የሊማዉ የአየር ንብረት ጉባኤ ፍፃሜና ዉጤቱ | ዓለም | DW | 16.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የሊማዉ የአየር ንብረት ጉባኤ ፍፃሜና ዉጤቱ

የሊማዉ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ የበለፀጉትና ደሀ ሃገራት ለአየር ንብረት ለዉጥ ሊደረግ ይገባል የሚሏቸዉ አጣዳፊ ጉዳዮች በመለያየታቸዉ ምክንያት ብዙም ዉጤት ያመጣል የሚል ተስፋ ሳያሳድር ነበር የተጀመረዉ።

ከኅዳር 22 ቀን አስቶ የተጀመረዉ ይኸዉ ጉባኤ ከአስርቀናት በኋላ ሲጠናቀቅ ተጨማሪ ሁለት ቀናት ታክሎበት ለመጪዉ የፓሪሱ ጉባኤ በመጠኑም ቢሆን መንገድ ጠርጎ ነዉ። ያም ቢሆን ግን የተሳታፊዎቹ ስሜት ለሁለት የተከፈለ ይመስላል አንዱ አዎንታዊ ሌላዉ በጥርጣሬ የሚታዘብ።

ዓርብ ይጠናቀቃል ተብሎ የተገመተዉ የተመድ የአየር ንብረት ጉባኤ ሁለት ቀን ተራዝሞ እሁድ ዕለት ሲጠናቀቅ አንድ እልባት ላይ ደርሶ ነዉ። የአየር ፀባይ ለዉጥ ያስከተለዉ ወደከባቢ አየር የሚለቀቀዉ አደገኛ ጋዝን ለመቀነስ መንግሥታት በየበኩላቸዉ ቃል ገብተዉ ማለት ነዉ።

በችኮላም ቢሆን ተሰብሳቢዎቹ በመጨረሻ በጎርጎሪዮሳዊ 2015ዓ,ም ፓሪስ ላይ በሚካሄደዉ እንዲፀድቅ ለድርድር ሊቀርብ የሚችል መነሻ ዉሳኔም ነድፈዋል። በሀገሩ አቆጣጠር ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ተኩል ላይ የጉባኤዉ ዋና አደራዳሪ የፔሩ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ማኑዌል ፑልጋር-ቪዳል በእጃቸዉ በያዙት መዶሻ ጠረጴዛዉን በመምታት፤ «ሰነዱ ያለምንም ተቃዉሞ ተቀባይነት አግኝቷል።» አሉ።

በዚህ መሠረትነትም ሃገራት የቀድሞዉን ስምምነት በመሰናበት በጎርጎሪዮሳዊዉ 2020 ሥራ ላይ የሚዉለዉን አዲስ ስምምነት ፓሪስ ላይ ያፀድቃሉ። እናም መንግሥታት በመጪዉ የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የፀደይ ወራት ማለት ከመጋቢት አጋማሽ እስከሰኔ አጋማሽ ባሉት ጊዜያት ለወደፊቱ የአየር ንብረትን ለማስተካከል በየበኩላቸዉ ለማድረግ ያቀዱትን ማቅረብ ይኖርባቸዋል። የጀርመን ተደራዳሪ ልዑካን መሪ ዮኻን ፍላዝባርት ሀገራቸዉ ከዚህም የተሻለ ጠንከር ያለ አቀራረብ እንዲኖር ብትመኝም ያሁኑም ቀላል እንደማይባል ነዉ የሚገልፁት፤

«እንዲያም ሆኖ አሁን የተገኘዉ ዉጤት ለቀጣይ ድርድር መልካም መሠረት የጣለ ነዉ።»

ምንም እንኳን የሊማዉ የአየር ንብረት ጉባኤ ለመጪዉ የፓሪሱ ስብሰባ፤ ሃገራት በቀጣይ ለሚደረሰዉ ዉሳኔ የየራሳቸዉን ሃሳብ ያቀርቡበታል ቢባልም አብዛኞቹ አዳጊ ሃገራት የበለፀጉትና ደሀ ሃገራት ሊያደርጉ ይገባል የሚለዉ ግልፅ አይደለም በሚል ተችተዋል። የበለፀጉት ሃገራት እንደዋና ጉዳይ ያዩት ከባቢ አየርን የሚበክለዉን የአደገኛ ጋዝ ልቀት ቅነሳ ነዉ። አዳጊ ሃገራቱ ደግሞ ከእነሱ ወገን በአየር ጠባይ ለዉጥ ምክንያት ለተጎዱ ሃገራት ሊሰጡት የሚገባዉ የገንዘብ ድጋፍ እልባት ማግኘቱን አጥብቀዉ ሲሹ ታይተዋል።

ከዚህም ሌላ በጉባኤዉ የበለፀጉትና ፈጣን እድገት እያሳዩ የሚገኙት እንደቻይና እና ሕንድ ያሉ ሃገራት ያላቸዉ ኃላፊነትም ግልፅ ተደርጓል። የሕንዱ ተወካይ ከጉባኤዉ «የምንፈልገዉን አግኝተናል» ሲሉ የቻይናዉ ቃል አቀባይ ደግሞ «መልካም መሠረት የጣለ» ጉባኤ ነበር ብለዉታል። በተቃራኒዉ ጀርመንና ሌሎች የበለፀጉ ሃገራት ኤኮኖሚያቸዉ እያደገ የሚገኝ ሃገራት ወደከባቢ አየር የሚለቁትን የበካይ ጋዝ መጠን ለመቀነስ ቃል መግባት እንዳለባቸዉ ጠይቀዋል። ከዚህም ሌላ በሊማዉ ጉባኤ የበለፀጉና ደሀ ሃገራት የተለያየ ጎራ ዳግም ፈጥረዉ ታይተዋል። ይህ ዉዝግብ ነዉ ባለፈዉ ዓርብ ይጠናቀቃል የተባለዉ ጉባኤ እስከእሁድ እንዲራዘም ግድ ያለዉ። ሂደቱ አድካሚ ቢሆንም በዉጤቱ መደሰታቸዉን ነዉ የጀርመን ልዑካን መሪ ዮኻን ፍላዝባርት የገለፁት፤

«በፍፁም አላዘንኩም። እርግጥ ነዉ ደክሞኛል ግን አንድ አግባቢ ዉጤት ላይ በመድረሳችን ደስተኛ ነኝ።«

የጉባኤዉ ዉጤት ግን ሁሉንም አላስደሰተም አካባቢ ጥበቃ ላይ ለሚሠራዉ የኦክስፋም ባልደረባ ያን ኮቫልሲግ ደካማ ሰነድ ነዉ ለፓሪስ የተደገሰዉ፤

«እርግጥ ነዉ ይህ ሰነድ ከሊማዉ ጉባኤ ወደፓሪሱ ይወስደን ይሆናል ነገር ግን ይህ ብቻ ነዉ። የወረቀቱ ይዘት ሲታይ ግን በጣም በሚያሳዝን መልኩ ደካማ ነዉ፣ አደገኛ በሆነ መልኩ ደካማ።»

በምሳሌነት ካነሱት መካከልም እስከጎርጎሪዮሳዊዉ 2020ዓ,ም ድረስ የአየር ንብረትን ለመጠበቅ ሃገራት ማድረግ የሚኖርባቸዉ አለመገለፁን ትልቅ ጉድለት ብለዉታል። ለተፈጥሮ ጥበቃ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርገዉ ዓለም ዓቀፍ ድርጅት WWF ባልደረባ ሬጊና ጉንተር በበኩላቸዉ አዝነናል ነዉ ያሉት፤

«ከጉባኤዉ የምንፈልገዉን ምንም አላገኘንም ማለት ይቻላል። ይህ ነዉ የሚባል ጠንካራ የመረጃ ፍሰት መስመር አልተገነባም፤ እናም እያንዳንዱ የፈለገዉን ማድረግ ይችላል። በጣም ነዉ ያዘንነዉ።»

በጉባኤዉ ከታቀደለት ሁለት ቀን ጨምሮ ባዶ ከሚባል ዉጤት ቢድንም አሁንም እስከፓሪሱ ጉባኤ ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ብዙ ሥራዎች ይጠብቋቸዋል።

ያኮብ ማይር / ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic