚፋለሙባት ሐገር ናት።በዛሬና በትናንቱ ፍልሚያ የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ጎራ የበላይነቱን ይዟል።የቃዛፊ ታማኝ ጦር አማፂያኑን ትናንት ከዛዊያሕ ከተማ አባሮ-ዛሬ የራስ ላንፉን መዳራሻ እደበደበ ነዉ።መንበሩን ቤንጋዚ ያደረገዉ ብሔራዊ ካዉንሥል የተሰኘዉ የአማፂያን ስብብብ በአምደ መረቡ ባወጣዉ መግለጫዉ እንዳለዉ እስከመጨረሻዉ ይፋለማል።

«ምርጫችን ሁለት ነዉ» አለ መግለጫዉ፥ «አንድም ነፃነትና እድገት፥ አለያም በሙዓመር ቃዛፊ ጫማ ሥር ባርነት።» ሰዉዬዉም እንደፎከሩ ነዉ።«በሊቢያ ላይ የተቀነባበረ ሴራ አለ።ሊቢያን ለመቆጣጠርና ነዳጅ ዘይታችንን ለመዝረፍ ያለመ ሴራ።ሊቢያዉያን በቁማቸዉ ይሕን አይፈቅዱም።ይፋለማሉ እንጂ።»

የአብዮታዊዉ መሪ መልዕክት በአዉሮጳና በአሜሪካኖችንም ላይ ያነጣጠረ ነዉ።የሁለቱ ወገኖች ዉጊያ-ዛቻ ሊቢያን ሲያነድ የተፋላሚዎች ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ከካይሮ-እስከ ፓሪስ ይቀለጣጠፍ ይዟል።ትናንት ካይሮ የገቡት የሊቢያ ምክትል መከላከያ ሚንስትር ከግብፅ ወታደራዊ መሪዎችና ከአረብ ሊግ ባለሥልጣናት ጋር ተነጋግረዋል።

ሞልታ፥ ሊዝበን፥ አቴንስ የገቡት መልዕክተኞችም ከየሐገራቱ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል።ወደ ፓሪስ ያቀኑት ግን የፈረንሳይ ባለሥልጣናትን ማነጋገር-አለመነጋገራቸዉ አልታወቀም።እዚያዉ ፓሪስ የሚገኙት የቃዛፊ ተቃዋሚዎች ግን ለቡድናቸዉ የፈረንሳይን እዉቅናና ሙሉ ድጋፍ አስግኝተዋል።

ፈረንሳይና ጀርመን ይዘዉሩታል የሚባለዉ የአዉሮጳ ሕብረት ዛሬ በዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ነገ ደግሞ በመሪዎች ደረጃ ሥለ ሊቢያ እየተነጋገረ ነዉ-ይነጋገራልም።የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮችም ብራስልስ ዉስጥ እየተወያዩ ነዉ።ዉይይቱ በሊቢያ ላይ የበረራ እገዳ ማዕቀብ-ይጣል አይጣል ነዉ።የጦር ተሻራኪዉ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንደርስ ፎግሕ ራስሙሰን ጦራቸዉ በሊቢያዉ ዉጊያ ጣልቃ አይገባም ይላሉ።
«ኔቶ ሊቢያ ጣልቃ የመግባት አላማ ፈፅሞ የለዉም።ጦራችን ለሁሉም ክስተት አስፈላጊዉን ዝግጅት እንዲያደርግ ነግረናል።ለዘመቻ ግን አልወሰንም።»

Libyen Aufständische Kämpfer bei Brega Panzer

የቃዛፊ ታማኝ ጦር

ዋና ፀሐፊዉ ትናንት ይሕን ይበሉ እንጂ የኔቶ ጦር የሊቢያን የአየር ክልል ለሃያ-አራት ሠአታት መቃኘት መጀመሩን አስታዉቋል።

ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ