የሊቢያዉ ድብደባና ጉባኤ | ዓለም | DW | 15.04.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሊቢያዉ ድብደባና ጉባኤ

የዶሐ፥ በርሊን ካይሮዉ ጉባኤ አስገምግሞ ሳያበቃ-ዛሬ የአዉሮጳ ሕብረት እና የኔቶ አባል ሐገራት አምባሳደሮች እንደገና ሥለ ሊቢያ ለመነጋገር እንደገና በርሊን ተሰብስበዋል።

default

የሊቢያዉ ዉጊያና ድብደባ የተለያዩ ሐገራትና ማሕበራት ባለሥልጣናትን ከጉባኤ፥ ጉባኤ እያጣደፈ ነዉ።ሊቢያን የሚያስደድቡት ሐገራትና ተባባሪዎቻቸዉ «አገናኝ ቡድን» ያሉት ስብስብ ባለፈዉ ሮብ ዶሐ-ቀጠር ላይ ያደረገዉ ጉባኤ ዉጤት በቅጡ ሳይታወቅ፥ የኔቶ አባል ሐገራት ተወካዮች ትናንት በርሊን ዉስጥ ተሰብስበዉ ነበር።ይሁንና ስብሰባዉ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ከሥልጣን ለማስወገድ ኔቶ የሚያደርገዉን ድብደባ እንዲያጠናክር በሚሹት በብሪታንያና በፈረንሳይ እና ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲፈለግ በሚጠይቁት ሐገራት መካካል ያለዉን ልዩነት ማጥበብ አልቻለም።የኔቶ ዋና ፀሐፊ አንድረስ ፎግሕ ራስሙስን አቀራራቢ ያሉት ሐሳብ ሁለቱንም እኩል ማስተናገድ ነዉ።
«ይሕ የዘመቻችን ግልፅ አለማ ነዉ።የሊቢያ ሠላማዊ ሰዎችን ከጥቃት ማዳን።ለዚሕ ችግር ወታደራዊዉ እርምጃ ብቻ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ሙሉ በሙሉ አምናለሁ።»

የኔቶ ባለሥልታናት የሊቢያ ዘመቻቸዉንና ልዩነታቸዉን እያነሱ ሲጥሉ-ትናንት የአረብ ሊግ ሌላ መፍትሔ ፍለጋ፥ ሌላ ጉባኤ ካይሮ ዉስጥ አስተናግዶ ነበር።በጉባኤዉ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፥ የአፍሪቃ ሕብረትና የአዉሮጳ ሕብረት ተወካዮች ተካፋዮች ነበሩ።ጉባኤተኞች ለሊቢያዉ ቀዉስ መፍትሔ ፍለጋ መሰብሰባቸዉን ቢያስታዉቁም የጋራ አቋም አልታየባቸዉም።የጉባኤዉ አስተናጋጅ አምር ሙሳ የሊቢያን ጉዳይ በቀጥታ ከማንሳታቸዉ በፊት ዙሪያ ጥምጥም መጓዙን ነበር-የመረጡት።

«በአረቡ ዓለም ሕዝባዊ የነፃነት ንቅናቄ እየተደረገ መሆኑን እናዉቃለን።ንቅናቄዉ አካባቢዉን እያጥለቀለዉ ነዉ።የሐሳብ ነፃነትና ዲሞክራሲን እንደግፋለን።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን በተለይ ለሚስራታ ከተማ ሕዝብ ሠብአዊ ርዳታ እንዲደርስ ተማፅነዋል።ባለፈዉ ሳምንት የሞከረዉ ሠላማዊ ድርድር የከሸፈበት የአፍሪቃ ሕብረት አሁንም ድርድር እንዳለ ነዉ።የአዉሮጳ ሕብረት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ወይዘሮ ካትሪን አሽተን ግን የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ታማኞችን ነዉ-ያስጠነቀቁት። «እኒያ የሥርዓቱ አባላት ሚናቸዉን መለየት አለባቸዉ።አንድም የኮሌኔል ቃዛፊ ጨቃኝ ሥርዓት አካል ሆነዉ መቀጠል፥ አለያም ለዲሞክራሲያዊ ሽግግር መሥራት አለባቸዉ።»

የዶሐ፥ በርሊን ካይሮዉ ጉባኤ አስገምግሞ ሳያበቃ-ዛሬ የአዉሮጳ ሕብረት እና የኔቶ አባል ሐገራት አምባሳደሮች እንደገና ሥለ ሊቢያ ለመነጋገር እንደገና በርሊን ተሰብስበዋል።የዩናይትድ ስቴትስ፥ የፈረንሳይና የብሪታንያ መሪዎች በፋንታቸዉ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ መወገድ አለባቸዉ በሚል አቋማቸዉ እንደፀኑ መሆናቸዉን በድጋሚ አስታዉቀዋል።ሩሲያ ግን ለሊቢያዉ ቀዉስ ሐይል መትሔ አይሆንም ብላለች።ኔቶ አለቅጥ የበዛ ሐይል መጠቀሙን እንዲያቆምም ሞስኮ አሳስባለች።

ነጋሽ መሐመድ